Print this page
Saturday, 11 June 2022 19:45

“የጓሮ ማህበረሰብ” ኤግዚቢሽን ዛሬ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  “የጓሮ ማህበረሰብ” (home gardening community) የተሰኘው ድረገጽ ያሰናዳውና ትኩረቱን የከተማ ግብርና ላይ ያደረገው “የጓሮ ማህበረሰብ” ኤግዚቢሽን  ዛሬ ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም  ካዛንቺስ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ይከፈታል፡፡
በዚህ ኤግዚብሽን ላይ ክረምቱን ተከትለው ለምግብነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ችግኞች፣ቤትና ግቢ ማስዋቢያዎች፣ ከግብርና ጋር የተያያዙ እውቀቶችን የያዙ መፅሐፍት፣የግብርና ባለሙያዎች፣የመማሪያ መድረኮችና  በርካታ ፋይዳ ያላቸው ሁነቶች እንደሚካሄዱ “የጓሮ ማህበረሰብ” ድረ ገጽ መስራች እና የኤግዚቢሽኑ አዘጋጅ አቶ ስለሺ ባየህ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
“ዝናቡ ሲመጣ ገበሬው ከቤቱ ይወጣል” በሚል ማራኪ መሪ ቃል የሚካሄደው ኤግዚብሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን በርካታ ባለድርሻ አካላት በአጋዥነትና በተሳታፊነት አብረው እንደሚገኙም አቶ ስለሺ ጨምረው የገለፁ ሲሆን በዕለቱም ከከተማ ግብርና፣ከጤናና ከተያዥ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ያላቸው ድንቅ ሀሳቦችን የያዘ መፅሔትም እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡
የጓሮ ማህበረሰብ ድረ ገፅ በ2012 ዓ.ም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትንና ከእንቅስቃሴ መገደብን ተከትሎ ሰዎች በግቢያቸው ያለውን ማንኛውንም ክፍት ቦታ ተጠቅመው ለምግብነት የሚያገለግሉና ለግቢና ለቤት ማስዋቢያነት የሚጠቅሙ አትክልቶችንና አበባዎችን እንዴት መጠቀም ይቻላሉ? የሚለውን ሀሳብ መነሻ በማድረግ የተመሰረተ ሲሆን በዚህ ድረ ገፅ ብዙዎች ስለከተማ ግብርና፣ስለጤና፣ጠባብ ግቢን በአግባቡ ስለመጠቀምና ችግኞችን ስለመለዋወጥ በርካች የተማማሩበት መድረክ ሆኖ ከመቀጠሉም በላይ ከ27 ሺህ በላይ ተከታዮችን ማፍራት መቻሉን አቶ ስለሺ ባዬህ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ የጓሮ ማህበረሰብ ሁለተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉንም እያበረከተ ይገኛል።

Read 1202 times