Saturday, 11 June 2022 18:22

የአሥሩ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ - በአገራዊ ምክክሩ ጉዳይ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ከሰሞኑ አሥር የፖለቲካ ድርጅቶች በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በጋራ ለማቅረብ የጋራ የምክክር መድረክ አቋቁመዋል፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች፡- መድረክ፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲ፣ የአፋር ፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ አረና ትግራይ እና የዶንጋ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ናቸው፡፡
የተቋቋመው የምክክር መድረክም በዋናነት አሁን ያለውን የምክክር ኮሚሽን አመሰራረትና የምክክሩ መመሪያ አዋጅ አወጣጥ ሂደትን የሚቃወም ሲሆን  ሂደቱ እንደገና ሁሉን አካታችና አሳታፊ  በሆነ መልኩ መጀመር አለበት የሚል አቋምን የሚያንጸባርቅ መሆኑ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በአገራዊ ምክክር ሂደቱ በትጥቅ ጭምር የሚፋለሙ ሃይሎች መሳተፍ አለባቸው፤አፋጣኝ የተኩስ አቁም መደረግ አለበት፤የምክክሩ አጀንዳዎች ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ መመረጥ አለባቸው፤ እንዲሁም ውይይቶቹ ዓለም አቀፍ ታዛቢ በተገኘበት ሊደረጉ ይገባል የሚል አቋም ይዘዋል ፓርቲዎቹ፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከሕብር ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ በቀለ ጋር  ባደረገው አጭር ቆይታ፣ ስለ አስሩ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ ማብራሪያ ሰጥተውታል፡፡ እነሆ፡-

            ስብስቡ ምንድን ነው?
ሁሉም እንደሚያውቀው የኛ ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ አስቀድሞም ከምርጫው በፊት ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል የሚል አቋም ይዞ ሲወተውት ነበር፡፡ ያንን መንግስት ሳይቀበለው አልፎት ነው የሄደው። ከዚያ በኋላም የምርጫ መወዳደሪያ ማኒፌስቶ መሪ መፈክር (ሞቶ)፤ "ያለ ብሔራዊ መግባባትና ሃገራዊ እርቅ የሚሰፍን ሠላም፣ የሚገነባ ዲሞክራሲና የምንሻገረው ችግርና መከራ የለም" የሚል ነበር፡፡ አሁን ከሁለት ወር በፊት ጉባኤያችንን ስናደርግም መሪ መፈክራችን ይሄው ሃሳብ ነበር፡፡ ይሄንን ሃሳባችንን በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክክር ቤት ስናስተጋባ ቆይተናል፡፡ በወቅቱ ጠ/ሚኒስትሩም መልካም ሃሳብ መሆኑን አምነውበት የተወሰኑ ፓርቲዎችን ሰብስበው እንዳነጋገሩ ይታወሳል፡፡ አሁን በድጋሚ ይሄ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉዳይ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ተነስቶ ውይይት ተደረገበት፡፡ በውይይቱ ወቅት የተወሰንን ፓርቲዎች በተለይ በመንግስት የተቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አመሰራረቱም አካሄዱም ችግር እንዳለበት አስረዳን፡፡ በምክከሩ ላይ ያሉ እንከኖች ደግሞ በሃገሪቱ ውስጥ  ይመጣል ብለን የያዝነውን ተስፋ ያጨናገፈ መሆኑን፤አሁን በተያዘው መንገድ የትም እንደማይደረስ አስረዳን፡፡

ስለ ምክክሩ ህግ ከማውጣት ጀምሮ እስከ ኮሚሽኑ አባላት መረጣና አሰያየም ያሉ  ችግሮችን ነቅሰን አወጣን፡፡ በሌላ ወገን ያሉ ፓርቲዎች ደግሞ "ችግሩ እንዳለ እኛም እንረዳለን፣ ነገር ግን መፍትሔው ሊሆን የሚገባው አሁን ያለውን ነገር አድሰን ቀባብተን አስተካክለን መቀጠል እንጂ ሂደቱ እንደ አዲስ መጀመር የለበትም" የሚል አቋም ያዙ፡፡ በእነዚህ ሁለት አቋሞች ላይ በምክር ቤቱ ድምጽ እንዲሰጥ ተደረገ። 13 ለ39 የሆነ የድምጽ ልዩነት ተፈጠረ። አስራ ሦስታችን የምክክሩ ሂደት በሙሉ ለሙሉ እንደገና መፈተሽ አለበት የሚለውን አቋም ያዝን፤ ሌሎቹ ባለበት ለመቀጠል ወሰኑ ማለት ነው፡፡ ይሄ የ13 ፓርቲዎች ቡድን በም/ቤቱ የተሰጠውን ድምጽ በፀጋ ተቀብሎ፣ ነገር ግን እኛ በጋራ መመካከር አለብን ብሎ በጋራ ተገናኝቶ መክሮ አቋሙን በመግለጫ ይፋ አደረገ ማለት ነው፡፡
አብላጫው የምክር ቤቱ አባላት አሁን ባለው ኮሚሽን አካሄድና አሠራር ተስማምተዋል ማለት ነው?


ግልፅ መሆን ያለበት እኛ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች አብዛኞቹ ይጋሯቸዋል፤ ነገር ግን በሚስተካከልበት መንገድ ላይ ነው የተለያየነው፡፡ በምክክሩ አስፈላጊነት፣ ወቅታዊነትና አላማው ላይ በመካከላችን ምንም ልዩነት የለም፡፡ ሂደቱ ላይ ነው ትልቁ ልዩነት፡፡ ኮሚሽኑ ሲቋቋም አሳታፊነቱ ትክክል አልነበረም፡፡ እኛ ስለ ኮሚሽኑ መቋቋም እየተመካከርን ባለበትና ለፓርላማው አፈ ጉባኤም ለፍትህ ሚኒስትሩም "ፓርቲዎች በጋራ ተመካክረን የደረስንበትን ግብአት ሊሆን የሚችል ነገር ይዘን  እንመጣለን፤ቀጣይ ምክክር እናደርጋለን" ብለን ሳለ ይሄን ዘለው ገዥው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ በሚቆጣጠረው ፓርላማ ወስደው አዋጅ አድርገውት አመጡልን፡፡ "ይሄ አዋጅ እኛ አልተሳተፍንበትም፤ ለኛም ግልጽ አልነበረም፤ ሁሉን አካታች ስላልሆነ ልክ አይደለም" ብለን እየተከራከርን ባለበት፣ እንደገና ደግሞ እኛ የማናውቃቸው፣ ከዚህ በፊት ትልልቅ የመንግስት ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎችን ሁሉ አካትተው፣ በአገሪቱ ነፃና ገለልተኛ ሰው የጠፋ አስመስለው ይዘው መጡ፡፡ እኛ ይሄን አንቀበልም፡፡ አዋጁም የኮሚሽነሮቹም ሹመት ትክክለኛ አካሄድን የተከተሉ አይደሉም፡፡ እንደገና አሳታፊ በሆነ መንገድ መዋቀር አለበት ነው፤ አቋማችን፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በቃ አንዴ ሆኗል፤ እንዲያስተካክሉ አድርገን እንቀጥል ነው፤ ሃሳባቸው፡፡


ያሰባሰባችሁ የምክክር ኮሚሽኑ ጉዳይ ብቻ ነው ወይስ ከዚያም ያለፈ አጀንዳ አላችሁ? የናንተ ፓርቲ አሁንም ድረስ የሚያቀነቅነው "የሽግግር መንግስት ይቋቋም" ጥያቄ ስላለ ነው ይሄን ያነሳሁት?
የለም፤ ያሰባሰበን የምክክር ኮሚሽኑ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ያለፈ ምንም በጋራ የያዝነው አቋም፣ የወሰንነው ውሳኔም የለም። የሽግግር መንግስት ጥያቄው የኛ ነው፡፡ ሃገሪቱ አሁን ላለችበት ችግር መፍትሄ ይሆናል ያልነው ሃሳብ ነው፡፡ ሃሳቡም የህብር ኢትዮጵያ ነው፡፡
በምን መልኩ ነው በኮሚሽኑ ላይ ያላችሁን ጥያቄ ይዛችሁ እንዲስተካከል ተፅዕኖ የምታሳርፉት?
አሁነ የያዝነው አቋም በራሱ አንዱ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ መከፈል ፖለቲካዊ ስህተት ነው ብለው አቋሙ የያዙ አሉ። ሙሉ በሙሉ ከእንዲህ አይነት ሂደት ራሳቸውን ያገለሉም አሉ፡፡ ኦፌኮ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ የያዟቸው አቋሞች አሉ፡፡

በዚያው ልክ ደግሞ በጋራ የሚያስማሙን ጉዳዮች አሉ፡፡ ስለዚህ በጋራ ግፊት ማድረጉ አንድ ነገር ላይ ያደርሰናል የሚል ሃሳብ አለን፡፡ ሰዎች ሊያውቁት የሚገባው ግን በመሃከላችን ምንም አይነት ስትራክቸራል ግንኙነት አልተፈጠረም፡፡ የጋራ የፖለቲካ ራዕይም የለንም፡፡ ጥያቄውን በጋራ እናቅርብ ነው ጉዳዩ፡፡
ከምክክር ኮሚሽኑ አባላት ጋር ውይይት አላደረጋችሁም ?
በፓርቲያችን የጋራ ምክከር ቤት ውስጥ ቀርበው ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከዚያ ባለፈ ግን ለብቻ አልተወያየንም። ከዚህ በኋላ እንዴት እናድርግ የሚለውን ማለትም ከመንግስትም ሆነ ከኮሚሽኑ ጋር ግንኙነታችን እንዴት ይሁን የሚለውን በጋራ መክረን እንወስናለን፡፡


Read 1394 times