Tuesday, 07 June 2022 07:06

ኢትዮ ቴሌኮም በ66 የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የዲጂታል መማሪያ ማዕከላትን አቋቋመ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ብሎም የነገ ሃገር ተረካቢ ዜጎችን በዕውቀት ለማነጽ የሚደረገውን ሁለገብ ሀገራዊ ጥረት ለማገዝ፣ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች በተመረጡ 66 የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ኮምፒውተሮች፣ ልዩ ልዩ የትምህርት ቤት መገልገያ መሳሪያዎችንና ከፍተኛ ፍጥነት ያለው መደበኛ የብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት በማሟላት ያቋቋማቸውን የዲጂታል መማሪያ ማዕከላት (digital learning centers) ከትላንት በስቲያ አስመርቋል፡፡
ኩባንያው በመላ አገሪቱ ለሚገኙ 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ45.48 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 1ሺ386 ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችን፣ 1ሺ386 ጠረጴዛዎችና ወንበሮችን፣ የትምህርት ቤት መገልገያ መሳሪያዎችን በማሟላት የዲጂታል የመማሪያ ማዕከሎቹን ያቋቋመ ሲሆን በዚህም ከ140 ሺ 596 በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ከእነዚህ 66 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 18 ትምህርት ቤቶች በአዲስ አበባ፣ ቀሪዎቹ 48 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በክልሎች የሚገኙ ሲሆን ተጠቃሚ ትምህርት ቤቶቹ የተመረጡት በአዲስ አበባና ክልል ትምህርት ቢሮዎች ከኢትዮ ቴሌኮም የሪጅንና የዞን ጽ/ቤቶች ጋር በመተባበር መሆኑ ታውቋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ “ተማሪዎች ከሌላ ት/ቤት ተማሪዎች ጋር መረጃ በቀላሉ መለዋወጥ እንዲችሉ፣ የምርምር ስራዎችን ለማከናወን እንዲሁም የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማና የተሻለ ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፤ #በተለይም ያለንበት ዘመን የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ መጠን፣ የዲጂታል መማሪያ ማዕከሎቹ መገንባት የቴክኖሎጂና አዲስ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር፣ ተማሪዎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂው ጋር እንዲጓዙ ለመደገፍ፣ የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ የበጎ ፈቃደኛ ሰራተኞች በትምህርትና በሥልጠና በማጎልበት ዕውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ለሚኖሩበት ማህበረሰብ እንዲያካፍሉ እንዲሁም ሙያዊ ትንታኔና ችግር ፈቺ ክህሎቶችን ለማዳበር ለት/ቤቶችና ተማሪዎቻቸው ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡;

Read 1429 times