Saturday, 04 June 2022 14:23

ኢሠመጉ ድብደባ የተፈፀመበትን የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጉዳይ እየተከታተለ መሆኑን ገለፀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


              በፖሊስ ጣቢያ በጠያቂ ቤተሰቦቹ ፊት በፀጥታ ሃይሎች ድብደባ የተፈፀመበትን የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጉዳይ ኢሠመጉ በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ገልጿል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ታስሮ በሚገኝበት አዲስ አበባ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ከትላንት በስቲያ ግንቦት 25 ከቤተሰቦቹ  ጋር እየተነጋገረ ባለበት ወቅት በሁለት ፖሊሶች መደብደቡን ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ አስታውቋል፡፡
ሃሙስ ረፋድ ላይ ተመስገንን ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ማምራቱን፣ በወቅቱም በመካከላቸው ባለው ከ10 ሜትር የበለጠ ርቀት የተነሳና ተመስገን ከዚህ ቀደም በእስር ላይ ሳለ ባጋጠመው የጆሮ ህመም ምክንያት መደማመጥ እንዳቃታቸው የሚናገረው ታሪኩ፤ ፖሊሶቹን “ትንሽ ቀረብ ብሎ ቢያወራኝ” ብሎ በሚያስፈቅድበት ወቅት ፖሊሶቹ ወደ ድብደባ መግባታቸውን ይገልጻል፡፡
ተመስገን ፖሊሶቹን ለማግባባት ቢሞክርም ፖሊሶቹ ከተጠያቂ እስረኞች መሃል ጎትተው በማውጣት በቦክስና በጫማ ጥፊ ለሁለት እንደደበደቡት ታሪኩ ያስረዳል፡፡
ይህ ድርጊት ሲፈፀም የሌሎች እስረኞች መታዘባቸውን የሚናገረው ታሪኩ፤ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ በቢሮ ውስጥ ተመስገንን ባገኘነው ወቅት የግራ አይኑ ስር አብጦ፣ የለበሰው ቲ-ሸርት ተቀዶ ነበር” ብሏል፡፡
በተመስገን ላይ የተፈፀመውን ድብደባ ለማጣራና ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተል አንድ የምርመራ ባልደረባውን ወደ ፖሊስ ጣቢያው ልኮ እንደነበር ያመለከተው ኢሰመጉ፤ ነገር ግን ስለሁኔታው በቂ መረጃ ከተደበዳቢው ጋዜጠኛ እንዳያገኝ ፖሊሶች ክልከላ ማድረጋቸውን አስታውቋል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ለኢሠመጉ ባልደረባ “ችግር ደርሶብኛል” ብሎ ዝርዝር ሁኔታውን  መናገር ሲጀምር ፖሊሶች በሃይል አቋርጠውት ወደ እስር ክፍሉ  እንደመለሱት አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ወደ ፖሊስ ጣቢያው ተልከው የነበሩት የኢሠመጉ ባልደረባ አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ የድብደባ ሁኔታ ኢሰመጉ በጥብቅና በትኩረት እንደሚከታተለው ተጨማሪ ማጣራትም እንደሚያደርግ የጠቆሙት የተቋሙ ባልደረባ፤ በእስረኛው ላይ  ከህግ አግባብ ውጪ ድብደባ የፈፀሙ የፀጥታ ሃይሎችም በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልፀዋል።
በጋዜጠኛው ላይ ከተፈፀመው ድብደባ  በኋላ ህክምና አግኝቶ እንደሆነ ከአዲስ አድማስ የተጠየቀው ታሪኩ ደሳለኝ፤ አይኑ ላይ በግልፅ የሚታይ የድብደባ ምልክት መኖሩንና ህክምናም እንዳላገኘ ተናግሯል፡፡

Read 1154 times