Sunday, 29 May 2022 00:00

ግብጽ 356 ሰዎችን በሞት በመቅጣት ከአለም 1ኛ ሆናለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    በመላው አለም በአመቱ 579 ሰዎች የሞት ፍርድ ተፈጻሚ ሆኖባቸዋል



            ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 ብቻ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 18 አገራት ውስጥ በ579 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ቅጣት ተፈጻሚ እንደሆነባቸውና፣ 356 ሰዎችን በሞት የቀጣችው ግብጽ ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን መያዟን ሰሞኑን የወጣ አንድ አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በ2021 የሞት ፍርድ የተጣለባቸው ሰዎች ቁጥር ካለፈው አመት በ20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና በአመቱ በሞት ቅጣት ከተገደሉት 579 ሰዎች መካከል 24ቱ ሴቶች መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ምንም እንኳን በርካታ ሰዎችን በሞት ቅጣት በመግደል ከአለማችን ቀዳሚዋ አገር ቻይና ብትሆንም፣ የአገሪቱ መንግስት መረጃ ለመስጠት ባለመፍቀዱ አገሪቱ በሪፖርቱ ውስጥ አለመካተቷንና በቻይና በአመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ብሎ እንደሚያምን ተቋሙ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
መረጃ ከሰጡ አገራት መካከል በሞት ፍርድ ግድያ ቀዳሚነቱን የያዘችው የአለማችን አገር ግብጽ ስትሆን፣ በአገሪቱ በአመቱ ቢያንስ 356 ሰዎች የሞት ፍርድ እንደተጣለባቸው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ኢራን 314 ሰዎችን፣ ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ 65 ሰዎችን በሞት ፍርድ በመግደል 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸውንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
እስከ 2021 መጨረሻ ድረስ በመላው አለም ከ28 ሺህ 670 በላይ ሰዎች የሞት ፍርድ እንደተጣለባቸው የገለጸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሞት ፍርድ ከተላለፉባቸው አገራት መካከል ኢራቅ ከ8 ሺህ በላይ፣ ፓኪስታን ከ3 ሺህ 800 በላይ፣ ናይጀሪያ ከ3 ሺህ 3 ሰዎች በላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ እንደያዙም አመልክቷል፡፡
በአመቱ የሞት ፍርድ ተፈጻሚ ከሆነባቸው ሰዎች መካከል አራቱ የተከሰሱበትን ወንጀል የፈጸሙት ከ18 አመት በታች እድሜ እያላቸው መሆኑን የገለጸው ሪፖርቱ፣ 134 የሚሆኑ ሰዎች የተገደሉት ከአደንዛዥ ዕጽ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ተከስሰው መሆኑንም አመልክቷል፡፡
እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ከአለማችን አገራት መካከል 144 ያህሉ የሞት ፍርድን ማስቀረታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ 55 አገራት በበኩላቸው አሁንም የሞት ፍርድን ተፈጻሚ እንደሚያደርጉም የገለጸ ሲሆን፤ በአመቱ የሞት ፍርድን እንደ አዲስ ተፈጻሚ ማድረግ የጀመሩ የአለማችን አገራት ቤላሩስ፣ ጃፓንና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡







Read 3204 times