Saturday, 28 May 2022 13:48

“መንጌ” ሊመጡ ነው እንዴ?

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(0 votes)

   ባለፈው ሳምንት የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ባልዋሉበት ሰፈር ስማቸው ሲነሳ ነበር። እርግጥ ዋነኛው ዜና በሩዋንዳ ዘር ፍጅት አስተባባሪነት ይፈለግ የነበረው የፕሬዚዳንቱ ዘብ ኃላፊ ፕሮታይስ ምፒራንያ፣ ዚምባብዌ ውስጥ ሞቶ ከተቀበረ ከ15 ዓመታት በኋላ እዛ ይኖር እንደነበረ መታወቁ ነው። ሀገሪቱ የወንጀለኞች መናኸሪያ ሆናለች የሚል ትችት ሲሰነዘር የመንግሥቱ ስምም በግርጌ ማስታወሻነት ተነስቷል። በጉዳዩ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ መግለጫ የሰጡት የዚምባብዌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሬድሪክ ሻቫ፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ የዚምባብዌን መንግሥት ከጠየቀ ጥያቄውን ተከትሎ መንግሥት አስፈላጊውን ርምጃ ይወስዳል” የሚል ጥንቃቄ የበዛበት መልስ ሰጥተዋል።
መንግሥት እንኳን ተላልፈው እንዲሰጡት ሊጠይቅ ቀርቶ አንድ ቀን ተነስተው ቦሌ ከች ቢሉ ፈተና ነው የሚሆኑበት። በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው የቀድሞ መሪ አሁን ቢመለሱ፣ ምናልባት ጥፋተኛ አይደለሁም ብለው እንደ አዲስ ይከላከሉ ይሆናል። ያ ስንት አመት እንደሚወስድ አይታወቅም። ያለፈው ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ለመስጠት ከአስር ዓመት በላይ ፈጅቶበታል። ያውም የሰውም ሆነ የሰነድ ማስረጃ ባልጠፋበት። አሁን ከተጎጂ ቤተሰቦች በስተቀር ለምስክርነት የሚቆጠር ማግኘት ቀላል አይሆንም። የጊዜው መራቅና የፖለቲካው ምስቅልቅል ተጨምሮ መንግሥቱን ችሎት ማቆም ራስ ምታት ነው የሚሆነው። ለድጋፍም የሚወጡላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች አይጠፉም።
በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች በመንግሥቱ ኃይለማርያም ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ትዕዛዝ ህይወታቸውን አጥተዋል። ሰሞኑን በቅርበት ከሳቸው ጋር ሲሰሩ የነበሩት የቀድሞ ባለሥልጣን ፋሲካ ሲደልል ከደረጀ ኃይሌ ጋር ካደረጉት ቃለምልልስ እንደሰማነው፤ “ጓድ ሊቀመንበር”፣ ግማሽ ሚሊየን ዶላር ያህል ዘግነው ሳይወጡ አልቀረም። በተረፈ ግን ከሕወሓት በኋላ ያለችው ኢትዮጵያ የመንግሥቱን ወንጀሎች ለማስታወስ ጊዜ ያላት አትመስልም።
የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አይነት እጣ የደረሳቸው አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች መጨረሻ ምን ይመስላል? ጥቂቶችን እንመልከት።
ሂሴን ሃብሬ
በ1970ዎቹና 80ዎቹ ቻድን አንቀጥቅጠው የገዙት ሂሴን ሃብሬ በስደት በኖሩባት ሴኔጋል ችግር ሆነው ነው የከረሙት። ሴኔጋል በሳቸው ምክንያት ፍርድ ቤቶቿ ሌላ ሀገር የተፈፀመን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማየት የሚችሉበትን ሕግ ብታወጣም ሰውየውን ችሎት ለመገተር ገንዘብ ቸግሯት ነበር። በዚህም የተነሳ ተመሳሳይ ሕግ ባላቸው ሀገሮች እንዲዳኙ በተለይም ለቤልጂየም ተላልፈው እንዲሰጡ ጥረቶች ተደርገዋል። በኋላ ግን በአንዳንድ ድርጅቶችና መንግሥታት በተገኘ ድጋፍ ለሕግ ቀርበዋል። ሀብሬ ፍርድ ቤቱን እየረበሹ ሲያስቸግሩ ተጎትተው እየወጡ፣ አንዳንዴ ጉዳያቸው በሌሉበት እየታየ በመጨረሻ እድሜ ይፍታህ ተፈርዶባቸዋል። ለአምስት አመት ያህል በእስር ከቆዩ በኋላ አምና የኮሮና ሰለባ ሆነው በ79 ዓመታቸው በሞት ተለይተዋል።
ዣን ቤደል ቦካሳ
ቦካሳ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ መሪ ነበሩ። እንደውም መሪነቱ አንሷቸው ራሳቸውን በንጉስነት ሾመዋል - ዓፄነቱ ዕውቅና ባይሰጠውም። በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ይዘው ሌላው ፈንቃይ እስኪፈነቅላቸው ለ13 ዓመታት ሀገሪቱን መርተዋል። ቦካሳ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን ከማስጨፍጨፍ ጀምሮ የተቀናቃኞቻቸውን አካል ለገበታ እስከማቅረብ በሚደርሱ ወንጀሎች ተከስሰው በሌሉበት ሞት ተፈርዶባቸው ነበር። የኮትዲቯርና ፈረንሳይ የስደት ኑሮ ሰልችቷቸው ሰተት ብለው ሀገራቸው ሲገቡ፣ ተይዘው ለፍርድ ቀርበዋል። ቦካሳ ‘ጥፋተኛ አይደለሁም’ ብለው ቢከራከሩም በመጨረሻ እድሜ ልክ ተፈርዶባቸዋል። ሰባት አመት ከታሰሩ በኋላ በምህረት ተለቅቀው በ75 ዓመታቸው እስካለፉበት ጊዜ ድረስ ተራ ዜጋ ሆነው ሕይወታቸውን መርተዋል።
ቻርልስ ቴይለር
የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛትነት ከወጡ አርባና አምሳ አመታት በኋላም ተጠርጣሪዎችን በሕግ መዳኘት ቅንጦት የሆነበት ሁኔታ ቢኖር የቻርልስ ቴይለር ጉዳይ አንዱ ነው። በ1980ዎቹ ዓመታት በላይቤሪያና ሴራሊዮን ለማየትም ሆነ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ወንጀሎች ተፈፅመዋል። በሴራሊዮን በባላንጣነት መጠርጠር ቅጣቱ አካል መቆራረጥንም ይጨምራል። በርካታ ዜጎች መዳፍ አልባ ሆነዋል። ይህ ቅጣት ታስቦበት የሚፈፀም ነበር። በአጎራባቿ  ላይቤሪያ ክላሺንኮቭ የታጠቁ፥ በዕፅ የደነዘዙ ሕፃናት ሀገሪቱን እንዳሻቸው እየተረተሩ ይሰፉ ነበር። መሪዎቻቸው ግን የሚያደርጉትን የሚያውቁ፥ የተማሩ፥ ሀገሪቱንም በሚኒስትርነትም ጭምር ያገለገሉ እንደ ቻርልስ ቴይለር አይነቶች ነበሩ።
ቴይለርን ተረኛው የጦር አበጋዝ ሲያባርራቸው ላይቤሪያ ጉልበቷ ሁሉ ዝሎ ለመቆም የምትውተረተርበት ወቅት ነበር። እንደዛም ሆኖ ተሸሽገው ይኖሩበት ከነበረው ናይጄሪያ ተላልፈው እንዲሰጧት ብትጠይቅም ሰውየው የተላኩት ግን ሆላንድ ውስጥ ላስቻለው የሴራሊዮን ጉዳይ ልዩ ፍርድ ቤት ነው። ቴይለር የተከሰሱት ሀገራቸው ውስጥ ለፈፀሙት ወንጀል ሳይሆን በሴራሊዮን የተፈፀሙ ሰቆቃዎችን አግዘዋል በሚል ነው። ፍርድ ቤቱም አምሳ ዓመት አከናንቧቸዋል። እዛ ቅጣታቸውን ለመፈፀም አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጠርላቸው መናገር ይቻላል።
ሚልተን ኦቦቴ
የዩጋንዳ መሪ የነበሩት ሚልተን ኦቦቴ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም ከነበሩት መሪዎች አንዱ በመሆናቸው ብዙ ጊዜ ከመስራቾቹ ጋር ፎቶ ላይ ያታያሉ። የሳቸውን አመራር ለየት የሚያደርገው ሁለት ጊዜ መገልበጣቸው ነው።
አንዴ እንኳን ያባት ነው። ሁለቴ ግን እርግማን መሆን አለበት። መጀመሪያ በኢዲ አሚን ቀጥሎ ደግሞ በአሁኖቹ የዩጋንዳ አመራሮች። ዩጋንዳን በመሩባቸው አመታት የባጋንዳዎችን ንጉስ ሙቴሳን ከማሳደድ ጀምሮ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማድረስ ይወነጀላሉ።  ከሥልጣን ለመጨረሻ ጊዜ ከተባረሩ በኋላ በስደት ዛምቢያ ኖረዋል። ባረፉበት ወቅት ግን ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በብሔራዊ ደረጃ ሽኝት አድርገውላቸዋል።
የኮሎኔል መንግሥቱ መጨረሻ ሲፃፍ ለየትኛው ይቀርብ ይሆን?

Read 3815 times