Saturday, 28 May 2022 13:46

የ446 ኢንዱስትሪዎች መዘጋትና ዳፋው

Written by  ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ
Rate this item
(0 votes)

  "መንግስት ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ሰላምን በመላ ሀገሪቱ ለማስፈን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡ በአንጻሩም የሰሜኑን ጦርነት በምን መልክ ሊቀጭ እንደሚችል መላ ዘይዶ በማርያም መንገድ ካልሾለከ በስተቀር፣ አድሮ በሚያገረሽ ጦርነት፣ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ውሃ የመውቀጥ ያህል መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡--"
         
            እየሆነ ያለውን ነገር እንኳንስ ተንትኖ ለመረዳት ይቅርና በወጉ ሰምቶ ለማለፍም የተረጋጋ ህሊና አልተገኘም፡፡ ግጭት--ውክቢያ---ትርምስ---ጋጋታ---ሁካታ----የእለት ቀለባችን ሆኗል፡፡ ነግቶ ምን እሰማ ይሆን ባይ ሁላ ጀሮውን እደጅ እያሳደረ፣ የሌሊቱን ርዝመት ለማጋመስ፣ የእግር ኳስ ቀጥታ ስርጭት ላይ ተጥዶ ያድራል። የሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ ተስፋ መሆኑ ጠቀመ እንጂ እየሆነ ባለው ነገራችን ነገን ለማየት መናፈቃችን በራስ ላይ እንደ ማፌዝ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለ አንዳንዱ ጉዳይ ሰምተን ባላየ ያለፍነው፣ አይተን የዘለልነው ብዙ ሆኖ ሳለ፣ እያደር አዳዲስ ግርምትን የሚያጭሩ ዜናዎች እንደ ክረምት ውሽንፍር ሲዘንቡብን እያየን ነው፡፡
ለጽሁፌ መነሻ የሆነኝን መረጃ እንኳንስ የሰማሁት ቀን ቀርቶ ዛሬም እንኳ ሳስበው እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ ለሚለው ጥያቄዬ ሁነኛ መላምት ባጣ ነው ወደ አደባባይ ያመጣሁት፡፡ ለወሬ አጀንዳነት የማይቀርቡ ጉዳዮች ማህበራዊ ሚዲያውን በሚያጥለቀልቁበት ዘመን፣ ይህ ግዙፍ አጀንዳ እንዴት ዝም እንደተባለ እንጃ! ተስፋ ቆርጠን ይሁን ወይስ የሚጠበቅ ነው ብለን ይሆን? የኢንዱስትሪ ሚኒስትር የሆኑት አቶ መላኩ አለበል በሚዲያ ቀርበው ከ446 በላይ ኢንዱስትሪዎች በመላ ሀገሪቱ አገልግሎት እንዳቆሙ ሲነግሩን እንዴት አይግረምኝ ጃል?! ለዚህ ዜና አደባባይ መውጣት “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚል ንቅናቄ መጀመሩን አስመልከቶ በተሰጠ መግለጫ ላይ የሰማነው አፍዝ የሆነ መረጃ ነው፡፡


ጎበዝ! ነገሩ እንዴት ነው? 446 ኢንዱስትሪ አገልግሎት አቆመ ማለት እንደ ተራ ወሬ ሲነገረን ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና መፃኢ እድል ፈንታ ማሰብ እንዴት ቸገረን? ነው ወይስ እሱ የከፈተውን ጉሮሮ እሱ ሳይዘጋው አያድርም ብለን ተማምነን ይሆን? እውር አሞራ የሚቀልብ እኛን አይረሳንም ብንልስ የጠዋት ዳቦ ካላገኘን ምን ይጠቅመናል? እየመጣብን ያለውን ናዳ እንዴት ችላ አልነው? የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶላቸው ወደ ትግበራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች፣ የትርፋማነት ጥያቄ ሳይነሳባቸው በአንድ ጊዜ ከ446 በላይ የሆኑት ማምረቻዎች በሰረገላ ቁልፍ ሲከረቸሙ አይተን እንዳላየን ያለፍነው ሳንረዳው ቀርተን ነው ወይንስ ምን አገባኝ ተጣብቶን ይሆን?


የአንድ ኢንዱስትሪ መዘጋት ዳፋው ለባለቤቱ መሆኑ ሃቅ ቢሆንም ከፋም ለማም ባለቤቶቹ የእለት እንጀራ የሚያስጨንቃቸው ሰዎች ወይም ድርጅቶች አይደሉም፡፡ እነርሱማ ይሄኔ የስንት አክስዮን ባለድርሻ ናቸው፡፡ ጉዳዩ የተዳፋነ ረመጥ ሆኖ እያደር ሥጋውን ለብልቦ አጥንቱን የሚጨርሰው ሌላውን ህዝብ ነው፡፡ ምስኪኑን ህዝብ!
ከምርት ትስስር አንጻር አንድ ኢንዱስትሪ ሲዘጋ ለኢንዱስትሪው የጥሬ እቃ ግብአት የሚያቀርቡ እጅግ በርካታ ወገኖች ከጨዋታው ውጭ ይሆናሉ፡፡ እነዚህ አካላት የሚያመርቱት ግብአት ተቀባይ ካጣ የንግድ ፈቃዳቸውን መልሰው ወደ ሌላ ዘርፍ ሲሄዱ ሊፈጥር የሚችለው ክስረት በካልኩሌተር ብቻ የምናወራርደው አሀዝ አይሆንም፡፡ ጥሬ እቃ አቅራቢዎች፣ ሰራተኛ ቀጥረው ግብር ከፍለው ያመረቱት ምርት ውሃ ሲበላው የስንት ሰዎች ህልም እንደ ሰም እንደሚቀልጥ ለመረዳት የጉዳዩ ባለቤት መሆን አያስፈልግም፡፡


በየትኛውም የማምረትና የመነገድ ስርዓት ውስጥ ድልድይ ሆነው ምርቶችን ከአምራች በመቀበል ለሸማቾች የሚያቀብሉ ህጋዊ አቀባባዮች መኖራቸው የጤነኛ ንግድ ስርዓት አንዱ አካል መሆኑ አሌ አይባልም። ኢንዱስትሪዎች ሲዘጉ እንጀራ ገመዳቸው ከሚበጠስባቸው አካላት መካከል የአከፋፋዮች ድርሻ የዝሆን ያህል ጎልቶ ይታያል፡፡ እነዚህ አከፋፋዮች፤ ሻጭና ገዢን፣ አምራችና ተጠቃሚን በአጭር የንግድ ሰንሰለት አገናኝ ሆነው የእለት ኢኮኖሚው ጤናማነቱን ጠብቆ እንዲጓዝና የምርት ክምችትም ብክነትም እንዳይፈጠር እንደ አቀጣጣይ ነዳጅ ሆነው ያንቀሳቅሳሉ፡፡ 446 ኢንዱስትሪዎች ሲዘጉ ስንት አከፋፋዮች አብረው እንደተዘጉ ግልጽ መረጃ ባይቀርብልንም፣ በኢኮኖሚክስ 101 አተያይ፣ ነገሩን መረዳት ሙዝ የመላጥ ያህል ቀሊል ነው፡፡
እኔ እበላ ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ እንደሚባለው ሁሉ፣ ሀገሪቱ እንደ ብራና ቆዳ በብዙ ውጥንቅጦች፣ አታካራዎችና ግጭቶች መሀል ተሰንቅራ፣ ሊሰጥም ሲል ተጨንቆ በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጭ መሀል ሆኖ አድነኝ እንዳለው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ሀገር አድኑኝ በምትልበት ዘመን፣ ጭራሽ የኢንዱስትሪ መዘጋት ዜና ታላቅ መርዶ ሆኖ መከሰቱ ቀጣይ የቤት ስራችን ባለ ብዙ ገጽ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ሃቁን እንዋጠው! ኢንዱስትሪ ሲዘጋ ቀጥታ በነበልባሉ ወላፈን የሚቃጠለው ሸማቹ ማኅበረሰብ ነው፡፡ አስቡት! ምርት ኖሮ እንኳን የእለት ጉርሱን ለመሸፈን የምግብ ሰዓት እየዘለለ የሚበላ፣ የመግዛት አቅም አጥቶ እየደኸየ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮውን ለመሸፈን ተራራ የሚቧጥጠው ህዝብ እንዴት ባለ ስቃይ ሊኖር እንደሚችል ገምቱት፡፡


ይህም ሆኖ ችግሩ በቀለለ ጥሩ ነበር፡፡ በ446 ኢንዱስትሪዎች ተቀጥረው ለእለት እንጀራ የሚለፉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቀጣሪዎችስ እድል ፈንታቸው እንዴት ያለ መራራ ጽዋ መጠጣት እንደሆነ ለማወቅ ጥናት ማድረግ አይጠበቅብንም። በአንድ ተቀጣሪ ዙሪያ ያለውን ቤተሰብ በቀሊል አሀዝ ብናስበው እንኳ ይህ ሁሉ ሰው ምን በልቶ ይውላል? ወላጅ ቤተሰቡን በምን ያስተዳድራል? ለሚሉ ጥያቄዎች ሁነኛ መልስ የሚሰጥ አካል ማግኘት ይከብዳል፡፡
ነገሩ እያሳሳቀ እንደሚወስድ ደራሽ ውሃ ነው። ዛሬ ኢንዱስትሪ ምርት አቆመ ብለን ስንናገር ለአፋችን ቢቀልም እነዚህን ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ለማስገባት ስንት ቢሊዮን ብር አፍሰስን እንዳስጀመርነው ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ምን ይሄ ብቻ? ነገ በለስ ቀንቶን ኢንዱስትሪዎቹን ወደ ምርት እናስገባ ብንልስ መቼ እንዲህ ይቀለናል? ገና ሌላ ቢሊዮን ብር አናታችን ላይ ይጨፍራል።  የኢንዱስትሪዎች መዘጋት የአንድ ድርጅት የግቢ በር መዘጋት ጉዳይ አይደለም፡፡ ከማምረቻው ግቢ ውስጥ ያለው ተቋማዊ ተግዳሮትና ከግቢው ውጭ ያለው ፈተና አንገት ድረስ የሚተናነቅ ነው። ከውስጥ ያለውን እንየው ካልን ምርት ሲቀንስ በአመራሩና በሰራተኛው መካከል ሊኖር የሚገባው ጤናማ ግንኙነት ላይ ክፉ ግርዶሽ ይጥላል፡፡ ሰራተኛውም በስራው እርካታ ያጣል፡፡ ይህም ሳያንስ ድርጅቱ ከተዘጋ በስራ ላይ ተሰማርቶ ይውል የነበረው ኃይል ወደ ስራ ፈትነት ብሎም ወደ ወንጀል ተባባሪነት የመቀየር እድሉ ሰፊ ነው። ውጫዊውን ስንመለከት ለወትሮውም የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ እንደ ኤሊ የሚንቀረፈፈው ኢኮኖሚያችን፣ ዛሬ ላይ ይህን መርዶ ሲሰማ አዲስ ኢንቬስተር ከሀገር ውስጥ ለማፍራትም ሆነ ከውጭ ለማምጣት ምን ያህል ዳገት እንደሚቧጥጥ መረዳት አያቅተንም፡፡
የአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት በራስ አቅም ማምረት መቻል ነው፡፡ ይህ አቅም ከተገነባ ለኤክስፖርት፣ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ፣ ለተፎካካሪነትና ለውጭ ምንዛሪ እድል መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ በዚያ ልክም ኢንዱስትሪ ሲዘጋ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለውጭ ገበያ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የእጅ አዙር ተገዢነት በምርኮ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ በተለይ እንደ እኛ ባለ የደሀ ኢኮኖሚ ኢንዱስትሪ እየዘጋን የውጭ ምርትን ብቻ ወደማስገባት ከተሻገርን  ምጽአቱን ያለ መላእክት አዋጅ ወደ ራሳችን የማቅረብ ያህል አስጊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡


ከላይ እንዳነሳሁት ሸማቹ ማህበረሰብ ተለዋጭ ምርቶችን ከራሱ ገቢ፣ ከምርቱ ጥራትና ከፍላጎቱ አንጻር አማርጦ እየመዘነ መግዛት ሲችል፣ አንዱ ምርት ላይ የናረ ዋጋ ሲያጋጥመው አሊያም የጥራት ጉድለት ሲያይበት ምርጫውን ወደ ተመሳሳይ ምርት ማዞሩ የሚታወቅ ነው። ይህ አንድ ሃቅ ሆኖ ሳለ  ኢንዱስትሪው ሲዘጋ ግን ሸማቹ ሌላ ተለዋጭ ምርት ሊያገኝ የሚችልበት እድል ሲጠፋ ለአንድ ምርት ተጋላጭነት ይጋለጣል። ይህ ደግም አምራቹ በሚወስነው የዋጋ ተመን ጥገኛ እንዲሆን ያስገድደዋል፡፡
ሚኒስትር መስርያ ቤቱ ለኢንዱስትሪዎቹ መዘጋት ምክንያት ናቸው ብሎ ያስቀመጣቸው  የግብዓት፣ የፋይናንስ፣ የመሰረተ ልማት፣ ብቁ የሰው ኃይል እጥረትና የተቀናጀ የመንግሥት ድጋፍ አለመኖር እንዳለ ሆኖ በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠረው ጦርነት ብዙ መከራ ውስጥ የከተተን ቢሆንም፣ ዛሬም አለመጠናቀቁ ደግሞ ላልተዘጉትም ኢንዱስትሪዎች የመዘጋት ዋዜማ እንዳይሆንባቸው አበክሮ መገንዘቡ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
የፀሐይን በምስራቅ መውጣትና በምዕራብ መግባት ላይ ለመከራከር እንደማንሞክር ሁሉ በሀገሪቱ ውስጥ በብሔር በሃይማኖትና በመሳሰሉ ጉዳዮች የሚነሱት ድንገተኛ ግድያዎችና መፈናቀሎች፣ ማህበረሰቡን ወደ ስጋት በመክተቱ ኢንዱስትሪዎቹ ትንፋሽ እንዳይኖራቸው ማድረጉንም መዝለል፣ ለችግሩ ሌላ ችግር መደረብ ይሆንብናል። ሰላም በሌለበት ሁኔታ የትኛውም ኢንዱስትሪ እድሜ ሊኖረው አይችልም። ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ምኅዳሩ ጤናማ አየር ከሌለው፣ ምርታማነትን ማለም ላም አለኝ በሰማይ ያስብላል፡፡ ስለዚህ ሁለንተናዊ ጸጥታችን የምርት ቅብብልና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳርፎአል፡፡
ሌላው ከአጉዋ መውጣታችን የኢንዱስትሪው ምርት ላይ ክፉኛ ጠባሳ እንደጣለ እንዴት መዘንጋት ይቻላል? ምርታችንን በአሜሪካ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ወርቃማ እድል ስንነጠቅ የተመረተውን ምርት የሚቀበል አካል ጠፍቶ ለተረፈ ምርት ከመጋለጣችን በላይ ውሎ አድሮ ለኢንዱስትሪዎች መዘጋት የራሱን የጠጠር ሚዛን እንደጣለ ማውሳት ይገባናል፡፡ የዚህ የጋርዮሽ ውል ምርታችንን በዓለም ገበያ ማቅረብ መቻላችን ብቻ ሳይሆን ከሽያጩም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምናገኝበት ዕድል እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ እድል ሲዘጋ መልካም አጋጣሚዎቹ አብረው ይዘጋሉ፡፡
እንደኛ ላለ ሀገር የኢንዱስትሪዎች መዘጋት እንደ ተራ ዜና የሚነገር አይደለም። ምክንያቱም ኢንዱስትሪዎቹን ዘግተን በበሬ ትከሻ ጥገኛ በሆነው ኢኮኖሚያችን ላይ እየሸለልን መኖር አንችልም፡፡ ወደድንም ጠላንም የውጭ ምንዛሬ ያስፈልገናል። የውጭ ምንዛሬ ምንጩ ደግሞ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኢንዱስትሪ ምርት ለገበያ ማቅረብ ነው፡፡


ነገሩን አስፍተን ካየነው በየዓመቱ ከዩኒቨርስቲዎች የሚመረቀው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዜጋ መብላት መጠጣት፣ የራሱን ቤት መቀለስ መፈለጉ አይቀሬ ነው። ይህን ኃይል ቦታ ቦታ እያስያዝን ፋታ መውሰድ የምንችለው ደግሞ ኢንዱስትሪዎችን በመዝጋት ሳይሆን በመክፈት መሆኑ ሃቅ ነው፡፡ ወጣቱ ኃይል ስራ ሲይዝ ደመወዝ መቀበል ብቻ ሳይሆን ለአዲስ ፈጠራ እሳቤና የተረጋጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሌላ ጉልበት ይፈጥርልናል፡፡ በተቃራኒው ይህ ወጣት ውሎ አድሮ ስራ ካላገኘ አእምሮው ወደ ክፉ እሳቤ መለወጡ የተፈጥሮ ሃቅ ነው፡፡
ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡ የኢንዱስትሪዎቹ መዘጋት ዘርፈ ብዙ ጉዳት ማስከተሉ እንዳለ ሆኖ መንግስት በቅርቡ የነዳጅ ዋጋ ድጎማ ማቆሙ የሀገሪቱ ንግድና የምርት ዝውውር ላይ ሌላ ፈተና ይዞ መጥቷል። የነዳጅ ጭማሪ በተደረገ ማግስት በትንሹ ከአንድ ብር ጀምሮ በሸቀጥ ላይ ጭማሪ ተደርጎ ጠያቂ አጥቷል፡፡ መከረኛው ሸማች ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጫና ተፈጥሮበት እዳ ከፋይ ሆኗል፡፡ መንግስት የሸቀጥ ዋጋን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማረጋጋት ከሸቀጦች ታክስ ይገኝ የነበረ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ እንዳይሰበሰብ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ የእሁድ ገበያን ዘርግቶ ምርት ለማከፋፈል ባደረገው ጥረት እንደ ቀልድ የማይታይ ውጤት እንዳስመዘገበ ራሳችን ምስክሮች ነን፡፡ ይህ ማለት ግን ዛሬም የመንግስትን ትከሻ የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የዘይት፣ የማዳበርያ የኮንስትራክሽን እቃዎች፣ የትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የጭቅጭቅ አጀንዳዎች እየተፈራረቁ ሲያከራክሩ እያየን ነው፡፡


በሌላ በኩል፤ ይህን ወቅት መሶብ ውስጥ ካለው እንጀራችን ጋር ብቻ እየመዘንን ከሰፈርነው ለስሁት ድምዳሜ ይዳርገናል። ጉዳዩ ዓለም አቀፋዊ ነው። በዜና ስናዳምጠው የነበረው የራሺያና ዩክሬን ጦርነት ኢኮኖሚያችንን መንካቱ አይቀሬ ነው። ይህ ቀን እንደ ሠርግና ምላሽ ይጠብቁ የነበሩ ጥቂት የማይባሉ የገዛ ሀገራችን ነጋዴዎች፣ ምርት በመደበቅና የተጋነነ ዋጋ በመጨመር የኑሮ ውድነቱ ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ እንደማይመለሱ የቀድሞ ልማዳችን ይነግርናል። በአናቱም ሲጸነስም ሲወለድም፣ ሲያረጅም ሲሞትም የጦርነት ልክፍት የተጠናወተው ህወሓት፣ ዛሬም አረ ጎራው እያለ ምርታማነታችን ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው፡፡ ነገሮቹን ስንደማምር የኢንዱስትሪዎቻችን መዘጋት ትልቅ ጉዳት ሆኖ፣ እኛም ጎን ለጎን ነገሮችን በሁለንተናዊ ማዕቀፍ እያየን ለመፍትሔው መታገል ተገቢነት ይኖረዋል፡፡
መንግስት ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ከሁሉ አስቀድሞ ሰላምን በመላ ሀገሪቱ ለማስፈን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡ በአንጻሩም የሰሜኑን ጦርነት በምን መልክ ሊቀጭ እንደሚችል መላ ዘይዶ በማርያም መንገድ ካልሾለከ በስተቀር፣ አድሮ በሚያገረሽ ጦርነት፣ ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ውሃ የመውቀጥ ያህል መሆኑ አይቀሬ ነው። በጎንም የአጉዋን ስምምነት ወደነበረበት ለመመለስ መጣር ይገባዋል፡፡ በሌላ መልኩ ዲፕሎማሲ ማለት በሰጥቶ መቀበል መርህ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት ሳያስደፍሩ መኖር ነውና በተለያዩ አጋጣሚዎችና ክስተቶች ከተለያዩ ሀገራት ጋር የገባንበትን መቃቃር በእልህ ከመፍታት ይልቅ በብልህነት፣ በሆደ-ሰፊነትና በታጋሽነት መፍታት ትልቁ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ በርግጥ ይህ እርምጃ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ ግቡ የሀገር ውስጥ ምርታችንን ወደ ውጭ መላክና ምንዛሪ በማግኘት አንድም ለኢንዱስትሪያችን አቅም መፍጠር ሲሆን በሌላ በኩል ዲፕሎማሲያችንን ወደ ተሻለ ምእራፍ ማሻገር ይሆናል፡፡ ሻሎም!

Read 1283 times