Print this page
Tuesday, 24 May 2022 07:10

በምልክት ብቻ፣ በጣት ውልብታ፣ በትንፋሽ ፍጥነት፣ በልብ ትርታ፣

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 • በጠቅ-ጠቅ ፍጥነት ነው፤ መግዛትና መሸጥ። አየር ባየር ነው፤ መክፈልና ማግኘት፣ መላክና መቀበል (click, click, send & received)
    • በጣት ውልብታ ሆኗል፣ መገናኘትና መሰናበት። በምልክት ብቻ ነው ዳኝነት። “ጓደኞችን” እንደ ልብ ማብዛት፤ ከእልፍ ሰዎች ጋርም “መጣላት”።
        (like, unlike, thumbs up, thumbs down)
            
             ድሮ ድሮ፣ የንጉሦች ምልክት ነበር - ወደ ሰማይ የተቀሰረ፣ ወይም ወደ ምድር የተደፋ አውራ ጣት። የዋዛ ይመስላል። በእርግጥ፣ ከጣትም፣ አውራ ጣት ነው። ከአውራ ጣትም፣ የንጉሥ አውራ ጣት ነው። ቢሆንም ግን፣ በጣት ውልብታ ብቻ፣ የት ይደረሳል? ወደ ላይ ቢሆን፣ ወደ ታች ቢዞር፣… ምን ይፈጠራል? አዎ፣ ነገሩ ቀላል ይመስላል። ግን፣ ቀላል የጣት ውልብታ፣ የሕይወትና የሞት፣ የፍርጃና የምህረት ልዩነት ታመጣለች።
ዘመኑ፣ ያኔ፣ የሮም ነገሥታት፣ “የአለም ገዢ” የነበሩበት ዘመን ነው፤ የዛሬ 2ሺ ዓመት ገደማ። ከ20 በላይ አገራትን የሚሸፍን ነበር፤ ሰፊው የሮም ግዛት። የፍልሚያ ትዕይንት፣ በሮም ምድር እጅግ የገነነውም በዚያ ዘመን ነው።
በጦርና በጎራዴ፣ በመጥረቢያና በመዶሻ የሚካሄድ የፍልሚያ ትዕይንት፤ ለሮም ከተማ፣ ትልቅ ክብረ በዓል ነበር። ንጉሡና ትልልቅ ባለስልጣናት፣ ከተራ ተርታው ዜጋ ጋር፣ እኩል ይታደሙበታል።
በተለይ፣ ለተራው የሮም ነዋሪ፣ የፍልሚያ ትዕይንት፣ እጅግ ተወዳጅና ተናፋቂ የመዝናኛ ድግስ ነበር። ግን፣ መዝናኛ ብቻ አይደለም። ትልቅ ክብረ በዓልም ነው።
እልፍ አእላፍ ነዋሪዎች፣ በጉጉት ይጠብቁታል። ይጎርፉለታል፣ ያብዱለታል። ግን፣ ነገሥታትም፣ ከትዕይንቱ አይቀሩም። ክብረ በዓል ነው። የሮም ንጉሥ ማለት፣ በዚያ ዘመን፣ የዓለማችን ኀያል ንጉሥ ነው - ብዙ ሚሊዮኖች የሚፈሩትና የሚታዘዙት። ነገር ግን፣ የፍልሚያ ትዕይንትን ችላ ብሎ ለመቅረት የሚደፍር ንጉሥ የለም፤ ጁሌስ ቄሳርም ቢሆን፣ አውጉስቶስ ቄሳርም ቢሆን።
ምናለፋችሁ፣ የፍልሚያ ትዕይንት፣ ለእልፍ አእላፍ ዜጎች፣ ተናፋቂ የመዝናኛ ፌሽታ ነው። ንጉሦች የሚያከብሩት በዓል ነው። እጅግ ተወዳጅ ክብረ በዓል ከመሆኑ የተነሳ፣… ለፍልሚያ ትዕይንት፣ በርካታ ግዙፍ ስታዲዬሞች ተገንብተዋል፤ በሮም እና በሌሎች ከተሞች።
ይታያችሁ፣ በዚያ ዘመን፣ ከ2000 ዓመታት በፊት፣ ግዙፍ ስታዲዬሞችን መገንባት! ከሃያ እስክ ሠላሳ ሺ ተመልካቾችን የሚያስተናገዱ የፍልሚያ ስታዲዬሞች የተገነቡት። ለሮም ግን፣ ይሄ በቂ አልሆነም። ሌላ ተጨመረ። በግዙፍነቱ ምክንያት፣ “Colosseum” ብለው ይጠሩታል። ባለ ሦስት ፎቅ ነው። ወደ ላይ፣ ቁመቱ ከ50 ሜትር ይበልጣል። 50 ሺ ተመልካቾችን ያስተናግዳል።
የፍልሚያ ትዕይንት፣ ምን ያህል የተከበረ በዓል ቢሆን ነው? ተጋጣሚዎች፣ በጦር በጎራዴ የሚገዳደሉበት፣ በመዶሻ በመጥረቢያ የሚከሳከሱበት የፍልሚያ ትዕይንት፣ ምን ያህል ተወዳጅ ቢሆን ነው?
በወርቅ እና በብር ጌጣጌጥ የተዋበ የክብር ቦታ ላይ፣ ንጉሡ፣ ከአማካሪዎቹና ከቤተመንግስት ሰዎች ጋር ይቀመጣል። ግራና ቀኝ፣ ዙሪያው፣ በተመልካቾች ይጥለቀለቃል። ግን፣ ጥላ አለው፤ መቀመጫ ተሟልቶለታል። ዓለም ነው። አርፎ መቀመጥ ግን የለም።
የፍልሚያ ትዕይንት፣ ያቁነጠንጣል። እረፍት አይሰጥም። ገና ፍልሚያው ሳይጀመር፣ ቁጭ ብድግ ያስብላል። የሮም ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ስታዲየሙን በሆታ ያደምቁታል። ማን ማንን ገድሎ እንደሚያሸንፍ ይወራረዳሉ፤ ቁማር ይጫወታሉ። ሜዳ ውስጥ የሚካሄደው ትዕይንት ግን፣ ጨዋታ አይደለም። የሞት ሽረት ፍልሚያ ነው።
አንዳንዴ ከአውሬዎች ጋር ነው ትግሉ፤ ከአንበሳ ከነብር ጋር። አውራሪስም ተወዳጅ ነው። ዋናው ትዕይንት ግን፤ የኀይለኛ ጦረኞች ፍልሚያ ነው። በመዶሻም ይሁን በጎራዴ፣ እስከ መጨረሻዋ የደም ጠብታ ነው፤ “ጨዋታው”። ተወግቶ ደምቶ፤ ተሰብሮ ተፈጥፍጦ፣ እዚያው በወደቀበት መቅረት የለም። “ማሸነፍ ወይም ሞት” ነው ፉክክሩ። ተዘርሮ መቅረት፣ ለሕይወት ፍፃሜ፣ ለመጨረሻዋ ስለት፣ ለመጨረሻዋ የመዶሻ ምት ተመቻችቶ እንደመጠበቅ ነው። በዚያው ያልቅለታል።
አንዳንዴ፣ በሕይወት የመትረፍ እድል ይኖራል። በጀግንት የተዋጋ ተወዳዳሪ፣ እንዳይነሳ ሆኖ ቢወድቅም፣ ከተጋጣሚውና ከተመልካቾች፣ አክብሮትን ሊያትርፍ ይችላል። ምናልባት ነው፣ ታዲያ። ተጋጣሚውን የዘረዘረ ጀግና፣ ተፎካካሪውን ጥሎ፣ ዙሪያውን ይመለከታል። ተመልካቾች በጩኸት ስታዲዬሙን ያናውጡታል። ንጉሡ፤ በክብር ከተቀመጠበት ግርማዊ ወንብር ላይ ሆኖ፣ እጁን ያሳያል። መዳን ጨብጦ አውራ ጣቱን ይዘረጋል።
የንጉሡ አውራ ጣት፣ ወደ ታች ከተደፋ፣ “የድጋፍ፣ የምህረት ምልክት” ነው። የተዘረዘረው ተፋላሚ፣ በግጥሚያ ቢሸነፍም፤ በሕይወት እንዲተርፍ ተፈርዶለታል። ምህረት ተደርጎለታል ማለት ነው። ተወግቶ ተሰብሮ፣ በሕይወት የሚድን ከሆነ፣ እድሉን መሞከር ይችላል።
ንጉሡ፣ አውራ ጣቱን ወደ ላይ ከቀሰረ ግን፣ የሞት ፍርድ ነው። የሕይወት ፍፃሜ ይሆናል። “ግደለው፣ ጨርሰው” እንደ ማለት ስለሆነ፤ አብዛኛው ተመልካች በሆታ ይሰክራል። በቁማር የተሳካላቸው ተመልካቾች፣ ድል አድራጊውን ተፋላሚ ያወድሳሉ። “ጨርሰው፤ ቁረጠው፤ ግደለው” እያሉ ስታዲዬሙን ያናጉታል።
በቁማር የተበሉ ተመልካቾችም፣ ዝም አይሉም። በተዘረረው ተጋጣሚ ይናደዳሉ። ቲፎዞነታቸው ወደ ጥላቻ ይቀየራል። “ይሄ ሙትቻ፣ ግደልው! ይሄ ሬሣ፣ ጨርሰው!” እያሉ፣ በብስጭትና በቁጭት ይጮሃሉ። እጅግ ብዙ አስጸያፊ ስድቦችን ትተን ማለት ነው። አዳሜ ሁሉ፣ እንደ ንጉሡ፣ አውራ ጣቱን ሽቅብ ይቀስራል። የሞት ፍርድን በአድናቆት ያራግባል።
በምልክት ነው፣ የያኔው የስታዲዬም ዳኝነት። ግን፣ ዛሬስ እንደዚያው አይደለም?
የአውራ ጣት ትርጉም ቢቀየርም፣ ወራሾች አግኝቷል።
ዛሬም፣ እንደጥንቱ፣ በምልክት ብቻ መፍረድ ይቻላል (በአውራ ጣት ምልክት)። በእርግጥ፣ ዛሬ የምልክቱ ትርጉም የተገላቢጦሽ ተቀይሯል። ታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት፣ ነገሩ፣ የአተረጓጎም ስህተት ነው። ከሮም ውደቀት ጋር፤ ብዙ የስልጣኔ ጅምሮች፣ በፍጥነት ነበር የከሰሙት። በጊዜው፣ ቶሎ የሚፈርሱ አይመስሉም ነበር። እንደ ጥንታዊዎቹ የግብፅና የግሪክ ግንባታዎች፣ የሮም ሕንፃዎች፣ ዘላለማዊ ነበር የሚመስሉት።
በእርግጥም፣ የሮም ግንባታዎች አስደናቂ የሥልጣኔ ውጤቶች ናቸው፤ አስገራሚ የሥልጣኔ ምልክቶች። ከሮም ውድቀት በኋላ፣ ለ1000 ዓመታት፣ እነዚያን የሚስተካከል ሕንፃ አልተሰራም።
“ብርሃንን አይቶ ወደ ጨለማ እንደ መውረድ ነው” ማለት ይቻላል - የሮም ውድቀት። የማንበብና የመፃፍ ችሎታ እንኳ፣ ብርቅ እስከመሆን ደርሷል። ታዲያ፣ የጥንት የሮም ፅሁፎችን ለማንበብና ለመተርጎም የሚሞክሩ የኋላ ዘመን ሰዎች ቢሳሳቱ፣ ምን ይገርማል?
ወደ ሰማይ የተቀሰረ አውራ ጣት፣ “የይሁንታና የአክብሮት፣ የምህረትና የድጋፍ ምልክት ነው” ተብሎ በስህተት ተተረጎመ። ወደ ታች የተደፋ አውራ ጣት ደግሞ፣ “የአሉታና የቅራኔ፣ የስድብና የውንጀላ፣ የጥላቻና የፍርጃ ምልክት” ሆነ… ይባላል።
ሌሎች የተለወጡ ነገሮችም አሉ። ዛሬ፣ የአውራ ጣት ምልክት፣ የንጉሦች ንብረት አይደለም። የአውራ ጣት የበላይ ጠባቂና ዋና ባለቤት ተቀይሯል። ፌስቡክ ሆኗል - የአውራ ጣት ወራሽ (የሥልጣን አልጋ ወራሽ ባይሆንም)።
የጥንቱ የሞት ሽረት ድግስስ? የፍልሚያ አውድማውና ታዳሚዎቹስ? በየከተማው፣ በስታዲዬም ውስጥ፣ ንጉሦችና እልፍ አእላፍ ሺ ነዋሪዎች፣ አለቆችና ምንዝሮች የሚታደሙት የፍልሚያ ድግስ፣ ድሮ ቀርቷል።
ዛሬ፣ አለማቀፍ ነው፣ ድግሱ። ከቢሊዮን በላይ ናቸው፣ የእለት ተእለት ታዳሚዎቹ። ንጉሦችና መንግስታት፣ ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት መሪዎችና አማፂ ቡድኖች፣… ማን የቀረ አለ? ከዓለማችን ቢሊዮነሮች ጀምሮ፣ እስከ ጎስቋላዎቹ የዓለማችን ቢሊዮን ነዋሪዎች ድረስ፣ ሁሉም ይታደሙበታል - የፌስቡክ፣ የቲዊተር፣… የምናምን ድግስ።
ያልተለወጠ ነገር ቢኖር፣ የሰዎች የምልክት ፍቅር ነው።
እንደ ድሮው ነው ምልክቱ። በአውራ ጣት ነው ዳኝነቱ። የያኔዎቹ ታዳሚዎች፣ አጫጭር መፈክሮችን እየተቀባበሉ፣ ጥቂት ቃላትን እየደጋገሙ፣ ድግሱን በሆይሆይታ ያደምቁታል። ዛሬም፣ ባጭር ባጭሩ ነው፣ ፖስት፣ ሼር፤ ትዊት፣ ሪትዊት።
ይሄ ሁሉ፣ በምልክት ላይ ያነጣጠረ ወቀሳ ይመስላል - የጥንቱንም የዛሬውንም ያዳበለ ነቀፋ። ግን ወቀሳ አይደለም።
በእርግጥ፣ ወቀሳ አልጠፋም። 2000 ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሰው፣ የዘመኑን የፍልሚያ ድግስ የሚያወግዙ ሰዎች አሉ። የያኔ ንጉሦች ላይ፣ ውግዘት የሚያወርዱና ጣታቸውን የሚቀስሩ ሰዎችም ይኖራሉ። “ጨካኝ ንጉሥ፣ ግፈኛ ገዢ፣ እብሪተኛ አምባገነን” ብለው ይወነጅላሉ - በጠቋሚ ጣታቸው እያመለከቱ።
ዛሬ፣ ብዙ ሰዎች፣ የውንጀላ ጣታቸውን የሚያሾሉት፣ በባለስልጣናትና በገዢዎች ላይ ብቻ አይደለም። “የኢኮኖሚ ጌቶች” ላይም ነው፤ ውግዘት የሚያወርዱት። ግዙፎቹን ኩባንያዎች ያወግዛሉ፤ የኩባንያዎቹን መሪዎች ይረግማሉ። “ሕዝበ አዳምን እያንጫጩ፣ የሩቅ የቅርቡን እያወዛገቡ፣ እኛን እያናቆሩ፤ እነሱ ቢሊዮነር ይሆናሉ” እያሉ ያማርራሉ።
ያው፣ አብዛኛው ውንጀላ፣ መስመር የለቀቀ ጭፍን ውንጀላ እንደሚሆን አትጠራጠሩ። ነገር ግን፣ ግዙፎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ “እንከን የለሽ ናቸው” ማለት አይደለም። በተለይ በተለይ፣ “የሰዎችን የግል መረጃ አያከብሩም” ተብለው ቢወቀሱ አይገርምም። የማይሰበስቡት የመረጃ አይነት የለም።
ለሁሉም ነገር፣ ግዙዎቹን ኩባንያዎች በጭፍን መኮነን ግን፣ ሌላ ነገር ነው። ሕዝበ አዳም፣ በየራሱ ምርጫ እያዘጋጀ፣ በየራሱ ፈቃድ የሚያሰራጨው ፅሁፍና ቪዲዮ፣ ጉዳትና መዘዝ ቢያመጣ፣ ኩባንያዎቹን ዋና ተጠያቂ ትክክል ነው? የተወሰነ ያህል ሃላፊነትና ተጠያቂነት ይኖርባቸዋል። የወንጀልና የጥቃት ተባባሪ፣ የጥፋት ዘመቻ አጋፋሪ መሆን የለባቸውም።
እንደ ወላጅ፣ እንደ አሳዳጊ፣ የስነምግባር ተቆጣጣሪ፣ የጨዋነት አስተማሪ እንዲሆኑልን መጠበቅ ግን፣ ትክክል አይሆንም። ወረቀት አምራቾችና የሕትመት ድርጅቶች፤ በወረቀት ታትሞ ለሚወጣ ፅሁፍ ሁሉ ተጠያቂ እንደማድረግ ይመስላል።
የጥንታዊቷ ሮም የፍልሚያ ትርዒት፣ ዘግናኝ ነው። የተመልካቾ፣ ደም የተጠማ ስካር፣… አስቀያሚ ነው። ነገር ግን፣ ስታዲዬም ያስገነቡ ሰዎችን ብንወነጅላቸው፣ አናጺዎች ላይ ብንፈርድባቸው አስቡት። በያኔው የምልክት ቋንቋ፤ አውራ ጣታችንን ብንቀስርባቸው ይታያችሁ።
ጉዳቸው ይፈላ ነበር። “አንገታቸው ለገመድ” ይሆን ነበር። ደግነቱ፣ ዛሬ፣ የምልክቱ ትርጉም ስለተቀየረ፣ አያሳስብም። ወደ ላይ የተቀሰረ አውራ ጣት፣ “ይሰቀሉ፣ ይገደሉ” ማለት አይደለም። ወደ ታች የተደፋ አውራ ጣት ነው፤ የፍርጃ ምልክት (በዛሬ ትርጉሙ)።
እውነትም፣ ያልተቀየረ ነገር ቢኖር፣ የሰዎች የምልክት ፍቅር ነው። “ሙዚቃ ሕይወቴ” ተብሎ እንደተዘፈነው፣ “ምልክት ሕይወቴ” የሚል ዜማ ቢመጣ፣ ዘመን የማይሽረው ተጨማሪ ዘፈን ይሆን ነበር። እንዲያውም፣ “የሰው ምንነቱ፣ በምልክት ማመኑ ነው” ቢባል ስህትት አይደለም። “የሰው ልዕልና የምልክት ባለጸጋ መሆኑ ላይ ነው” ማለት ይችላል።
በእርግጥ፣ “ምልክት” ለብቻው እየገነነ፣ ከእውኑ “ቁምነገር” እየተነጠለ ከእጅ ካመለጠ፣ ርቆ እየፈረጠጠ፣ አየር ባየር፣ በባዶ እየናኘ፣ መከራ ያመጣል። ምልክት፣ የሰው ፀጋ ከመሆን ይልቅ፣ የሰው እዳ ይሆናል። በራስ እጅ የሚመጣ የእርግማን መዓት፣ ወደ ራስ የተቀሰረ የፍርጃ ቅጣት እንደማለት ነው - ባዶ ምልክት።
በሌላ አነጋገር፣ ከቁምነገር ያልተላቀቀ ምልክት፣ እጅግ ክቡር ነው።
የዚያኑ ያህል ደግሞ አደገኛ ነው - በባዶ የተለቀቀ ምልክት።
በጣት ውልብታ፣ “ውጋው፤ ግደለው” እያሉ እንደዘበት በሕይወት ላይ መፍረድ፤ እንደዋዛ አንዱን ማንገሥ አንዱን መገርሰስ፣ አንዱን ወደ ከፍታ ማጽደቅ፣ ሌላውን ወደ መቀመቅ ማውረድ፣ በዘፈቀደ መሸለምና መቅጣት፣ ከአንዱ ቀምቶ ለሌላኛው መስጠት - በቅንጣት ምልክት ብቻ። ሁሉንም ነገር ለማቅለል፣ ለማፋጠን፣ ለማዛመት የሚቻለው በምልክት ነው። አውራ ጣትን በመድፋት ወይም በመቀሰር፤ ወደ ምድር አውርደው ወይም ወደ ሰማይ ስቀለው የሚል ከባድ መልዕክት፤ በቀላል ምልክት። ለዚያውም፣ በጠቅ-ጠቅ ፍጥነት።
ግን፤ ምልክት ላይ አትፍረዱ። ምልክትን አትጥሉ። ያለ ምልክት፣ ሰው መሆን አይቻልም። ያለ ምልክት እንዴት ተብሎ ማወቅና ማሰብ ይቻላል? እንዴትስ በሰዎች መካከል፣ መግባባት፣ መገበያየትና መከባበር ይፈጠራል? በቋንቋ ወይም በሌላ ምልክት እንጂ፣ ሌላ ምን ዘዴ አለ?
ቋንቋ የተባለ ነገር በሙሉ ደግሞ፣ የምልክቶች ቅንብር ነው - የድምጽ፣ የፅሁፍ ወይም የሌላ። ከሀ እስከ ሆ፣ አቡጊዳሄውዞ፣ የፊደሎች ድምፅ ወይም ቅርፅ፣ … ምልክቶች ናቸው። ከእውቀትና ከግንዛቤ ጋር ሲዋሃዱ፣ ትልቅ ፀጋ፣ ብዙ በረከት ይሆናሉ። በባዶ ሽምደዳ ሲሆኑ፣ ዋጋ ያጣሉ። እውነትን የማያመለክቱ፣ የውሸትና የሸፍጥ መሳሪያ ስናደርጋቸው ደግሞ፣ ጥፋትን ያስከትላሉ። እንደ አጠቃቀማችን ናቸው።
ምልክትንና ቁምነገሩን፤ የወረቀት ገንዘብንና ሃብትን ማምታታት።
የወረቀት ገንዘብ፣ የሃብት ምልክት እንደሆነ ምን ይጠየቃል? በእርግጥ፣ ወረቀቱ ራሱ፣ ሃብት አይደለም። ትርጉም የሌለው ቁራጭ ወረቀትም አይደለም። ሃብት ባይሆንም፣ የሃብት ምልክት ነው። ወረቀቱ፣ “ራሱን የቻለ ሃብት” የመሰለን ጊዜ ግን፣ ችግር ይፈጠራል።
የሕትመት ማሽኖችን አስመጥተን፣ በሳምንት ለሰባት ቀናት፣ በየቀኑም ለ24 ሰዓታት፣ የወረቀት ገንዘብ እያተምን፣… አገር ምድሩ በሃብት ሲጥለቀለቅ ይታያችሁ። ሁሉም ሰው እንደልቡ ሃብታም እስኪሆን ድረስ፣ ህትመት ላይ መትጋት! ዋናውን ቁምነገር ረስተን፣ ምልክቱን ብቻ ይዘን እንቀራለን። ተጨማሪ ሃብት ሳንፈጥር፣ ምርታችን ሳይበረክት፣ የወረቀት ገንዘብ በገፍ ከታተመ፣ ክብሩ ይረክሳል። ዋጋው ይወርዳል። የምርቶች ዋጋ ደግሞ ይንራል። ኑሮ ይወደዳል፤ ይናጋል። ኢኮኖሚ ይቃወሳል።
የወረቀት ገንዘብ፣ ትልቅ ክብር የሚኖረው፣ ሃብትንና ምርትን፣ ማለትም “ዋናውን ቁም ነገር” የሚወክል ምልክት ሲሆን ነው። ምልክት መሆኑን የዘነጋን እንደሆነ ግን፣ ዋናውን ቁም ነገር የሚተካ የመሰለን እንደሆነ ግን፣ … ምልክትነቱ ይረክሳል። ኑሮን ያራቁታል፤ ከዋናው ቁምነገር ጋር ያራርቃል።
ፖለቲካና የመንግስት ስልጣን፣ ኢኮኖሚና ሙያ፣ ቢዝነስና ገበያ፣ ፍቅርና ቤተሰብ… ሁሉም የምልክት ደንበኞች ናቸው። ሃይማኖት ደግሞ አለ። የምልክቶች ባለፀጋ ነው- ሃይማኖት። ምልክቶችን በመውቀስም፣ ሃይማኖት ቀዳሚ ነው። “የጣዖት አምልኮ” በማለት ምልክቶችን ያወግዛሉ - የሃይማኖት ሰዎች።
ሃይማኖትና የሃይማኖት ምልክቶች - እንደ እውቀትና እንደ ዲፕሎማ ወረቀት።
የጣዖት አምልኮ፣ እንደ ፎርጅድ ዲግሪ ቁጠሩት። ወይም በገፍ እንደታተመ የወረቀት ገንዘብ።
የትምህርትና የሙያ ብቃትን የሚመሰክር ወረቀት፣ ፋይዳም ክብርም አለው - የእውቀትና የችሎታ ምልክት ነውና። የውሸት ከሆነ ግን፣ “የምስክር ወረቀት” መሆኑ ይቀራል። ምንን ይመሰክራል? የብቃት ደረጃን ዘንግተን፣ ወረቀቱ ላይ ስንሻማ፣ ዋናውን ቁም ነገር ትተን፣ ምልክቱን ብቻ ታቅፈን እንቀራለን። ይሄኔ ነው፣ “የጣዖት አምልኮ” የሚሆነው።
ምልክት መኖሩ አይደለም ችግሩ። ቁምነገርን ያቀፈ ምልክት ጥሩ ነው። ከቁምነገሩ የተነጠለ ምልክት ነው፣ ችግሩ።
የብቃት ማረጋገጫ ሲሆን ነው የምስክር ወረቀት ክብሩ። ብቃትን የማይመጥን “ምስክር ወረቀት” ነው ቅሌቱ።
በአለባበስም ሆነ በአምልኮ ሥርዓት፣ በሕንፃ አሰራርም ሆነ በአርማ፣… ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ብዙ ሃይማኖቶች፣ በይፋም ሆነ በልማድ፣ በምልክት እጅግ የበለፀጉ ናቸው። ከዚህ ጎን ለጎን፣ “ምልክቶች” ላይ የሚሰነዘሩ መራራ ወቀሳዎችም፣ በብዛት ከሃይማኖቶች በኩል የሚመጡ ናቸው - “የጣዖት አምልኮ” በሚል። አለምክንያት አይደለም።
በአንድ በኩል፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ነገሮች፣… ሃይማኖትን የሚያመለክቱ ቁሳቁሶች፣… በብዙ አማኞች ዘንድ፣ እጅግ ይከበራሉ። አለማክበር አላዋቂነት፤… ማጣጣልም፣ ነውር ነው። ምክቶችን ማበላሸትና ማፍረስ ደግሞ፣ አስቀያሚ ጥፋት ይሆናል። ለዚያውም ጋጠወጥ ጭፍን ጥፋት። ሃይማኖታዊ ነገሮችን ማበላሸት፣ እንደ ተራ የንብረት ጉዳት ይቆጠራል? በሃይማኖት ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት ሆኖ ሲታያቸው አልታዘባችሁም? ይሄ ላይገርም ይችላል።
ሃይማኖታዊ ነገሮች፣ የሃይማኖት ምልክት ናቸው። የሃይማኖት ምልክቶችን ማክበር ደግሞ፣ የሃይማኖቶች የተለመደ ባሕርይ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሃይማኖት ምልክቶች፣ እንደ ጣዖት አምልኮ ተደርገው እየተቆጠሩ፣ ነቀፋ ይሰነዘርባቸዋል።
“በአምላክ ስም ማሉ”፣ “በአምላክ ስም ተናገሩ”፣ “የአምላክን ስም ቀድሱ” ብሎ ማስተማር አለ። ከዚህ ጋር፣ “የአምላክን ስም በከንቱ አታንሱ” የሚል ትምህርት መኖሩንም አትርሱ። ስም ማንሳት በቁምነገር ሲሆን መልካም ነው። ስም ማንሳት፣ በከንቱ በባዶ ሲሆን ግን፣ ስህተት ነው። በአምላክ ስም አትማሉ፤ እንዲያውም፣ መሐላ ይቅርባችሁ፣ አዎ ወይም አይደለም በሉ” የሚል የሃይማኖት ትምህርትም አለ። “ጌታዬ ጌታዬ ስላላችሁ አትጸድቁም” እንደተባለም ማስታወስ ይቻላል። “መልካም የሕይወት መንገድን ትታችሁ፣ የመስዋዕት አቀራረብ ወይም የፆም ስርዓትን ግን ብታከናውኑ፣ አምላክ አይፈልገው” የሚል ተግሳፅም ተመሳሳይ መልዕክት አለው።
ምክሮቹ የሚቃረኑ ይመስላሉ። ግን፣ ቅራኔ ላይሆን ይችላል።
በአንድ በኩል፣ “መሐላ መስጠት፣ የአክብሮት ስርዓት ማከናወን፣ ጽድቅን ማወደስ”፣… እንከን የለባቸውም። የእውነት፣ የቀና መንገድ፣ የመልካም ሕይወት ምልክቶች ናቸው። ጥሩ።
እውነትን ጥለን፣ የመልካምነትና የሕይወት መንገድን ትተን፣ ምልክቶችን ብቻ ታቅፈን ስንቀር ነው ችግሩ። ውሸትን እየተናገርን፣ እውነትን የተናገርን ለማስመሰል የሚያገለግል መሳሪያ እናደርገዋለን - መሐላ።
“የይስሙላ፣ የግብር ይውጣ፣ የታይታ፣ የይምሰል ብቻ አትሁኑ” የሚል ይመስለኛል - የትምህርቱ መልዕክት፣ የጣዖት አምልኮ ላይ የሚሰነዘረው ነቀፋ።
ዋናው ነገር፣ ሃይማኖትንና የሃይማኖት ምልክቶችን አለማምታታት ይመስላል - መፍትሔው። ምልክቶች፣ ዋናውን ቁምነገር የሚጠቁሙ፣ እንደ ማስታወሻ፣ እንደ መታሰቢያ የሚያገለግሉ፣ የአክብሮት ማሳያና መግለጫ፣ የግንዛቤ ማህተምና ምልክት ሲሆኑ በጎ ናቸው። ከቁምነገር ሲፋቱ ግን፣ ባዶ ይሆናሉ - የጣዖት አምልኮ እንዲሉ።


Read 2163 times