Print this page
Saturday, 21 May 2022 13:14

የአመቱ የአለማችን 2000 ግዙፍ ኩባንያዎች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   • የአሜሪካው ቤክሻየር ሃታዌ 1ኛ ደረጃን ይዟል
          • ኩባንያዎቹ በ12 ወራት 5 ትሪሊዮን ዶላር ትርፍ አግኝተዋል

              የኩባንያዎችን ሽያጭ፣ ትርፍ፣ ሃብትና የገበያ ዋጋ በማስላት በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ከሰሞኑም የ2022 የፈረንጆች አመት የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የአሜሪካው ቤክሻየር ሃታዌ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ኢንሹራንስ፣ ትራንስፖርት፣ ማኑፋክቸሪንግና ኢነርጂን በመሳሰሉ ሰፋፊ የንግድ ዘርፎች የተሰማራውና በአሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን በፌት የሚመራው ቤክሻየር ሃታዌ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 276.09 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ በማስመዝገብ፣ 89.08 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፤ የኩባንያው ሃብት 958.78 ቢሊዮን ዶላር፣ የገበያ ዋጋው ደግሞ 741.48 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የፎርብስ መረጃ ያሳያል፡፡
ላለፉት 9 ተከታታይ አመታት የአለማችን ቁጥር አንድ ግዙፍ ኩባንያ ሆኖ የዘለቀው የቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ ዘንድሮ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ያለ ሲሆን፣ የሳዑዲ አረቢያው የነዳጅ ኩባንያ አርማኮ 3ኛ፣ የአሜሪካው ጄፒ ሞርጋን 4ኛ፣ የቻይና ኮንስትራክሽን ባንክ ደግሞ 5ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ የአሜሪካው አማዞን 6ኛ፣ የአሜሪካው አፕል 7ኛ፣ የቻይና የግብርና ባንክ 8ኛ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ 9ኛ፣ የጃፓኑ ቶዮታ ሞተርስ 10ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ፎርብስ መጽሄት የአመቱ የአለማችን 2000 ግዙፍ ኩባንያዎች ብሎ የመረጣቸው ኩባንያዎች በድምሩ 47.6 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ፣ 5 ትሪሊዮን ዶላር ትርፍ፣ 233.7 ትሪሊዮን ዶላር ሃብትና 7.5 ትሪሊዮን ዶላር የገበያ ዋጋ ማስመዝገባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአመቱ 2000 የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች የ58 የተለያዩ የአለማችን አገራት ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ አሜሪካ 590 ኩባንያዎችን በዝርዝሩ ውስጥ በማካተት ቀዳሚነቱን ስትይዝ፣ ቻይና በ351፣ ጃፓን በ196 ኩባንያዎች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

Read 5891 times
Administrator

Latest from Administrator