Saturday, 21 May 2022 12:54

ከ50 አመታት በፊት በሳንዱች የተቀየረው ስዕል 350 ሺህ ዶላር ተሸጠ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ከ50 አመታት በፊት ነው…
ነዋሪነቱ በለንደን የሆነው ጆን ኬነር የተባለው ታዋቂ ካናዳዊ ሰዓሊ፣  አንድ ማለዳ የሆነ ሃሳብ ብልጭ አለለት፡፡ ጊዜም ሳያባክን ከቤቱ ወጥቶ ወደ አንድ ሬስቶራንት ጉዞ ጀመረ፡፡ሬስቶራንቱ ውስጥ እንደገባ፣ የድርጅቱን ባለቤት አይሪን ዴማስን አስጠራት፡፡ ራሱን አስተዋውቋት፣ ምግብ መግዣ ገንዘብ ስለሌለው የራሱን ወይም ወዳጆቹ የሆኑ የሌሎች ሰዓሊያንን የስዕል ስራዎች እየሰጣት በምላሹ ምግብ እንድትሰጠው ጠየቃት፤ ተስማማች፡፡
አንድ ምሽት…
ሰዓሊው ጆን ኬነር ጥሩ ሳንዱች መብላት አማረው፡፡ የቅርብ ወዳጁ የነበረችውና እንደ እሱው በድህነት ስትቆራመድ የኖረች ማውድ ሊዊስ የተባለች ሰዓሊ የሳለችውን “ጥቁር የጭነት መኪና” የሚል ርዕስ ያለው ስዕል ብድግ አደረገ፡፡ስዕሉን እያየ በድህነት ተቆራምዳ የሞተችውን ሰዓሊዋን ማውድ ሊውስን አሰባት፡፡ ኑሮ ዳገት ሆኖ ሲፈትናት የኖረችውንና አንዲት ክፍል ቤት ውስጥ በህመም ስትሰቃይ የባጀችውን ያቺን ምስኪን ሰዓሊ ሊውስን አስታወሳት፡፡
ቸግሯት ነበር፡፡ ድንቅ ሰዓሊነቷን የሚመሰክሩላት የመብዛታቸውን ያህል፣ ከአቅሟ በላይ የሆነውን የኑሮ ውድነት የሚያግዛትም ሆነ የዕለት እንጀራዋን  ለማግኘት ሲቸግራትና ስትራብ ስትጠማ እስኪ ይህቺን ቅመሽ የሚላት አላገኘችም ነበር፡፡ በችጋር ከመሞት ይልቅ የሚያማምሩ ስዕሎቿን እስከ 2 ዶላር በሚደርስ ገንዘብ እየሸጠች ርሃቧን ለማስታገስ ደፋ ቀና ስትል አሳዝናው ነበር፣ በደጉ ጊዜ እሷን ለመርዳት ሲል ገንዘብ አውጥቶ ይህን ስዕል የገዛት፡፡
ኬነር ሰዓሊዋን እያሰበ ትንሽ ተካከዘ፡፡ ሲተካክዝ ቆየናም፣ ስዕሉን ይዞ  ከቤቱ በመውጣት ወደ ሬስቶራንቱ አቀና፡፡
ለሬስቶራንቱ ባለቤት ቀደም ብለው በተስማሙት መሰረት ስዕሉን ሰጣት፤ እሷም ጣፋጭ የሆነ የአይብ ሳንዱች አቀረበችለት፡፡ ጆን ኬነር ከአመታት በፊት ከምስኪኗ ሰዓሊ ሊዊስ የገዛውን ታሪካዊ ስዕል ከፍሎ፣ የቀረበለትን ሳንዱች ማጣጣሙን ቀጠለ፡፡
ይህ ከሆነ ከ50 አመታት በኋላ…
ሰዓሊው ኬነር እ.ኤ.አ በ1973 በዚያች ምሽት ላጣጣማት ሳንዱች በክፍያ መልክ ለሬስቶራንቱ ባለቤት ያበረከታት ያቺ ታሪካዊ ስዕል፣ ከሰሞኑ ኦንታሪዮ ውስጥ ለጨረታ ቀርባ በ350 ሺህ ዶላር ተሸጠች፡፡ሚለር ኤንድ ሚለር በተባለው የካናዳ አጫራች ኩባንያ አማካይነት ለሽያጭ የበቃችው ስዕሏ 35 ሺህ ዶላር ያህል ታወጣለች ተብሎ ቢገመትም፣ በአስር እጥፍ ያህል በሚበልጥ ዋጋ ተሽጣ እነሆ ሰሞንኛ አለማቀፍ የስነጥበብ ወሬ ለመሆን መብቃቷን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

Read 1069 times