Saturday, 21 May 2022 10:56

ኢሰመኮ ከህግ አግባብ ውጪ ታስረዋል ያላቸው የኦነግ አባላት በአፋጣኝ እንዲፈቱ አሳሰበ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

 ኮሚሽኑ ለ10 ቀናት በስፍራው በመገኘት ምርመራ ማካሄዱን አመልክቷል
                     
             ከህግ አግባብ ውጪ በተለያዩ ወህኒ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮችና  አባላት በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡
ከመጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በቡራዩ በገላንና በሰበታ ከተሞች ፖሊስ መምሪያዎች በአካል በመገኘት ምርመራና ክትትል ማካሄዱን የጠቆመው ኮሚሽኑ፤ የምርመራ ግኝት ሪፖርቱንም ይፋ አድርጓል።
እስረኞችን፣ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎችን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንንና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተወካዮችን ማነጋገሩን ያመለከተው ኢሰመኮ፤ በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት እስረኞቹን በሚመለከት በፍርድ ቤትና በዐቃቤ ህግ የተሰጡ ውሳኔዎችንና ትዕዛዞችን እንዲሁም የህክምና ሰነዶችን መመርመሩን አስታውቋል።
በምርመራውም ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደላቸው፣ የክስ መዝገቦቻቸው ተዘግተው በፍርድ ቤት ውሳኔ በነፃ የተሰናበቱ፣ ምንም ዓይነት ክስ ያልተመሰረተባቸውና ዐቃቤ ህግ ክስ የማይመሰርትባቸው መሆኑን በማረጋገጡ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ ሆኖም ከወራት እስከ ሁለት ዓመት ለሚሆን ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ከህግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙና የተወሰኑትም በእስር ሂደቱ በተፈጸመ ተገቢ ያልሆነ አያያዝና ድብደባ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶችና የጤና ችግር የተጋለጡ እስረኞች መሆናቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ እንደገለጹት፤ የኦነግ ፓርቲ አመራሮች ለተራዘመ ጊዜ ከህግ አግባብ ውጪ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁና ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል።
ከዚህ በተጨማም የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ህግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ እየተጣሱ እስረኞቹ ከህግ አግባብ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ስለሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድበት ይገባል ብለዋል፤ኮሚሽነሩ።
እስረኞቹ ለኮሚሽኑ አባላት የደረሰባቸውን ግፍና በደል በዝርዝር ማስረዳታቸውን የጠቆመው ይኸው ሪፖርት፤ ድብደባ፣ ማሰቃየት፣ ምግብና ውሃ መከልከል፣ ህክምና እንዳያገኙ ማድረግ፣ ያሉበትን ከቤተሰብ መሰወርና የስነ-ልቦና ጫና  እንደተፈጸመባቸው መናገራቸውን አመልክቷል፡፡ ስለጉዳዩ የመንግስት አካላትን ጠይቆ እንደነበር የገለጸው ኮሚሽኑ፤ “ጉዳዩን የያዘው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በመሆኑ እኛ እስረኞችን ይዘን ከማቆየት ውጪ የተጠረጠሩበት ጉዳይ እኛን አይመለከተንም” በማለት የቡራዩ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ምላሽ መስጠቱን አመልክቷል።
በገላንና በሰበታ ፖሊስ መምሪያዎች በአካል ተገኝቶ ጉብኝት ማድረጉን የጠቆመው የኮሚሽኑ  ሪፖርት፤ ጉብኝት በተደረገበት ወቅት የኦነግ አመራሮች የሆኑ እስረኞች በእስር ቤቱ የሌሉ መሆኑ በፖሊስ እንደተገለጸለት አመልክቷል። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ በእስር ቤቶቹ ውስጥ ባደረገው ምልከታ የኦነግ ፓርቲ አመራሮች መሆናቸውን የገለጹ እስረኞችና ሁለት የኦ.ኤን.ኤን ጋዜጠኞች ማግኘቱን ገልጧል። እስረኞቹ ምርመራቸው ተጠናቆ መዝገቦቻቸው ለዐቃቤ ህግ መተላለፉንና የዐቃቤ ህግ ውሳኔን  በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ እንደተገለጸለት ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመልክቷል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን ያመለከተው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ ፖሊስ ኮሚሽኑም በሰጡት ምላሽ፤ “የኦነግ አመራሮች የተባሉ ተጠርጣሪዎች በሙሉ እንደተፈቱ ነው የምናውቀው” ማለታቸውን ጠቁሟል፡፡
ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በኩል አገኘሁት ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የተወሰኑ የኦነግ አመራሮች በ2013 ዓ.ም ክስ ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ያልተገኘባቸው በመሆኑ የምርመራ መዝገቡ ተዘግቶ ተጠርጣሪዎቹ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ መተላለፉን፣ የተወሰኑት ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸው በፍርድ ቤት ነፃ መባላቸውን በመግለጽ፤ በአሁኑ ወቅት በኮሚሽኑ ምርመራ ስማቸው ከተጠቀሰው እስረኞች መካከል በምርመራ ላይም ሆነ በክስ ሂደት ላይ የሚገኙ እንደሌሉበት አረጋግጫለሁ ብሏል።
ኮሚሽኑ በምርመራው እስረኞቹ ያለ ተገቢ የፍርድ ሂደት፣ የፍርድ ቤት ወይም የዐቃቤ ህግ ውሳኔዎችንና ትዕዛዞችን በመቃረን በህግ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውጪ በእስር እንዲቆዩና በተደጋጋሚ ከቦታ ቦታ እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን፣ የተወሰኑ እስረኞችም በተፈጸመባቸው ድብደባ ምክንያት ለአካል ጉዳትና የጤና ችግር መጋለጣቸውን ማረጋገጡን አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ባቀረበው ምክረ ሃሳብም፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፖሊስ ኮሚሽን፣ ያለተገቢ ፍርድ በእስር ላይ የሚገኙትን እስረኞች በአፋጣኝ ከእስር እንዲፈታና በእስረኞቹ ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ እንዲከፍል እንዲሁም በእስረኞቹ ላይ ድብደባ የፈጸሙ የኦሮሚያ  ክልላዊ መንግስት የጸጥታ አባሎችና ኃላፊዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ ተገቢ እርምጃዎች እንዲወሰዱና የህግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አሳስቧል።Read 10172 times