Saturday, 14 May 2022 00:00

ላልተጻፈው መልክዐ - ዓለማየሁ የተዘጋጀ መግቢያ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ዓለማየሁ ገላጋይ የሚጽፈው ምናባዊ ይሁን እውናዊ ታሪክ፣ ለታሪኩ የሚያለብሰው የሐሳብ እና የስሜት ስጋ እና መንፈስ፣ ይህንኑም ለአንባቢ የሚያቀርብበት ቅርፅ (ማኅደሩ)፣ እነዚህን ሁሉ ወደ አንባቢው የሚያደርስበት ቋንቋ እጅግ የሚያሳስበው ደራሲ ነው፡፡ “አጥቢያ”፣ “ቅበላ”፣ “የብርሃን ፈለጎች”፣ “ወሪሳ”፣ “በፍቅር ስም”፣ “ታለ፤ በእውነት ስም”፣ “ሐሰተኛው፤ በእምነት ስም” የተባሉት ረጅም ልቦለዶቹ እና “ኩርቢት” እና “ውልብታ” የአጫጭር ተረኮች መድበሉ ሙያውን አውቆ ስለመጻፉ ምሥክሮች ናቸው፡፡
ደራሲው ከጠቀስኳቸው የፈጠራ ሥራዎቹ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ጉልህ ስፍራ የሚያሰጡት ሁለት ጥናታዊ መጽሐፎችም አሉት፤ ሁለቱም በደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ሕይወት እና የሥነ ጽሑፍ አበርክቶዎቹ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው “ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር፤ ሕይወት እና ክህሎት” (2000 እና 2009) የተባለው በዋነኛነት የስብሃትን ሥራዎች ያሄሰበት መጽሐፉ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ ወደ ሠላሳ ገደማ ሐያስያንን፣ ደራስያንን፣ ገጣሚያንን እና ሰዓሊያንን አስተባብሮ የሠራው፣ የስብሃትን ገፀ ብዙነት የሚያሳየው “መልክአ ስብሐት” (2005) ሥራው ነው፡፡
ደራሲው ምናባዊ ሳይሆን እውናዊ መብሰልሰሎቹን፣ ቁዘማዎቹን፣ እሳቤዎቹን፣ ስሜቶቹን ያስተላለፈባቸው እና ከሰውየው ከአቶ አለማየሁ ገላጋይ ጋር ያቀራርቡናል፤ የልቦለድ ድርሰቶቹን ሳይቀር፣ ለመረዳት ያግዙናል ብዬ የማምንባቸውን “ኢህአዴግን እከሳለሁ” (2004) እና “መለያየት ሞት ነው” (2010) የመጣጥፍ ስብስቦቹን አሳትሟል፡፡
Michel de Montaigne “our life is nothing, but movement.” ይላል- ሕይወታችን ሌላ ሳይሆን እንቅስቃሴ ነው- ድርሰት የዚህ እንቅስቃሴ ማቆሚያ ልጓም ነው፡፡ በአለማየሁ ወጎች ተጽፈው በቃቸው ብሎ እስኪወስንባቸው ድረስ ውስጡ ሲሯሯጡ፣ ቁጭ ብድግ ሲሉ እና ሲያስብሉት የነበሩ ሐሳቦቹ፣ ስሜቶቹ፣ እምነቶቹ ከእንቅስቃሴያቸው ተገትተው የቀረቡባቸው ናቸው፡፡
እነዚህ ወጎቹ ሐያሲነቱ፣ ጥልቅ አንባቢነቱ እና ጨዋታ አዋቂነቱ ጭምር የታዩባቸው ናቸው፡፡ ዓለማየሁ ተርጓሚነቱ የታየበት “የፍልስፍና አፅናፍ” የተሰኘ መጽሐፍም አለው፡፡ ዓሌክስ ሌላው ቅጥያ ሁሉ ቀርቶብኝ ደራሲ ብቻ ልባል ቢልም፣ በአርታዒነት፣ በሐያሲነት፣ በተርጓሚነት እና በንግግር አዋቂነት እናውቀዋለን፤ 14 መጻሕፍቱን እና ሰውየውን በምልዓት ለማሳየት “መልክዐ ዓለማየሁ” የሚል መጽሐፍ መጻፍም አይበቃኝ፡፡
ድኅረጡፍ፡- አሁን አሌክስ “የተጠላው እንዳልተጠላ” የሚል ሥራ ሊሰጠን አጓጉቶናል፡፡ የአሌክስን አዲስ ሥራ እርግጠኝነት በተጫነው ጉጉት ለመጠበቅ የሚገፋፋን ይህ ከሽፎብን የማያውቅ አባባሉ ይመስለኛል፡- “የሚቀጥለው ሥራዬ ከአሁኑ አዲስ መሆን አለበት፤ ለምንድነው የምደጋግመው፤ የተሰጠኝ ብዙ ነው፡፡ መደጋገም መጀመሬን ጥሩ ወዳጅ የነገረኝ ቀን አቆማለሁ፡፡ ነባሮቹ ተደጋግመው ይታተሙ፡፡ መዘብዘብ ምን ያደርጋል!”

Read 1486 times