Saturday, 14 May 2022 00:00

ተፈጥሮን የመመለስ ተጋድሎ በአርሲ ጭላሎ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዛሬ 40 እና 50 አመት በፊት ሙሉ በሙሉ በደን የተሸፈነ ነበር። ያውም በተፈጥሮ የጥድ ዛፎችና በተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች። ዛሬ ግን ለምልክት ያህል ታሪክ ነጋሪ፣ ትናንትን ዘካሪ መስለው እዚህም እዚያም ጣል ጣል ብለው ከቆሙት እድሜ ጠገብ የጥድ ዛፎች በስተቀር ወደ ምድረ በዳነት ተለውጧል ማለት ያስደፍራል።
በአካባቢው ተወልደው ጣፋጭ የልጅነት ጊዜያቸውን በዚያ ደጋማ አየርና ጥቅጥቅ ደን ውሰጥ ያሳለፉ ሁሉ በቁጭት የሚያወሩለት አካባቢ ነው - አርሲ ዞን ውስጥ የሚገኘው የጭላሎ ጋሌማ አካባቢ። የጭላሎ አካባቢና ተራራማ ሰንሰለቶች የውሃ ማማነታቸው የተመሰከረላቸው፣ በበርካታ የአፋን ኦሮሞ ዘፈኖች ውስጥ ስማቸው ተደጋግሞ የሚጠቀስ ነው።
ታዋቂው የኦሮምኛ ዘፋኝ አበበ አሸተው በአንድ ተወዳጅ ዘፈኑ “ጭላሎ ጎባ በዬን ቀመዲ በቆጂ ገዲ ኢላላ” ሲል የአካባቢውን ውበትና መልክአ ምድር እንዲሁም የስንዴ አዝመራ የሚታፈስበት መሆኑን ይገልፀዋል። ይህም ማለት “ጭላሎ ላይ ወጥቼ የበቆጂን የስንዴ ሰብል አካባቢን ቁልቁል ልየው” እያለ።
ይህን በልባቸው የሚዘምሩና በልጅነታቸው የአካባቢውን ውብ ገፅታ የሚያስታውሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ፊዚክስ ያስተማሩት ዶ/ር ሙሉጌታ በቀለ፤ “ሥፍራው ለሶስት የውሃ ተፋሳሾች የሚመግቡ ምንጮችና ጅረቶች መነሻ የሆነ የአካባቢው የውሃ ማማ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም” ይላሉ።
የዶ/ር ሙሉጌታን ሃሳብ የሚጋሩት የአካባቢው ተወላጅ ሻምበል በለጠ ማሞ በበኩላቸው፤ በአሁን ወቅት አካባቢው ተራቁቶ፣ በርካቶቹ ምንጮች ደርቀው፣ ውብ የነበረው መልክአ ምድርና ስነ ምህዳር ተጎሳቁሎ ሲመለከቱት ሁሌም ቁጭት እንደሚፈጥርባቸው ይናገራሉ።
ሻምበል በለጠም ይሁኑ የአካባቢው ተወላጅ ምሁራን ይህን ቁጭታቸውን እያብሰለሰሉ፣ እጅና እግራቸውን አጣጥፈው ለመቀመጥ አልፈለጉም። ያ የዋቢ ሸበሌ ወንዝ መነሻ፣ የአዋሽ ወንዝ ገባሮች መነሻና የተለያዩ ምንጮች መገኛ የሆነው ምድር  ወደ ነበረበት ለመመለስ ያስችላል ያሉትን መፍትሄ ነበር የተለሙት። አስቀድሞ በሻምበል በለጠ የተጀመሩ ተግባራት የነበሩ ቢሆንም፣ ሌሎች የአካባቢው ተወላጅ ምሁራን እንደ እነ ዶ/ር ጌታቸው ተድላ፤ ዶ/ር አጥላው ንጉሴ፤ ዶ/ር ሙሉጌታ በቀለና ሌሎች በመሰባሰብ፣ አካባቢውን በደን ለማልበስ ያስችላል ያሉትን ፕሮጀክት የካቲት 4 ቀን 2010 ዓ.ም በይፋ ሊጀምሩ ችለዋል።
“ፕሮጀክቱን የጀመርነው እዚያው አርሲ የተወለድን፣ የአካባቢው ስነ ምህዳር መጎሳቆል ያሳሰበን ከሁሉም ብሄር የተሰባሰብን ተወላጆች ነን” የሚሉት ዶ/ር ጌታቸው ተድላ፤ “በተለይ በአካባቢው ተወልደን ያደግን ሰዎች ቀድሞ በደን ተሸፍነው የውሃ ምንጭ የነበሩት ተራራዎች ተራቁተው፣ ድንጋያቸው ፈጦና አግጦ ማየት እጅግ ልባችንን የነካ ጉዳይ ነበር” ይላሉ።
ከዚህ ቁጭት በመነሳት የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት በፍጥነት ለመመለስ ያስችላል ያሉትን በዋናነት የቀርከሃ ተክልንና ደንን የማስፋፋት ፕሮጀክት ወደ መዘርጋቱ ሊገቡ እንደቻሉ ያወሳሉ- ዶ/ር ጌታቸውና ጓደኞቻቸው። “ጭላሎ ጋሌማን በደን እናለብሳለን” ብለው የዛሬ አራት አመት የጀመሩት ፕሮጀክት ምን ላይ እንደደረሰ የመስክ ምልከታ ለማድረግና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለመተለም ያለመ የመስክ ጉብኝትም ቅዳሜ ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም የፕሮጀክቱ የቦርድ አባላትና አመራሮች አከናውነው ነበር።
አዲስ አድማስም ብቸኛው የጉብኝቱና የመስክ ምልከታው ተሳታፊ ሚድያ የነበረ እንደመሆኑ የፕሮጀክቱን ጠንሳሾች ፕሮጀክቱ ሊያሳካቸው ያቀዳቸውን ጉዳዮች፣ እስካሁን ያስመዘገባቸውን ውጤቶች እንዲሁም በዋናነት በቀርከሃ ተክል ላይ ለምን እንደተተኮረና የቀርከሃን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በተመለከተ ፕሮጀክቱን እየተገበረ የሚገኘው “የሪል ግሪን ቪሽን ጀነሬሽን ኢትዮጵያ” ድርጅት ስራ አስኪያጅን ሻምበል በለጠ ማሞን፣ የቦርድ ሊቀ መንበሩን ዶ/ር ሙሉጌታ በቀለን እንዲሁም የፕሮጀክቱ የፕላንና እቅድ መሪውን የምጣኔ ሃብት ምሁሩን ዶ/ር አጥላው ንጉሴን በጉብኝቱ የተሳተፈው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል።




            “ፕሮጀክቱን ስንጀምር ምንም ባጀት አልነበረንም”


         በቅድሚያ ራስዎን ያስተዋውቁንና ስለ ፕሮጀክቱ ቢነግሩን?


ሻምበል በለጠ ማሞ እባላለሁ በሙያዬ ወታደር ነኝ። ሃረር ሚሊተሪ አካዳሚ ነው የተመረቅሁት፡፡ በሶማሊያ ጦርነት ወቅት 11 ዓመት ሶማሊያ ታስሬ ተመልሻለሁ። ከዚያ በኋላ ትንሽ ጊዜ የመንግስት ስራ ላይ ከሠራሁ በኋላ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትን አቋቁሞ መስራትን ነው የመረጥኩት። በመሃል ላይ እንደ አጋጣሚ ቃሊቲ እስር ቤት ገብቼ ነበር፡፡ በወቅቱ በተለይ በሶማሊያ እስር ቤት ያሳለፍኩትን ታሪክ ፅፌ በመፅሐፍ መልክ ከማዘጋጀት ጎን ለጎን፣ ከእስር ቤት ስወጣ የምሰማራበትን ስራም ፕሮጀክት ነድፌ ነበር፡፡ በወቅቱ እኔ ሲፈረድብኝ ባለቤቴ በደም ግፊት ህይወቷ አልፎ ነበር፡፡ እኔ ግን በእስር ላይ የቆየሁት ሁለት ዓመት ነበር፡፡  ከእስር ከተፈታሁ በኋላ እንደገና መንግሰት ይፈልገኝ ስለነበር ወደ አርሲ አካባቢ መጣሁ (ቃለ ምልልሱ የተደረገው በአርሲ ጭላሎ ጋሌማ አካባቢ ባለው መስክ ላይ ነው)። ወደዚህ ስመጣ ቀጥታ ይሄን ተራራ ነው በፈረስ ላይ ሆኜ  ተዘዋውሬ የጎበኘሁት፡፡ ቦታው አርሲ ጭላሎ ጋሌማ ይባላል፡፡  የታላቁ ዋቢ ሸበሌ ወንዝ መነሻዎች እነዚህ ተራራዎች ናቸው። ዋቢ ሸበሌ ከዚህ አካባቢ ተነስቶ ነው ሶማሊያ ገብቶ ህንድ ውቅያኖስ አካባቢ አሸዋ ውስጥ ሰርጎ የሚቀረው፡፡ በዚህ በስምጥ ሸለቆ ኮሪደር በኩልም ከታር የሚባል ወንዝ አለ፡፡ የዚያ ወንዝ ገባሮችም መነሻ ጅረቶችም እነዚሁ ተራራዎች ናቸው። ዝዋይ፣ ቡልቡላ ሃይቅ፣አብያታ ሃይቅ እስከ ላንጋኖ ድረስ የሚሄዱ የውሃ ሃብቶች ምንጩ ይሄ የጭላሎ ጋላማ አካባቢ ነው። እነዚህ ተራራዎች ተራቆቱ ደረቁ ማለት በርካታ የስነ ምህዳር ችግር ይከሰታል፡፡ ስለዚህ የነደፍኩትን ፕሮጀክት በዚህ ቦታ ላይ መተግበር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ከዚያም የፕሮጀክት ሃሳቡን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ላሉ መምህራን ወዳጆቼ አቀረብኩላቸው፡፡ እነሱም በሃሳቡ ተደሰቱ፡፡ አካባቢው  የአዋሽ ወንዝም ገባር ጅረቶች የሚመነጩበት እንደመሆኑ ትልቁ የውሃ ምንጭ ነው። ይሄ አካባቢ ተራቆተ ማለት ብዙ ችግር ነው የሚያጋጥመን፡፡ ይሄ በእጅጉ ያሳስበኝ ነበር፡፡ መራቆቱ በዚሁ ከቀጠለ ከ25 ዓመት በኋላ የአካባቢው ህዝብ በድርቅ ምክንያት ሊሰደድ ይችላል የሚል ምልከታም ነበረኝ። የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያማከርኳቸው ወዳጆቼ፤     “ስራውን በጋራ እንሰራለን፤ በል አሁን ፍጠንና የድርጅቱን ፈቃድ አውጣ” አሉኝ፡፡ ፈቃዱን እንደምንም አውጥቼ ስራው ተጀመረ ማለት ነው፡፡
ስራውን ስንጀምር ምንም አይነት በጀት አልነበረንም፤ የቤት እቃዎችን እየሸጥን ነው የጀመርነው፡፡ በመሃል ላይ አትሌት ደራርቱ ቱሉ አንድ ስብሰባ ላይ 50 ሺህ ብር ሰጠችን፡፡ መነሻችን ያ ገንዘብ ነው። ከዚያ በተረፈ የቤት እቃዎቻችንን ፍሪጅ የመሳሰሉትን እየሸጥን ነው የጀመርነው። በመጨረሻም UNDP ይሔን ጥረታችንን ተመለከተና ፕሮጀክት ፕሮፖዛል አቅርቡ አለን፡፡  አቀረብን። 1.4 ሚሊዮን ብር ሰጠን። በዚያ 1.4 ሚሊዮን ብር በ5 ወረዳዎች ላይ መልሶ የደን ማልበስ ስራ ጀመርን ማለት ነው፡፡ አሁን ላይ ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር ሞዴል የተፋሰስ ስራ መሆኑን መስክሮ ልክ እንደራሱ ፕሮጀክት አድርጎ 1.2 ሚሊዮን ብር መደበልን። በዚህ 1.2 ሚሊዮን ብር የችግኝ ማፍያ ጣቢያ ተሰርቷል፤ አስቀድሞ እንደ ጎበኛችሁት የቀርክሃ ችግኞችን በቦታው በስፋት እያፈላን ነው፡፡ ያፈላነውን ችግኝ ወደ ተራቆቱ ተራራዎች ወስደን እየተከልን ነው፡፡ አሁንም ተተክለው ያሉ አሉ፡፡ ቀርከሃ ደግሞ በባህሪው በየቀኑ በ50 ሴንቲሜትር ነው ወደ ላይ የሚረዝመው። በዚህ መሰረት ከ3 ዓመት በኋላ ለምርት ይደርሳል ማለት ነው፡፡ ይሄን ስናደርግ ሌላ የገበያ እድል ይፈጥራል፡፡ የቀርክሃ ስራ በጣም የተለመደና እየተስፋፋ ያለ ነው፡፡ የኛ ፕሮጀክት በሌላ በኩል የገበያ ትስስር ይፈልጋል ማለት ነው፡፡ ለዚህ እንዲረዳን አዲስ አበባ ላይ የእደ ጥበባት ማዕከል አቋቁመናል፡፡  አዲስ አበባ ላይ የከፈትነው  የቀርከሃ የዕደ ጥበብ ማዕከል 4መቶ ሺህ ብር ፈጅቶብናል። ሌላው ደግሞ አዳማ ላይ 560 ሺህ ብር ገደማ በፈጀ ወጪ የፍራፍሬ ዛፎች፣ የከተማ ግብርና ሠርቶ ማሳያና የቆላ ቀርከሃ ችግኝ ጣቢያ ሠርተናል። ይሄ ፕሮጀክታችን በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት የተራቆቱ የሰሜንና የአርሲ ቆላማ አካባቢዎችን የሚሸፍን ይሆናል፡፡ ወደ 10 ሺህ ችግኝ በአንድ ጊዜ ማምረት እንችላለን፡፡ በዓመት ሶስት ጊዜ ችግኝ ማምረት ስለሚቻል፣ ወደ 30 ሺህ ችግኝ በዓመት እናመርታለን፡፡ 30 ሺህ ችግኝ ደግሞ ወደ 30 ሄክታር መሬት መሸፈን የሚችል ነው፡፡ በዋናነት ቀርክሃ ላይ እናተኩር እንጂ የፍራፍሬ ዛፎችንም በስፋት እያዘጋጀን ነው፡፡  በቀጣይ ድርጅቱ ራሱን በገቢ እንዲችል በርካታ ጥረቶች እያደረግን ነው፡፡
የቀርከሃ ችግኝ ጣቢያው ከተቋቋመ በኋላ ምን ያህል ችግኞች ተዘጋጅተው ጥቅም ላይ ውለዋል?
ችግኝ ጣቢያው የተቋቋመው የዛሬ 4 ዓመት 2010 ላይ ነው፡፡ በመጀመሪያው ዓመት 8 ሺህ የቀርክሃ ችግኞች ተዘጋጅተው ለ11 ቀበሌ አርሶ አደሮች ተዳርሷል፡፡ እንደገና በዓመቱ ደግሞ ወደ 5 ሺህ ችግኞች በተመሳሳይ ለአርሶ አደሮቹ ተዳርሷል፡፡ እንደገና በዓመቱ ደግሞ ወደ 5 ሺህ ችግኞች  ለአርሶ አደሩ ተሰራጭተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ደግሞ 4 ሺህ ችግኞች  ተሰራጭተው ተተክለዋል፡፡ በአጠቃላይ 19 ሺህ ያህል ችግኞች ተሰራጭቷተዋል፡፡ ከ17 ሔክታር በላይ መሬት ላይ የቀርክሃ ተክል ተተክሏል።

____________________


               “የአካባቢው የውሃ መጠን ወደ ነበረበት እንዲመለስ እየሰራን ነው”


                  በቅድሚያ ራስዎን ቢያስተዋውቁን?
ሙሉጌታ በቀለ እባላለሁ፡፡ የፊዚክስ መምህር ነኝ። በፊዚክስ መምህርነቴ ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1995 ጡረታ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳገለግል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በጡረታ 19 ዓመት ቆይቻለሁ። ነገር ግን አሁንም በኮንትራት ስምምነት ማስተማሬን አላቋረጥኩም፡፡
እንዴት የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ ችግኝ የማልበስ ፕሮጀክቱ ተሳታፊ ሆኑ?
እኔ ተወልጄ ያደኩት አርሲ ሳጉሬ አካባቢ ነው፡፡ እዚያው እስከ 12 ተምሬ ኋላም ቀዳማዎ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ ገባሁ ማለት ነው፡፡ በስራ አለም በቆየሁባቸው አጋጣሚዎች ወደ ተወለድኩበት ቦታ  በምመጣባቸው ጊዜያት ሁሉ ግን የአካባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየተራቆተ መምጣት ያሳስበኝ  ነበር፡፡ ይሄ ሁኔታ  እንዴት መገታት ወይም የተራቆተው መመለስ ይችላል የሚለውን ከወዳጆቻችን ጋር እንመካከር ነበር፡፡ በተለይ የአካባቢው ተወላጆች የሆንን የኢኮኖሚክስ ምሁር ዶ/ር አጥላው ንጉሴ፣እነ ፕ/ር አበበ ጌታሁን፣ ፕ/ር እንደሻው በቀለ ፣ዶ/ር ጌታቸው ተድላ ያሉ እዚሁ አርሲ አካባቢ ተወልደን ያደግን ሰዎች መመካከር ጀመርን፡፡
በዋናነት የፕሮጀክታችሁ አላማ ምንድን ነው?
እንደሚታወቀው አርሲ ጭላሎ ጋሊማ አካባቢ የሶሰት የውሃ ተፋሰስ ምንጮች መገኛ ነው፡፡ በልጅነታችን ያየነውን የውሃ ሃብት ወደ ነበረበት  ለመመለስ ነው ዛሬ ጥረት እያደረግን ያለነው፡፡
በዋናነት የቀርክሃ ችግኝ መትከል ላይ ነው እየሰራችሁ ያለው። ቀርክሃን ለምን መረጣችሁ? ቀድሞ አካባቢው በቀርክሃ ይታወቅ ነበር?
ቀርከሃ ድሮ አልፎ አልፎ ነበር በአካባቢው የሚገኘው፡፡ ቀርክሃ አፈር ቆንጥጦ የመያዝ ባህሪ ያለው ነው፡፡ በተለይ ተዳፋት ቦታዎች ላይ ቀርክሀ ከተተከለ አፈር አይሸረሸርም። ውሃ ወደ መሬት ሠርጎ እንዲገባ በማድረግ የአካባቢውን የውሃ ሃብት በሚገባ መጠበቅ የሚያስችል ተክል ነው፡፡ የአካባቢው የውሃ መጠን ወደ ነበረበት እንዲመለስ ነው እየሰራን የቆየነው፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ሌሎች የፍራፍሬ ዛፎችን ጨምሮ መትከል ይጀመራል፡፡
በቀጣይ የያዛችኋቸው እቅዶች ምንድን ናቸው?
በቀጣይ ስራችንን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከግብርና ሚኒስቴርና ከእነ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ጋር እየሰራን ስለሆነ ትልቅ ለውጥ እናመጣለን። በተለይ የግብርና ሚኒስትሩ የቅርብ ድጋፍና ክትትል ያደርጉልናል። እሳቸው ባቀረቡልን ሃሳብ መሰረትም፣ ስራውን አስፋፍተን በጭላሎ ጋሌማ ዙሪያ ያሉ 25 ወረዳዎችን ለማካለል  ነው እቅዳችን፡፡
የዚህ ፕሮጀክት ጠንሳሽ ማን ነው?
ስራችን ህጋዊ ሰውነት ያለው እንዲሆን ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ ቀደም ብሎ ህጋዊ እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረው ሻምበል በለጠ ማሞ ነው፡፡ እሱን ማግኘታችን እንቅስቃሴያችን ህጋዊ ሰውነት እንዲኖረው ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። የጭላሎ ጋሌማን እናልማ የሚለውን ሃሳብ ዶ/ር አጥላው እኔ፣ሻምበል በለጠ ሆነን መከርንበትና የአካባቢውን ተወላጆች ማሰባሰብ ጀመርን። በዚህም በርካቶችን አካተትን፡፡ በኋላም የካቲት 4 ቀን 2010 ቦርዱን በልዩ ስነስርዓት አቋቋምን፡፡ በኋላም “የተባበሩት የልማት ፕሮግራም” ለሁለት ዓመታት የቆየ ድጋፍ አደረገልን። 48 ሺህ ዶላር ነበር የሰጡን፡፡ በሱ ሁለት ዓመት ስንንቀሳቀሰ ቆየን፡፡ በኋላም ግብርና ሚኒስቴር 1.2 ሚሊዮን  ብር ድጋፍ አድርጎልን አሁን በዚህ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ሌሎች ባለሃብቶችም ድጋፍ እያደረጉልን ነው፡፡ ይህ 1.2 ሚሊዮን ብር የዚህ ዓመት ክረምት መግቢያ ድረስ ያቆየናል የሚል ሃሳብ አለን፡፡ በቀጣይ ግን ከልመና ወጥተን ራሳችንን ለመቻል እያሰብን ነው፡፡
ፕሮጀክቱ ራሱ ገንዘብ ማመንጨት የሚችልበት መንገድ አለ?
አዎ፣ የቀርክሃ ስራዎችን መስራት ይቻላል፡፡ ከወዲሁ የጀመርናቸው ስራዎችም አሉ፡፡ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ቀርከሃም ብዙ አይነት ምርቶችን ይሰጣል፡፡ ከከሠል ጀምሮ የቀርከሃ ወንበሮች፣መኖሪያ ቤት እና ድልድይ ስራ ድረስ ጥቅም አለው፡፡ ወደ ቀርከሃ ውጤቶች ምርት ለመግዛት ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው።

_______________________


                “ቀርከሃ ሰፊ ጠቀሜታ ያለው የኢንዱስትሪያል ተክል ነው”


           ራስዎን ያስተዋውቁንና ስለ ፕሮጀክቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ይንገሩን?


መልካም። እኔ አጥላው አለሙ እባላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ነኝ፡፡ ቀደም ብሎ ሙያዬ ምህንድስና ነበር። ከዚያ ኢኮኖሚክስ ላይ አተኩሬያለሁ ማለት ነው፡፡ ስለ ፕሮጀክታችን ጥቂት ለማብራራት ያህል፣ በዋናነት የተሰማራነው የቀርክሃ  ተክል ላይ ነው፡፡ የቀርክሃ ተክል ቶሎ አድጎ መሬትን በመሸፈን  የአፈርና የውሃ ሃብት ጥበቃን ከማገዙም ባሻገር ካደገ በኋላም በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ትልቁ አሳሳቢ ነገር የተፈጥሮ ሃብታችንን እያጣን መሆኑ ነው፡፡ ደኖች እየወደሙ ወንዞች እየደረቁ ነው፡፡ ስለዚህ የደኖችን ይዞታ መመለሱ ወሣኝ ነው፡፡ ቀርክሃ ደግሞ ፈጥኖ መሬትን በደን ለማልበስ በጣም ጠቃሚ ነው። ቀርክሃ የአካባቢ ጥበቃን ፈጥኖ ለማከናወን ከማገዙም ባሻገር ፈጣን  የሆነ ቀጥተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አለው፡፡ ዛፉን መሸጥ ይቻላል፤ የቀርክሃ እንጨት ጠንካራ በመሆኑ በኮንስትራክሽን ግንባታ ስካፎልድ (መውጫ) መስሪያ ይሆናል፤ ለከሰል ይሆናል፣ በበቂ ሁኔታ የሚመረት ከሆነ ጨርቃ ጨርቆች ይመረትበታል፤ ቅጠሉ ለእንስሳት መኖ ይሆናል፤ እንቡጡ  ደግሞ ለሰውም ምግብ ይሆናል። ቀርክሃ ከምግብነት፣ ከአካባቢ ጥበቃ  ጀምሮ ባለ ብዙ ዘርፍ ጥቅም ያለው ነው፡፡ በየ3 ዓመቱ ፈጥኖ ለምርት የሚደርስ መሆኑ እንዲሁም፣ ፈጥኖ ራሱን የሚተካና የሚራባ መሆኑም ተመራጭ ያደርገዋል። ቀርክሃ በአጠቃላይ ሰፊ ጠቀሜታ ያለው ኢንዱስትሪያል ተከል ነው፡፡ የገበያ ትስስር ከተፈጠረለት በሰፊው የስራ እጦትን ይቀርፋል፡፡ በኢኮኖሚ ማህበራዊና አካባቢ ጥበቃ በኩል እጅግ ተዘርዝረው የማያልቁ ጥቅሞች ያሉት ተክል ነው፡፡
ይሄን ጠቀሜታ ለገበሬው እያስገነዘባችሁ ነው?
የስልጠና ማዕከል አዘጋጅተናል፡፡ እናሰለጥናለን፤ እናስተምራለን፡፡ ተክሉን ከማርባት ጀምሮ ወደ ምርትና እደ ጥበባት የሚገቡበትን መንገድ እናሰለጥናለን። ለወደፊትም ሠፊ የማስገንዘብ  ስራ እንሰራለን፡፡ አሁን ተክሉን መትከልና ማራባት ላይ ነው ያተኮርነው። በቀጣይ ወደ ኢንዱስትሪ የሚቀየርበትን መንገድ በሰፊው እናሰለጥናለን፡፡ ቀርክሃ ሁለት አይነት ዝርያ ነው ያለው፡፡ የደጋ እና የቆላ ተብሎ ይከፈላል፡፡ የደጋውን ዝርያ ለማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ አሁን የዚህን የደጋ ቀርክሃ ነው እያራባን ለገበሬው እያከፋፈልን ያለነው፡፡ የተደራጁ ገበሬዎች ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ችግኞችን ወስደው ሠፊ ቦታ ላይ ነው የተከሉት። ስለዚህ የፓምፕ እና መሰል ድጋፎችን አድርገናል። እኛ በዋናነት ችግኙን እናቀርብላቸዋለን፤ የእንክብካቤ ስልጠና እንሰጣቸዋለን፡፡ ከዚህ በኋላ የማሳደጉና ወደ ጥቅም የመለወጡ ተግባር የገበሬዎቹ ይሆናል ማለት ነው፡፡
የዚህ ፕሮጀክት የመጨረሻ ግቡ ምንድን ነው?
ትልቁ ግብ የአካባቢ ጥበቃ ማድረግ ነው። የአካባቢ ስነ ምህዳር መጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን  ደግሞ ቀርክሃ ኢንዱስትሪያል ተክል እንደመሆኑ የስራ አድል እንዲፈጠርና ለአርሶ አደሩም ለአምራቹም የገቢ ምንጭ እንዲሆን ነው፡፡ በተለይ ወጣቶች የገጠር ኢንዱስትሪ  ላይ እንዲሰማሩ ቀርክሃ ሠፊ እድል ይፈጥራል፡፡ ይሄ ፕሮጀክት ምሳሌ እንዲሆንና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎቸ  እንዲተገበር ነው ሃሳባችን፡፡










Read 9179 times