Saturday, 14 May 2022 00:00

የሻይ ሳይሆን የቡና እረፍት ነው መባል ያለበት!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በአለም አቀፍ ደረጃ ቡና ከ50 ሀገሮች በላይ የሚመረት ሲሆን ከ120 ሚሊዮን በላይ የአለም ህዝብም ኑሮው የተመሰረተው በቡና ላይ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡  ኢትዮጵያ በዓለም ተወዳጅ የሆነው አረቢካ ቡና መገኛና ቡናን ለዓለም ያበረከተች ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ከ5 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ቡናን የሚያመርቱ ሲሆን በአጠቃላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኑሯቸው በቡና ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ቡና 5 ከመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ብሔራዊ ምርት የሚሸፍንና ከ25-30 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ነው፡፡
ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር አቦል፣ ቶና በረካ በሚል በየቀኑ በመላው ኢትዮጵያ በመጠጣት ዜጎች ሀሳባቸውን በመለዋወጥ የኢትዮጵያን ማህበራዊ ካፒታል/ Social Capital/ ከመገንባቱም በላይ ሀገራችንን ለአለም በማስተዋወቅ ረገድ የኢትዮጵያ ብራንድ እየሆነ ይገኛል፡፡ ስለዚህ
የእረፍት ሰዓታችን የሻይ እረፍት ከሚባል ይልቅ የቡና እረፍት ቢባል የተሻለ ነው፡፡  ምክንያቶቹም፡-
ለአለም ዲሞክራሲ እውቀትና ፍልስፍና  መስፋፋት ያደረገው አስተዋፅኦ
 እ.ኤ.አ. በ1964 በአሜሪካ የላብአደሩ ተደራዳሪዎች፣ “እርስዎ የቡና እረፍት ይስጡና የሚሠጡትን ሁሉ ያግኙ” በሚል መሪ ቃል ከባለሀብቱ ጋር እልህ አስጨራሽ ድርድር በማድረግ፣ “የቡና ዕረፍት” ተግባራዊ  ሆኖ የላብአደሩ አካላዊና አዕምሮአዊ ብቃት በቡና ዕረፍት ምክንያት በመጨመሩ የባለሀብቱ ምርትና ምርታማነት ማደግ ጀመረ፡፡
ቡና በተለይም የእውቀት የምክንያትና የፍልስፍና ዘመን ለሚባለው የ18ኛው ክ/ዘመን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል። በ18ኛው ክ/ዘመን የነበሩት እውቅ ፈላስፋዎች እንደ ቨልተር ሩሶ ያሉት በቡና ካፌ ውስጥ በመሰብሰብ የሃሳብ ፍጭት ያደርጉ ነበር፡፡ አዳዲስ ሃሳቦችንም ያፈልቁ ነበር፡፡ ፈላስፋዎቹም ቡናን ፉት ማለት ያዘወትሩ ነበር፡፡ ይህ “የእውቀት የፍልስፍና፣ የብርሃን” ዘመን ተብሎ የሚጠራው የ18ኛው ክፍለዘመን #የሥልጣን ምንጭ መሆን ያለበት ምክንያታዊነት ነው;  የሚል አቋም ተቀባይነት ያገኘበት ዘመን ነበር፡፡ ስለዚህ ቡና ለዲሞክራሲ ማደግና መስፋፋት ላደረገው አስተዋፅኦ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡
ቡና በዓለም ዲሞክራሲ እንዲበለጽግ ያደረገው አስተዋጽኦ መነሳት ያለበት ነው። ጀርገን ሀቨርማስ የተባለው የጀርመን ሶሽዮሎጂስትና የፖለቲካል ሣይንስ ምሁር፣ 18ኛው ክፍለ ዘመን የዲሞክራሲ ወርቃማው ዘመን ነበር ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ Public Sphere በሚለው ፅንሰ ሀሳቡ፣ በወቅቱ ሰዎች በቡና ካፌዎችና በመሣሠሉት ቦታዎች በመሰባሰብ ስለ ህይወታቸው፣ ስለ የጋራ ጉዳያቸው፣ ስለተለያዩ ሀሳቦች ያለ ምንም ገደብ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ በምክንያት ይከራከራሉ፡፡  መግባባት የተደረሰበት ስምምነትን በተግባር ያውሉታል፡፡ ሰዎች በቡና ካፌዎች ተሰብስበው ሲወያዩ የገንዘብ፣ የትምህርት፣ የመደብና የመሣሠሉት ልዩነቶች ግምት ውስጥ አይገቡም ነበር፤ ይላል ሀቨርማስ፡፡ እሱ እንደሚለው፤ መንግስታትም ተቀባይነት ለማግኘት ዜጐች በቡና ካፍቴሪያዎች ተሰባስበው የተወያዩበትንና ስምምነት የደረሱበትን ሀሳብ ተቀብለው ተግባራዊ ያደርጉት ነበር ይላል፡፡ በኋላ ግን ሚዲያ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጥናት በሚል ሰበብ ወካይ ያልሆነ የጥናት ውጤት በማቅረብ፣ ለህዝብ መወገን ትተው፣ ለባለሀብት በመወገን  Public Sphereን በግለኝነት ተኩት ይላል፡፡ ያም ሆነ ይህ ቡና ሀሣብ ለማፍለቅ በምክንያታዊነት ለመከራከርና ለማመን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ለዚህም እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡
ቡና የኢትዮጵያ መለያ (ብራንድ) መሆን አለበት
የብራንድ ባለሙያዎች፣ ሀገራት አንድ ብቻ ምርት (አገልግሎት) ልዩ መለያቸው /ብራንድ/ ቢሆን ከኢንቨስትመንትና ቱሪዝም አንጻር ተጠቃሚ ይሆናሉ ይላሉ። በዚህ ውድድር በበዛበትና የሸማች ዘመን በሚባልበት ወቅት ሸማቹን ለመያዝ አንፃራዊ ብልጫ ባለ ምርት ላይ ማተኮር አዋጭ ነው።  የሀገራትም ተሞክሮ የሚያሳየው ይኸንኑ ነው፡፡  አሜሪካ ሲባል “የዲሞክራሲ ቁንጮ” መሆኗ፣ እንግሊዝ ሲባል “ኘሪሚየር ሊግ”፣ ፈረንሳይ ሲባል “ወይኗ”፣ ግሪክ ሲባል “ፈላስፋዎቹ”፣ ግብፅ ሲባል “ፒራሚዶቿ” ይታወሳሉ፡፡
ከዚህ በመነሣት ኢትዮጵያ ሲባል ልዩ መለያዋ ቡና መሆን አለበት፤ ከቡና የተሻለ ምርት ወይም አገልግሎት የለም፡፡ በአለም ላይ ከ4 ቢሊዮን ስኒ በላይ ቡና  በየቀኑ ይጠጣል፡፡  በቢሊዮን የሚቆጠረው የቻይና ህዝብ እንኳን 1ዐ በመቶ የቡና ሱሰኛ ቢሆን የምናገኘውን የገበያ እድል እናስበው፡፡  ይህንን ለማድረግ ደግሞ በሀገራችን ለሚገኙ ቻይናውያን ሁሉ በተገኘው አጋጣሚ ስለ ቡና ማውራትና ከተቻለም በመጋበዝ  ማለማመድ ይቻላል፡፡  ስለዚህ የዕረፍት ሰዓታችንን የሻይ እረፍት ከማለት ይልቅ የቡና እረፍት ማለት ያዋጣናል ማለት ነው፡፡
ሀገራችን ያላት የዲኘሎማሲ ቦታ
አዲስ አበባ በአለም ላይ በዲኘሎማቲክ መቀመጫነት  በ3ኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ  መረጃዎች  ያሣያሉ።  በርካታ አለም አቀፍ ሁነቶችን ታስተናግዳለች፡፡ ታዲያ በእነዚህ ሁነቶች ጊዜ መርሃ ግብሩ “Tea Break”   ከሚል ይልቅ  “Coffee Break” ቢል ቡናን በነፃ ለማስተዋወቅ ይረዳል፡፡ በየቡና እረፍቱ ደግሞ በባህላዊ የቡና አፈላል ስርዓት በመጠቀም  ቡናን ማስተዋወቅ ይቻላል፡፡
ለኢኮኖሚ ባለው ፋይዳ
ቡና ለሀገራችን ከ25-30 ሚሊዮን ለሚደርስ ህዝብ የኑሮ መሠረት ነው፡፡ ከአጠቃላይ ብሔራዊ ምርት 5 በመቶውን ይሸፍናል፡፡ ከኤክስፖርት ገቢ ከ25-30 በመቶ በመሸፈን የአንበሣውን ድርሻ ይይዛል፤ ስለዚህ እውቅና ሊሠጠው ይገባል። በአለም ገበያ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ከቡና የተሻለ ምርት የለንም፡፡ የእኛ ቡና ጣዕም አለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ነው፡፡
ቡናና የአየር ንብረት ለውጥ
ጥናቶች እንደሚያሣዩት፤ ቡና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት አደጋ ከተጋረጠባቸው  ምርቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ቡና ከአለም እንዳይጠፋና የ120 ሚሊዮን ቡና ላይ የተመሠረተው የአለም ህዝብ ህይወት አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ኢትዮጵያ ውስጥ በቡና ላይ ኢንቨስት ማድረግ መፍትሄ እንደሆነ ተመራማሪዎች እያሳሰቡ ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የተጀመረው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ፖሊሲና አተገባበር ከቀጠለ፣ የቡናን ምርት በ4 እጥፍ ማሣደግ እንደሚቻል ተመራማሪዎቹ እማኝነታቸውን ሠጥተዋል፡፡
ስለዚህ ይህንን የአለም አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ ማለትም የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢነት ለአለም ማህበረሰብ የበለጠ ለማሣወቅ “የቡና ዕረፍት” በማለት ስለጉዳዩ የበለጠ ግንዛቤ በማስያዝ፣ ለመፍትሄዎቹ የአለም ማህበረሰብ የራሱን ሚና እንዲጫወት ማድረግ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ የቡና እረፍት መባሉ ለቡና ልማት ትኩረት ለመስጠት የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
ቡናን በመገኛ አገሩ አምርተን አለምን እናጠጣለን!

Read 1480 times