Saturday, 14 May 2022 00:00

"ላግዝሽ ቢሏት፤ መጇን ደበቀች"

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከኢራቅ ተረቶች አንዱ የሚከተለውን ይመስላል፡-
ከዕለታት አንድ ንጉሥ፣ በግዛቱ ዋና ከተማ ሳይታወቅ፣ በግዛቱ እየተዘዋወረ፣ ህዝቡ ምን እንደሚያወራ ለማዳመጥ እየሞከረ ነበር፡፡ በአንድ መስኮት አጠገብ እያለፈ ሳለ ሶስት ሴቶች ሲያወሩ ሰማ፡፡
አንደኛዋ - "ንጉሡን ለማግባት ብችል ግዛቱን ሁሉ ሊሸፍን የሚችል ምንጣፍ ወይም ስጋጃ እሰራለት ነበር” አለች፡፡
ሁለተኛዋ - "እኔ ደግሞ ንጉሡን ለማግባት ብችል መላ ሰራዊቱ በልቶ የማይጨርሰው ትልቅ ድፎ ዳቦ እጋግርለታለሁ" አለች፡፡
ሦስተኛዋ - “እኔ ደግሞ ንጉሱን ባገባ ሁለት ልጆች እወልድለታለሁ፡፡ አንደኛው ራሱ ላይ የብር ፀጉር፣  ሌላኛው ራሱ ላይ የወርቅ ጸጉር ያላቸው ይሆናሉ" አለች፡፡
ንጉሡ በሚቀጥለው ቀን ባባቶቻቸው በኩል ሴቶቹን ልጆች አስጠርቶ ተራ በተራ እያስጠየቀ፤  "በሉ ያላችሁትን ሰርታችሁ አሳዩኝ" አላቸው፡፡
የመጀመሪያዋ ስጋጃውን መስራት አልቻለችም፡፡
ሁለተኛዋ ዳቦውን ለመድፋት አቃታት፡፡
የመጀመሪያዋን ስለ ጉራዋ ማዕድ ቤት ውስጥ እንድትቀመጥ ፈረደባት፡፡ ሁለተኛዋን ደግሞ ኩሽና እንድትቀመጥ ቀጣት፡፡
ሦስተኛዋን ግን አገባት፡፡ ከ9 ወር በኋላ የብር ጌጥና የወርቅ ፀጉር ያላቸው መንታዎች ተወለዱ፡፡  እነዚህን  ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ልጆች ያዩት የንግስቲቱ እህቶች ቅናት ያዛቸውና፣ ከሞግዚቷ ተማክረው ወስዳ ጫካ እንድትጥላቸው አስደረጓት፡፡ በቦታቸውም ሁለት አሻንጉሊት ተካች፡፡ ንጉሱ የሆነውን ሲሰማ እቤቱ ፊት ለፊት ንግስቲቱን እስከ ጡቷ ድረስ ትቀበር አለ፡፡ መንገደኛው በድንጋይ እንዲወግራትም አስደረገ። ንጉሱ አንድ አሳ አጥማጅ አለው፡፡ የንጉሱ አሳ አጥማጅ ወንዙ ውስጥ አንድ ሳጥን ያገኛል፤ ሲይዘው ይከብዳል። ለሚስቱ ሄዶ ነገራት፡፡ ቤታቸው ወስደው ሲከፍቱት ምን የመሳሰሉ ባለ ወርቅና ባለ ብር ጸጉር ልጆች! ልጆች ስላልነበራቸው ሚስትየዋ በጣም ተደሰተችና ልታሳድጋቸው ወሰነች፡፡ ንጉሡ ወደ ሩቅ ሀገር ሊሄድ አስቧል፡፡  ሁለቱ ኩሽና ያሉት ልጆቹን ምን ላምጣላችሁ አላቸው፡፡
የመጀመሪያዋ - "በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስ!" አለችው፡፡
ሁለተኛዋ - "በአልማዝ የተሰራ የአንገት ሀብል!" አለችው፡፡
ሁለቱ እህታማቾች ቀጥለው ደረቷ ድረስ የተቀበረችውን እህታችንን ምን እንደምታመጣላት ጠይቃት አሉት፡፡
"አታላኛለችና ለእሷ አላመጣላትም" አለ፡፡
"ግድ የለህም ሚስትህ ናት፤ ለእኛም እህታችን ናት፤ ተባበራት!" አሉት፡፡ ወተወቱት፡፡ በመጨረሻም ተስማማና፤ "ላንቺስ ምን ላምጣልሽ?" አላት
“ምንም፤ በሰላም ሂድ፤ በሰላም ይመልስህ" አለችው፡፡
“በጭራሽ አንድ ነገር እዘዢኝ" አላት፡፡
“የትዕግስት አሻንጉሊትና የትዕግስት ቢላ አምጣልኝ” አለችው፡፡
“የምትሔድበት ሀገር እነዚህን ሁለቱን አታጣም፤ ከረሳህ የምትሳፈርበት ጀልባ  እሺ ብሎ አይንቀሳቀስም” አለችው፡፡
ንጉሡ ሩቅ ሀገር ሄደ፡፡ ንግዱን አሳካ፡፡ ነጋዴዎች በእንቁ የተንቆጠቆጠ ቀሚስና የአልማዝ የአንገት ሀብል እንዲገዙለት አደረገ፡፡ ከዛ ወደ ሃገሩ ሊመለስ መርከብ ላይ ወጥቶ “እንሂድ” አለ፡፡ ካፒቴኑ ግን መጥቶ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ መርከቡ አልሄድ ብሎኛል" ብሎ ሪፖርት አደረገ፡፡ ንጉሡ የረሳው ነገር ትዝ አለውና፤ የትዕግስት አሻንጉሊትና የትዕግስት ቢላዋ አስገዛ፡፡ የሸጠለት አንጥረኛ ግን አንድ ነገር አደራ አለው፤ ቃል አስገባው፡፡
“ንጉስ ሆይ፤ ለሚስትህ ስጦታውን ስትሰጣት፣ በሩ ስር ተደብቀህ የምታደርገውን ሁሉ እይ!”
ንጉሡ አንጥረኛው እንዳለው አደረገ፡፡ ለሁለት ሚስቶቹ ስጦታቸውን ከሰጠ በኋላ ግማሽ ወደ ተቀበረችው ሚስቱ ሄዶ ያመጣላትን ሰጥቶ ተደብቆ የምታደርገውን ማየት ጀመረ፡፡ ለአሻንጉሊቱ የሚከተለውን ተናገረች፡፡ እህቶቿ ልጆቿን እንደሰረቁባትና በቦታቸው አሻንጉሊቶች እንድታስቀምጥ ሞግዚቷን እንዳዘዟት ገለጠች፡፡ እስከዛሬ ድረስም ሀዘን ላይ መሆኗን እያነባች ተናገረች፡፡ እንዲህም አለች፡-
“የትዕግስት አሻንጉሊት ሆይ አንተ ትዕግስት ነህ! እኔም ትዕግስት ነኝ! እኔ በትዕግስት ምን ያህል  ስቃይ ተሸከምኩ? ምን ያህል መከራ ተቀበልኩ?!”
 አሻንጉሊቱ እየገዘፈ ሄደና ፈነዳ!
 ይህንን ያለችው ሦስተኛዋ ሚስት፤ "ውይ የትዕግስት አሻንጉሊት ሆይ ልብህ ፈነዳ!” ከዛም ቢላዋ አንስታ ራሷን ልትወጋ ስትል ንጉሥ ከተሸሸገበት ዘሎ አዳናት፡፡
 ከዚያም "ምነው ለአሻንጉሊቱ የነገርሽውን ለምን  ለእኔ አልነገርሽኝም?" ሲል ጠየቃት፡፡
"እህቶቼ ስላጠፉት እንዳትጎዳ"
ሁለቱን እህቶቿን ወደ እስር ቤት ላካቸው፡፡ ቀጥሎም የጠፉትን ሁለት ልጆቹን  እንዲፈልግ ህዝቡን በአዋጅ ጠየቀ፡፡ አዋጁ በመላ አገሪቱ ተሰማ፡፡ ይህን የሰሙት አሳ አጥማጁና ሚስቱ፣ ተመካክረው ልጆቹን ወደ ንጉሥ አምጥተው አስረከቡ፡፡ እንደ ሽልማትም ከቤተ መንግስቱ አቅራቢያ መኖሪያ ቤት ተሰርቶላቸው፤ ልጆቹንም በየጊዜው እያዩ ኖሩ!
****
ንጉስ እናስደስታለን ብለን ያለአቅማችን አንመኝ፡፡ የማይሆን ቃል አንግባ፡፡ የሚፀፀት ንጉሥ አያሣጣን። ስሕተቱን ሳይውል ሳያድር የሚያምንና የሚቀበል፤ ይቅርታ መጠየቅ የማያስፈራው መሪ፣ ባለስልጣን ፖለቲከኛ ይስጠን፡፡ እዚህ ላይ የታዋቂውን ገጣሚ አርክቴክና መሀንዲስ አሌክሳንድራ ፖፕን አባባል መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ “መሳሳት የሰው፤ ይቅር ማለት ግን የመለኮት ነው!” ይለናል፡፡ `To err is human; to forgive divine`
በየጊዜው፤ በማናቸውም ሂደቶች፣ እንቅስቃሴ ውስጥ እና ወቅት፣ ጥፋት መፈጠሩ እንግዳ ነገር አይሆንብንም፡፡ ዋናው ወሳኙ ነገር ምን ያህል መሳሳታችንን ልብ ብለናል? ምን ያህልስ ስህተታችንን አምነን ተቀብለናል? ለመታረምስ ምን ያህል ዝግጁ ነን? በተለይ ያጠፋነውን ካጠፋን በኋላ ጥፋቱን ያዩ ሰዎች እፀፁን ሲነግሩን መቆጣትና “ብቆጣም እመታሻለሁ፤ ብትቆጭም እመታሻለሁ!” ማለት ተአብዮ ነው፡፡ እንዲህ ያለ አመለካከት የአምባገነንነት እኩያ ነው! የአብዛኞቹ አምባገነኖች ዋነኛ ችግር ሰው ጤፉ መሆን ነው፡፡
ሁለተኛውና ከዚሁ ጋር በቅርብ የተሳሰረው ነገር የቅራኔ አፈታት ችግር ነው፡፡ የሚታረቅና የማይታረቅ ቅራኔ በአግባቡ መለየት ነው፡፡ (antagonistic and non-antagonistic contradiction እንዲል መፅሐፈ-ዲያሌክቲክስ፡፡) በትልቁም በትንሹም፣ በሚያስፈልገውም በማያስፈልገውም፣ ፖለቲካ በሆነውም ባልሆነውም ጉዳይ፣ መጨናነቅ ተገቢ አይደለም፡፡ በተለይም፣ “በጠብታ ውሃ ውስጥ ጎማሬ አየን” ከሚሉ ወሬ አራጋቢዎች አለመጠንቀቅ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ አንዳንዴ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚለውን አባባል አለመዘንጋት ከብልጥነት ይልቅ በብልህነት የሚፃፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገሮች ተርፏት ታበድራለች የሚለው ጉራ የማይገብዘንን ያህል፣ "ኢትዮጵያ አልቆላታል! በአፍጢሟ ተደፍታለች!” የሚለውን ጨለምተኛና “ሁሉን አውድም" (nihilistic) አስተሳሰብንም አራቱንም የሀገራችን ማዕዘናት እኩል  የሚነካ ፍሬ ጉዳይ አርገን ወስደነው፣ አሸባሪ ሊሆንብን አይገባም! ሚዛናዊ አመለካከት ቢያንስ "በአረብ-ቤት  ሚዛን እንዳንሸቀብ" ይረዳናል፡፡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተንታኞቻችን እንደምንም የባለ- ሱቅ ስሌት (shop- keeper’s analysis) ከሚባለው ጠለቅና መጠቅ ያለ፣ ለነገ ታሳቢነት ያለው ሂሳብ ቢቀምሩ መልካም ነው እንላለን፡፡
 የሥርአተ ማሕበራችንን ነገር፣ አንድም በሶሻል ዲሞክራሲ፣ አንድም  በሱታፌ ዲሞክራሲ (participatory democracy) ንፍቀ ክበብ ውስጥ ይሁነኝ ብለን እንመድበው ብንል እንኳን፤ ከነባራዊ ባህላዊ ስርአት ርቆ ያራቀ በመሆኑ፤ እቁብ እየከፈሉ የእድር ድንኳን እየተጋሩ፣ ጥዋ እየተጣጡ፣ ዘካና ምፅዋት እየሠጡ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲያድርብን ጥናቱን ይስጠን ማለቱ፤ ለጊዜው ከረሀቡም ከጠብና ግጭቱም፣ ከጦርነቱም እንኪያ-ስላንቲያና አርቲ ቡርቲ ይገላግለን ይሆናል!! ፓርቲዎችና ቡድኖች “የማይተማመን ባልንጀራ ወንዝ ለወንዝ ይማማላል” ከሚለው የተረት ማዕቀፍ ውጪ አይደሉም፡፡ “አንድነት ለጋራ ጠላት፤ ወዝግብና ንትርክ በጓዳና ቤት!” አይነት ነው ነገረ ስራቸው፡፡ ቀና ትችት እንደሌላቸው ሁሉ፣ በሀሳዊ- ውዳሴ የተሞሉ ናቸው፡፡ በዚያም ላይ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፤ "ካድሬው ሁሉ ሥልጣን በሸተተው ማግስት፣ አካሄዱ ሁሉ እንደ ድመት ኮርማ ይሆናል!” ያለው፤ ዛሬ “ፋሽን” ወደ መሆን አድጓል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ሁሉ ብርታቱን የሰጠው ሰው ጨክኖ፣ ልርዳችሁ፣ የአቅሜን ላዋጣ፣ ችግሩን አብረን እንፍታ፣ አሳትፉኝ፤ ቢላቸው እንኳ ጀርባቸው ሲሰጡ ይገኛሉ፡፡ "ላግዝሽ ቢሏት፤ መጇን ደበቀች" ማለት ይሄው ነው! ከዚህም ይሰውረን!


Read 10084 times