Saturday, 14 May 2022 00:00

ኢዜማ ቀጣይ መሪውን በጥብቅ የምርጫ ሥርዓት ይመርጣል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በመጪው ሰኔ 11 እና 12 ቀን 2014 ዓ.ም አንደኛ መደበኛ ጉባኤውን የሚያካሂደው ኢዜማ፤ ቀጣይ መሪውን ለየት ባለ የምርጫ ሥርዓት እንደሚመርጥ አስታውቋል፡፡
የመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ አዋቅሮ ከመጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያከናወነ መሆኑን ያመለከተው ኢዜማ፤ ቀጣይ መሪዎቹን አስቀድሞ እጩዎችን በመመዝገብና በተቀመጡ መስፈርቶችና መመዘኛዎች መሰረት በመለየት የሚመርጥ ይሆናል፡፡
በሀገሪቱ የፓርቲ ፖለቲካ ባህል አዲስ ነው በተባለው የመሪዎች ምርጫ ሂደት፣ አስቀድሞ ለመሪነት የተዘረዘሩ መስፈርቶችን አሟላለሁ የሚሉ የፓርቲው አባላት ራሳቸውን በእጩነት እንዲያቀርቡ በማድረግ፣ በነጥብ መዝኖ የተሻለ ነጥብ ያመጣ እጩ መሪ ሆኖ የሚመረጥ ይሆናል፤ብሏል ኢዜማ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ን ለመምራት ብቁ ነኝ ብሎ የሚወዳደር ግለሰብ ሊያሟላቸው ይገባል የተባሉ አምስት ያህል ግልፅ መመዘኛ መስፈርቶች የተቀመጡ ሲሆን፤ 16 ያህል በምርጫው ለመሳተፍ መሟላት አለባቸው የተባሉ ደንቦችም በግልፅ ተዘርዝረዋል።
እጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫው ለመሳተፍ ማሟላት ከሚገባቸው ደንቦች መካከል እድሜ ከ21 አመት በላይ፣ የፖለቲካ ልምድና በመስፈርቱ የተቀመጡ የትምህርት ማስረጃዎች ማቅረብ፣ በእጩነት የሚቀርብ ግለሰብ በህግ የመመረጥ መብቱ ያልተገደበ መሆን የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
በተጨማሪም በዚሁ ባለ 16 ነጥብ የምርጫ ደንብ፣ ተወዳዳሪዎች ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉበት አሰራር የተቀመጠ ሲሆን ማንኛውም ለመጨረሻ እጩነት ያለፈ ግለሰብ በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት የሚያወጣው ወጪ በራሱ የሚሸፈን ይሆናል። ማንኛውም እጩ ተወዳዳሪ የጉባኤው ቀን ከመድረሱ ሁለት ቀናት በፊት ምንም አይነት የምረጡኝ ቅስቀሳ ማካሄድ እንደማይችል የሚያመለክቱና ሌሎች ተያያዥ ደንቦችም ተካትተዋል።
የእጩነት መመዘኛ መስፈርቶችን በተመለከተም 5 ግልፅ መመዘኛዎች የቀረቡ ሲሆን አጠቃላይ ውጤታቸው ከ100 ነጥብ የሚደመር (የሚያዝ) ይሆናል።
የመጀመሪያው መስፈርት የትምህርት ደረጃ ሲሆን አንድ እጩ፣ ፒ.ኤች.ዲ እና ከዚያ በላይ ካለው 40 ነጥብ ይኖረዋል፣ ማስተርስ 30 ነጥብ፣ የመጀመሪያ ድግሪ 20 ነጥብ፣ ዲፕሎማ 15 ነጥብ፣ ሰርተፍኬት 10 ነጥብ ይያዝላቸዋል።
ሁለተኛው መመዘኛ መስፈርት የፖለቲካ ልምድ ሲሆን የስራ አስፈፃሚ አባል የነበረ 25 ነጥብ፣ ከኢዜማ በፊት በሌላ ፓርቲ ውስጥ ስራ አስፈፃሚ (ብሄራዊ ኮሚቴ )የነበረ 20 ነጥብ፣ በኢዜማ ወይም ቀደም ሲል የምርጫ ክልል አመራር፣ በልዩ ልዩ ኮሚቴ የተሳተፈ 15 ነጥብ  ይያዝለታል።፡
ሦስተኛው መመዘኛ መስፈርት የሥራ ልምድ ሲሆን በተለያዩ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኃላፊነት የሰሩ (የግል ተቋም የመሰረቱ፤ የዩኒቨርስቲ ዲን፣ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ መምሪያ ሀላፊ ወዘተ የነበሩ) 20 ነጥብ፣ ቡድን መሪ፣ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ዳይሬክተር ወዘተ የሆኑ 15 ነጥብ እንዲሁም ኦፊሰር እና መምህር 10 ነጥብ ይያዝላቸዋል።
አራተኛው መስፈርት የፆታና የአካል ጉዳተኛነት ማበረታቻን የተመለከተ ሲሆን ሴት አካል ጉዳተኛ 15 ነጥብ፣ አካል ጉዳተኛ ብቻ 10 እንዲሁም ሴቶች ተወዳዳሪዎች 10 ነጥብ ይያዝላቸዋል።
አምስተኛው መስፈርት ከሚወዳደሩበት የኃላፊነት ቦታ ጋር ያቀረቡት የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ሲሆን ከ5 ነጥብ ይያዝላቸዋል።
በዚህ ደንብ፣ መመዘኛ መስፈርት መሠረት፤ ራሳቸውን ለእጩነት የሚያቀርቡ ግለሰቦች ከሚያዝያ 25 እስከ ግንቦት 5 ቀን ብቻ ማመልከት የሚችሉ ሲሆን ለመጨረሻ ውድድር የተመረጡ ሦስት እጩዎች እስከ ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ይታወቃሉ ተብሏል፡፡
የመጨረሻዎቹ ሦስት እጩዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያከናውኑበት ጊዜ ከግንቦት 21 እስከ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ሲሆን መሪው የሚለይበት ቀንም የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ዕለት - ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ይሆናል ተብሏል።




Read 9085 times