Tuesday, 10 May 2022 00:00

ኪም ጆንግ ኡን በ4 ወራት 14ኛውን ሚሳኤል አስወነጨፉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አገራቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿን ከመቼውም በተለየ ፍጥነት እንደምታበለጽግና ለማንም እንደማትተኛ ባሳለፍነው  ሳምንት በአደባባይ የዛቱት የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን፣ ባለፈው ረቡዕ በ4 ወራት ጊዜ ውስጥ 14ኛውን ባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፋቸው ተነግሯል፡፡
ሰሜን ኮርያ ከመዲናዋ ፒንግያንግ አቅራቢያ ከሚገኘው ሱናን የተባለ አካባቢ ወደ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻዋ ያስወነጨፈችው በሰዓት 13 ሺህ 119 ኪሎ ሜትር ፍጥነት የመጓዝ አቅም ያለው ባለስቲክ ሚሳኤል፣ በፈረንጆች አመት 2022 አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ያስወነጨፈችው 14ኛው ሚሳኤል መሆኑን የዘገበው ሮይተርስ፤ ደቡብ ኮርያ በበኩሏ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀረውን የአዲሱ ፕሬዚዳንቷ ዩን ሱክ ዮል በአለ ሲመት ለማሳመር ተፍ ተፍ በምትልበት ወቅት የተፈጸመውን ይህን የሚሳኤል ሙከራ #ውጥረትን አባባሽ; ስትል በፍጥነት እንዳወገዘችው አስነብቧል፡፡
የደቡብ ኮርያ መንግስት ክስተቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ሰሜን ኮርያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያዥጎደጎደችው ያለው የሚሳኤል ማስወንጨፍ ድርጊት ለኮርያ ባህረ ሰላጤ ብቻ ሳይሆን ለአለማቀፉ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ስጋት ነው ሲል እንዳወገዘው የጠቆመው ዘገባው፣ አገሪቱ ከሰሜን ለሚቃጣባት ማንኛውም ጥቃት የከፋ የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ማስታወቁንም አመልክቷል፡፡
የጃፓን ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ማካቶ ኦኒኪ በበኩላቸው፤ ከምድር በ780 ኪሎ ሜትር ያህል ከፍታ 500 ኪሎ ሜትሮችን ያህል ያቆራረጠውን ይህን የሚሳኤል ማስወንጨፍ ድርጊት #በትዕግስት ሊታይ የማይገባው ጸብ አጫሪ ትንኮሳ; ሲሉ ያወገዙት ሲሆን፣ ሰሜን ኮርያ ባለፈው ወር ህዋሶንግ የተባለውን በግዙፍነቱ አቻ የማይገኝለት አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ማስወንጨፏንም ዘገባው አስታውሷል፡፡



Read 2631 times