Saturday, 07 May 2022 14:14

አርሂቡ ቻይና!

Written by  በስንታየሁ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

     ቡና ኢትዮጵያ ለአለም ያስተዋወቀችው ምርጥ ስጦታ ነው፡፡ ቡና የኢትዮጵያ ብራንድ ነው፡፡ ከቡና የተሻለ ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ ምርትና አገልግሎት ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ቡና ኢትዮጵያውያንን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የሚያስተሳስር ማህበራዊ ካፒታል ነው፡፡ ማህበራዊ ካፒታል ለሃገር ብልፅግና፣ ለዴሞክራሲ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። የማህበራዊ ካፒታል መበልፀግ በበኩሉ፤ ለሃገር ብልፅግና ተመልሶ ከፍተኛውን ሚና ይጫወታል፡፡
 በዚህ ውድድር በበዛበት የሉላዊነት ዘመን፣ ሃገራት አንፃራዊ ብልጫቸውን በመለየት ምርትን (አገልግሎትን) ብራንድ በማድረግ፣ ዜጎች ብራንዳቸውን ለማስተዋወቅ እንደ አንድ ሰራዊት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ከቡና የተሻለ ምርት ወይንም አገልግሎት የለም፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ቡና ከነዳጅ ቀጥሎ ከፍተኛ ግብይት የሚካሄድበት ሸቀጥ ነው፡፡ በዓለም ላይ በየቀኑ ከ3 ቢሊዮን ስኒ በላይ ቡና  ይጠጣል፡፡ ኢትዮጵያ በቡና ጥራት በዓለም የሚወዳደራት ቀርቶ አጠገቧ የሚደርስ ቡና አቅራቢ ሃገር የለም፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ እ.ኤ.አ. በ2014 ታዋቂ የሆኑ የቡና ኤክስፖርተሮች ተጠይቀው፣ ለኢትዮጵያ ቡና 25 ነጥቦች በመስጠት በአንደኛ ደረጃ ሲያስቀምጡት፣ ኬንያ በ12 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ፣ ኮሎምቢያ በ10 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ይሁንና በተዛባው የዓለም የንግድ ስርዓት ምክንያት ኢትዮጵያ ከቡና መጠቀም የሚገባትን ያህል ተጠቅማለች ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመፍትሄዎች መካከል በፍጥነት በማደግ ላይ ባሉት ሃገሮች በተለይም በወጣቶች ላይ አተኩሮ የኢትዮጵያን ቡና የማስተዋወቅ ሥራን አጠናክሮና በድግግሞሽ ማስቀጠል ነው፡፡
ዘኢኮኖሚስት እንደዘገበው፤ ቻይና የሻይ ተጠቃሚ ሃገር ብትሆንም፣ አሁን ቡና በመልመድ ላይ ናት፡፡ ወጣት ቻይናውያን ቡና ከሚጠጡት በላይ ቡና መሸጫ ሱቆችን ምስል ለመለዋወጥ አመቺ ሆነው አግኝተውታል ይላል፤ ዘገባው። የደቡብ ምእራብ ክፍለ ሃገር ዋና ከተማ በሆነችው ቹንዱ፣ ሃንግሻይ የቡና መጠጥ አሰራርን ስትሞክር አግኝቷታል። ትምህርቱ ቡና ከሚቆላበት እስከ ቡና ጠጪዎች መስተንግዶ ክህሎትን የያዘ ነው፡፡ ከአውሮፓ ቡና ላኪ ማእከላት ስለ ክህሎቱ ማረጋገጫ አግኝታለች፡፡ በ20ዎቹና 30ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ 7 ሴቶች የቡና መጠጫ ሱቅ ለመክፈት ትምህርቱን እየተከታተሉ ነው ተብሏል፡፡
የአሜሪካ የግብርና መምሪያ በበኩሉ፤ በ2020/2021 የቡና ፍጆታ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር 80  በመቶ በማደጉ  መልካም እድል እንዳለ ያሣያል ብሏል። የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቶማስ ጀፈርሰን፤ #ቡና የሰለጠነ ሰውና አገር መጠጥ ነው; ማለታቸው ይወሳል፡፡  በቻይና በመካከለኛና ከፍተኛ ከተሞች፣ የወጣቶች የቡና ተጠቃሚነት መጨመር የአባባሉን እውነተኛነት ያረጋግጣል፡፡
እስከ 1990ዎቹ (እ.ኤ.አ.) ድረስ በቻይና ቡና የሚጠቀሙት የውጪ ሃገር ዜጎች ብቻ ነበሩ፡፡ ያውም ማግኘት የሚቻለው በቅንጡ ሆቴሎች ብቻ ነበር፡፡ ሁኔታዎች መሻሻል ያሳዩት ስታር ባክስ በ1999 (እ.ኤ.አ) በቻይና አገልግሎቱን መስጠት ሲጀምር ነው፡፡ ስታር ባክስ ቡናን ለማለማመድ ወተትና ስኳር ቀላቅሎ በመሸጥ ነበር የጀመረው፡፡ እንደ የአለም የቡና ድርጅት መረጃ መሰረት፤ አሁንም ቢሆን በቻይና አማካይ የቡና ፍጆታ መጠን በአመት ለአንድ ሰው አምስት ስኒዎች ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአሜሪካ ወይንም በጃፓን ቡና ከሚጠቀመው አንድ ሶስተኛ ብቻ ማለት ነው፡፡ ይሁንና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ቻይናውያን ዘንድ ቡና መጠጣት ፋሽን እየሆነ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ስታርባክስ 3,800 የቡና መሸጫ መዳረሻዎች በቻይና አሉት፡፡ ይህ ደግሞ ቻይናን ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል፡፡
ስታቲስትዩ የተባለ የቢዝነስ ኢንተሊጀንስ ተቋም እንደሚለው ከሆነ፤ የተቆላ ቡና ገበያ በቻይና በየአመቱ አስር በመቶ እያደገ ነው። አሁን ግን ላኪንኮፊ ቤይጂንግን ማዕከል አድርጎ ተመሥርቷል፡፡ ከተቋቋመበት ከዛሬ ሁለት አመት ጀምሮ እስካሁን 2,300 መዳረሻዎችን ከፍቷል፡፡ ሜይ 17 ቀን 2019 በወጣው የስቶኩ የጨረታ ገበያ፣ 570 ሚሊዮን ብር ሰብስቦ፣ ዋጋውን ወደ 4 ቢሊዮን ዶላር አሳድጓል። የላኪን አስገራሚ እድገት በቻይና የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ መሆኑን ማሳያ ነው። ከእንግዲህ ቻይናውያን ቡናን እንደ ቅንጦት አያዩትም። ብዙዎቹ የላኪን ቡና መሸጫ ሱቆች ተጠቃሚዎች፣ በአእምሮ ስራ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍል ናቸው።  በጣም የሥራ ጫና ያለባቸው በመሆኑ ትእዛዝ የሚሰጡት በኦንላይን ነው፡፡
የሻይ እና የቡና ገበያ በቻይና የተለያዩ ናቸው፡፡ የሻይ ቤቶች ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ ቻይናውያን ሲዘወተሩ፣ የቡና መሸጫ ሱቆች ግን በወጣቶች ይዘወተራሉ። ወጣት ቻይናውያን የቡና መሸጫ ሱቆችን የሚጠቀሙባቸው ለማህበራዊ ትስስር ነው፡፡ ብዙዎቹ ቡና እየጠጡ ምስላቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ይለቃሉ፡፡
የኢኮኖሚስት ዘገባ እንደሚለው፤ በቻይና የቡና ገበያን ሰብሮ ለመግባት ዕምቅ እድሎች ያሉ ሲሆን  የቡና ጠቀሜታን የሚያስረዱ ማስታወቂያዎችንና የፕሮሞሽን ስራዎችን በትጋት መስራትን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ፡- ቡና መጠጣት የእድሜ ጣሪያን በ15 ዓመታት እንደሚጨምር በጥናት  ተረጋግጧል፡፡ የእድሜ ጣሪያ ደግሞ የፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል መገለጫዎች  ከሆነው የሰው ሃብት ልማት (human development index) አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ ቻይናውያን ቡናን በመጠጣት የሚያገኙትን ጥቅም (call to benefit) መሰረት ያደረገ መልእክት ቀርፀን ለቻይናውያን በማስተላለፍ፣ ወደ ቻይና ገበያ ሰብረን መግባት ለነገ የማይባል ሥራ ነው፡፡ አርሂቡ ቻይና!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2361 times