Print this page
Saturday, 07 May 2022 13:22

“በኢትዮጵያነት ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር አንደራደርም”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 • በከልል አደረጃጀት ላይ የተለየ ሃሳብ ይዘን መጥተናል
   • መሬት የህዝብና የዜጐች ነው ብለን እናምናለን
   • የተለየ የቋንቋ ፖሊሲ ቀርፀናል

                አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ በምስረታ ላይ ነው - “የኢትዮጵያ ዜጐች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት” ይሰኛል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠና አለማየሁ አንበሴ፣ ከፓርቲው የምስረታ አስተባባሪ ኢ/ር እንግዳወርቅ ማሞ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡ አዲሱን ፓርቲ እንተዋወቀው፡፡

             እስቲ በምስረታ ሂደት ላይ ስለሚገኘው ፓርቲያችሁ ጥቂት ይነገሩን?
አሁን ፓርቲያችንን እንደ አዲስ የምንመሰርተው ቢሆንም ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ግን የነበረ ፓርቲ ነው፡፡ በወቅቱ በነበረው መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች እውቅና ነፍጎን የቆየን ሲሆን አሁን የተሻለ ነገር መጥቷል ብለን ነው እንቅስቃሴ የጀመርነው፡፡ ፓርቲያችን በውስጡ ትልቅ ፅንሰ ሃሳብ ያለው፣ ሀገራዊነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ በህዝብ ፍፁም የስልጣን ባለቤትነት የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ ስያሜውም “የኢትዮጵያ ዜጐች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት” የሚል ነው። መርሁ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ ብቻ የሚመሰረት ፖለቲካን ማራመድ ነው፡፡
የፓርቲው የምስረታ ሂደት ምን ላይ ደርሷል?
ከምርጫ ቦርድ የመመስረቻ ሂደቱን የምናሳልጥበት የድጋፍ ደብዳቤ ካገኘን በኋላ፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ጀምረናል፡፡ በፀረ ሽብር ህጉ “ሽብርተኛ” ተብለው በተፈረጁ ድርጅቶች ውስጥ ተሳትፎ የሌላቸውን ዜጐች በሙሉ በፓርቲያችን ውስጥ በአባልነት የማሰባሰብ ስራ እያከናወንን ነው። አሁን ወደ ማጠቃለሉ እየሄድን ሲሆን ቀጣይ ተግባራችን ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ይሆናል፡፡
መቼ ለማካሄድ አቅዳችኋል?
በቅርቡ ጉባኤውን እናካሄዳለን፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ጉባኤውን ያካሄደበትን አራዳሽ እንዲፈቅድልን ጠይቀናል፡፡ እኛ ብልፅግናን አዳራሽ ስንጠይቅ፣ ብዙዎች ግር ሊላቸው ይችላል፡፡ በኛ ግንዛቤ ግን የብልፅግና ጉባኤ የተደረገበት አዳራሽ የህዝብ ንብረት ነው፡፡ ለብልፅግና ብቻ የሚያገለግልበት ምክንያት የለም፡፡ እኛም የመጠቀም መብቱ አለን፡፡ በዚህ መሰረት ነው የአዳራሽ ጥያቄውን ያቀረብነው ድንገት የማይሳካ ከሆነ ብለን ደግሞ ሆቴል ዲ አፍሪክንም ጠይቀናል፡፡
ፓርቲያችሁ የሚመራበት ርእዮተ ዓለም ምንድን ነው?
ለበራሊዝም ነው፡፡ ሊበራሊዝም ስንል ከሌሎች ለየት የሚያደርገን፣ በሀገራዊ እሳቤዎች የተቃኘ መሆኑ ነው፡፡ መሬት የህዝብና የዜጐች መሆን አለበት ብለን አናምናለን፡፡ በዚያው ልክ በተመረጡ የኢኮኖሚ መስኮች ላይ መንግሥት ጣልቃ መግባት አለበት የሚል እምነት አለን፡፡  ወደፊት ይፋ የምናደርገው ለየት ያለ የቋንቋ ፖሊሲ አዘጋጅተናል፡፡ በክልል አደረጃጀት ላይ የተለየ ሃሳብ ነው ይዘን የመጣነው፣ ፕሮግራማችንን ለህዝብ ይፋ ስናደርግ የሚገለፅ ይሆናል፡፡
ፓርቲያችሁ ሊያሳካቸው የሚሻቸው ግንቦች ምንድን ናቸው?
አንደኛ፤ ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን ማፅናት ላይ እንሰራለን፡፡ አንዳች መልካም ግብ ላይ ለመድረስም እንተጋለን፡፡ ስልጣን በጉልበት ሳይሆን በህዝብ ይሁንታ ብቻ የሚገኝበት ሀገር ለመፍጠር እንሻለን፡፡ ለዚህም ያለንን እውቀት ሁሉ ተጠቅመን እንታገላለን፡፡ ሀገሪቱ በትክክል የዜጐች መብት የሚረጋገጥባት እንድትሆን እንተጋለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት የነገሰባት፣ ኢትዮጵያ እንደትመሰረትም አበክረን እንታገላለን፡፡ የአገሪቱን ሉአላዊ ድንበር እናስከብራለን፡፡ እኛ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ከማንም ጋር አንደራደርም፡፡
በዋናነት በየትኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ነው የምትንቀሳቀሱት?
በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች አባላት አሉን፤ ስለዚህም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች -  በመላው ኢትዮጵያ እንንቀሳቀሳለን ማለት ነው፡፡ በጉባኤያችን ላይ ከ1500 በላይ አባላት ይሳተፋሉ፡፡


Read 1135 times
Administrator

Latest from Administrator