Saturday, 07 May 2022 13:19

ጋዜጠኞችን ከህግ ውጭ መያዝም ሆነ ማሰር እንዲቆም ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ደብዛ እስካሁን አልተገኘም


            “የቀድሞ የኢሳት” ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፤ ባለፈው እሁድ ሚያዝያ  23 ቀን 2014 ዓ.ም የሲቪል ልብስ በለበሱ የፀጥታ ሀይሎች ከመኖሪያ ቤቱ “ለጥያቄ ትፈለጋለህ በሚል ከተወሰደ በኋላ የትና በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ  አለመታወቁ ያሳስበኛል” ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኋን ባለሞያዎች ማህበር ገለፁ።
ማህበሩ፤”ጋዜጠኛን ከህግ ውጭ ሰውሮ ማቆየት ይቁም “በሚል ርዕስ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤”የማህበራችን መስራች አባል የሆነው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ታፍኖ ተወስዶ እንዲሰወር የተደረገው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ሳምንት በሚከበርበት ወቅት መሆኑ መንግስት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ጥቃት እንደከፈተ ያስቆጥረዋል ብሏል፡፡ “ለጊዜው ከህግ አግባብ ውጭ መንግስትና በመንግስት ስም የሚንቀሳቀሱ ህገ ወጥ ሃይሎች፣ በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት የህዝብ አይንና ጆሮ የሆነውን ሚዲያ ሊያሸማቅቀው ቢችልም፣ ድርጊቱ ይዋል ይደር እንጂ ራሱን መንግስትን ዋጋ የሚያስከፍለው መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡” ሲልም አሳስቧል ማህበሩ፡፡
“ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ያጠፋው ቢኖር እንኳን እንደማንኛውም ተጠርጣሪ በህግ ቁጥጥር ስር ሊውልና ዳኝነት ሊሰጠው ሲገባ፣ ከተያዘበት ቀን ጅምሮ የት እንደሚገኝ እንኳን ሳይገለፅ ቀናትን ማሳለፉ የመብት ጥሰት ብቻ አይደለም ያለው መግለጫው፤ ይልቁንም መንግስት ይህ ያልተገባ አደገኛ አዝማሚያ በጋዜጠኞች ላይ  እንደመብት የቆጠረው ያስመስለዋል፡፡” ሲል ወቅሷል፡፡
በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ማናቸውም ግልፅና ህቡዕ ጥቃቶች እንዲቆሙ ደጋግሞ ማሳሰቡን ያስታወቀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባሙያዎች ማህበር፤ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ለምን በዚህ ሁኔታ እንደታሰረ፣የት እንደሚገኝና የተያዘበት ምክንያትም በሚመለከተው ወገን  በይፋ እንዲገለፅ በአፅንኦት ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ረቡዕ የተከበረውን የፕሬስ ነፃነት ቀን ምክንያት በማድረግ ባወጣው መግለጫ፣የጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች  እስር እንዲሁም በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን መልከዓ ምድር  ላይ ተግዳሮት የሚሆኑ እንደ ግብር፣ የፕሮዳክሽን ወጪዎች፣ የመረጃ ተደራሽነት የማደራጀት አቅምና የመሰረተ ልማት የመሳሰሉ ጉዳዮች እንደሚያሳስበው አስታውቋል፡፡  ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በመግለጫው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በቅርቡ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ሃይሎች ከቤቱ ከተወሰደ በኋላ ደብዛው የጠፋው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ የት እንዳለ ጉዳዩ በእጅጉ ያሳስባል ብለዋል።
የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ አዲሱ አልጋው፤ደንበኛቸው እስካሁን ፍ/ቤት አለመቅረቡንና ታስሮ የሚገኝበትን ስፍራ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት እስዳልተሳካ ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
“በከባድ ወንጀል የተጠረጠሩ ወይም እጅ ከፍንጅ የተያዙት ተጠርጣሪዎች ካልሆኑ በቀር በመርህ ደረጃ ፖሊስ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማንኛውንም ሰው ማሰር አይችልም” ያሉት ጠበቃው፤ “በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍ/ቤት መቅረብ አለበት” ብለዋል ህጉን ጠቅሰው፡፡

Read 13141 times