Saturday, 30 April 2022 14:45

ለመጨረሻ ዙር የለዛ አዋርድ ሽልማት ያለፉት ዕጩዎች ተለዩ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


            የመጀመሪያው ዙር የለዛ አዋርድ የሽልማት ድምጽ ለአንድ ወር ሲካሄድ መቆየቱንና ለመጨረሻው ዙር ያለፉ እጩዎች መለየታቸውን የለዛ አዋርድ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ አስታወቀ።
WWW.lezashow.com ላይ በተሰበሰበው ድምጽ ለቀጣዩና ለመጨረሻው ዙር ያለፉት ሥራዎችና ሙያተኞች የተለዩ ሲሆን በዚህም መሰረት የዓመቱ ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም በሚለው ዘርፍ “የእግር እሳት”፣ “ዘመን”፣ “ዘጠነኛው ሺህ”፣ “እረኛዬ” እና “ሚዛን” ሲያልፉ በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዝን ፊልም ተዋናይት ዘርፍ ድርብ ወርቅ ሰይፉ ከ”እረኛዬ” ሜላት ወልዴ ከ” ዘጠነኛው ሺህ”፣ ሳያት ደምሴ ከ”እረኛዬ”፣ መስከረም አበራ ከ”የእግር እሳት” እንዲሁም ገነት ንጋቱ ከ”ሚዛን” ተመርጠዋል።
የዓመቱ ምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ተዋናይ በሚለው ዘርፍ ደግሞ፣ ሰለሞን ቦጋለ ከ”እረኛዬ”፣ ኤሊያስ ወሰን የለህ ከ”የእግር እሳት”፣ ሚሊዮን ብርሃኔ ከ”ዘጠነኛው ሺህ”፣ እንዲሁም አበበ ተምትም ከ”ዘጠነኛው ሺህ” ወደ መጨረሻው ዙር ማለፋቸው ታውቋል። የዓመቱ ምርጥ ተዋናይት በሚለው ዘርፍ ዘሪቱ ከበደ (ወጣት በ97)፣ ማርታ ጎይቶም (ኪያ)፣ እድለወርቅ ጣሰው (ያራዳ ልጅ 5)፣ ሀና ፈቃዱ (በአንድ ቀን)፣ መስከረም አበራ (እንሳሮ) ሲመረጡ፣ ምርጥ ተዋናይ በተሰኘው ዘርፍ ደግሞ ሄኖክ ወንድሙ (ከርቤ) ዓለማየሁ ታደሰ (ግራና ቀኝ)፣ አማኑኤል ሀብታሙ (እንሳሮ)፣ ቸርነት ፍቃዱ (ኪያ)፣ አለምሰገድ ተስዬ (ያራዳ ልጅ 5) በተሰኙት ፊልሞች ተመርጠዋል ተብሏል።
የዓመቱ የሙዚቃ አልበም በተሰኘው ዘርፍ ተወዳድረው ወደመጨረሻው ዙር ያለፉት ደግሞ የመሰሉ ፋታሁን “አትሽሺ ጀምበር”፣ የጥላሁን ገሰሰ “ቆሜ ልመርቅሽ”፣ የዳዊት ጽጌ “የኔ ዜማ” የሀጫሉ ሁንዴሳ “ማሊማሊሳ” እና የገላና ጋሮምሳ “ባሊ” ሲሆኑ፣ የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ በሚለው ዘርፍ ደግሞ የሀይሌ ሩት “ላይቻል የለም”፣ የጥላሁን ገሰሰ “ቆሜ ልመርቅሽ”፣ የመሰሉ ፋታሁን “ወይ ልምጣ ወይ ምጣ”፣ የዳዊት ጽጌ “እትቱ” እና የፀዲ “ሰበበኛ” ተመርጠዋል።
የዓመቱ ምርጥ ፊልም በተባለው ዘርፍ “የፍቅር ጥግ”፣ “ኪያ”፣ “ወጣት በ97” እና እንሳሮ ሲመረጡ ምርጥ አዲስ ድምጻዊ በሚለውም ዘርፍም እንዲሁ እጩዎች ተመርጠዋ። ከ2011 ሰኔ 30 እስከ 2013 ሰኔ 30 ድረስ የተሰሩ የሁለት ዓመት ስራዎች የሚሸለሙበት “ለዛ አዋርድ” ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በሂልተን ሆቴል የሚከናወን ሲሆን በባላገሩ ቴሌቪዥንና በለዛ ሾው የዩቲዩብ ቻናል በቀጥታ ስርጭት ይተላለፋልም ተብሏል።


Read 1341 times