Saturday, 30 April 2022 13:52

እርክክብ ያልተደረገልን ትውልድ

Written by  ዮናስ ታረቀኝ
Rate this item
(1 Vote)

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ


              እኛ ካለፈው ያልተሳሰርን፣ እርክክብ ያልተደረገልን የለብ ለብ ትውልድ ነን። እድለ ቢስ፣  ሀገር አልባና ሽኝት ያልተደረገለት ትውልድ። ፀሐያችን ሾጣጣ፣ ፍቅራችን ጨካኝ፣ ወጣትነታችን ወጣት አልባ። ድንበር የሌለን፣ ስሜታችን የታፈነና ከለላ ያጣን ትውልድም ነን። ከህጻን አልጋችን ላይ ተገፍትረን የሚንቁን ባዘጋጁት ዓለም ውስጥ የተጣልን። ያም ሆኖ የእዚህ ዓለም መንጠቆ ይህንን ዓለም ሲዞረው፣ ልባችንን የሚይዝልን አንዳች አምላክ ያልተሰጠን። በመሆኑም አምላክ አልባ የሆንን። ምክንያቱም እኛ  የኋላውን ያልተረከብን፣ ትኩረት የተነፈግን  ትውልድ ነን።    
አረካካቢዎቻችን እግሮቻችንና ልቦቻችን አንዴ እቶን በሚተፉ፣ አንዴ ደግሞ በሰው ቁመት ልክ በረዶ በሚጋግሩ ጎዳናዎች ላይ እንዲንቀዋለሉ እያደረጉ ሽኝት ያልተደረገለት ትውልድ አደረጉን። ትስስር የሌለን ትውልድ ነን። ቅብብሎሽ ያላየን፣ ያልተፈቀደልንም። ምክንያቱም መንገድ በሳቱ እግሮቻችን የሚንከራተተው ልባችን ላይ ሸፍጥ ስለሚሰራ።
የተረከብነው አንዳች ነገር የለም።  ጀግንነታችሁ አልተዋሃደንም፣ ስልጣኔያችሁ ቆሞ እንደቀረ ነው። ባህላችሁ አልተጋባንም። እምነታችሁ አልደረሰንም። ኩራታችሁ አንገታችንን አስደፍቶናል። እውቀታችሁ አልጎበኘንም። አንድነታችሁ አላስተሳሰረንም።
አረካካቢዎቻችን ከእናንተ ያስረከቡን አንዳች ነገር የለም። በጥላቻ ተሞልተናል፣ ዘረኝነት ያንዘረዝረናል። ጽንፈኝነታችን እስከ አጽናፍ ነው። እምነታችን የከንቱ ከንቱ ሆኗል። ሰው መሆን አቅቶናል። ማሰብ ተስኖናል።
 የተረከብነው ምንም የለም። ተጋድሏችሁ መበሻሸቂያ፣ እምነታችሁ መሳለቂያ፣ ሥራችሁ የተናቀ፣ ቋንቋችሁ መደናቆሪያ፣ ንግሥናችሁ ጥፋት፣ ጥበባችሁ የማይረባ ሆኗል።
አረካካቢዎቻችን ያለፈውን እየኮነኑ፣ ሲያሻቸው እያፈረሱ፣ በል ሲላቸው እያንቋሸሹ፣ ካለፈው ትውልድና አስተሳሰቡ ጋር አንዳች ትሥሥር እንዳይኖረን አድርገዋል። እርክክብ ያልተደረገለን ዝም ብለን የምንቀዋለል፣ መነሻችንንም መድረሻችንንም  የማናውቅ፣ ሀገር ሲባል የማይሞቀን፣ ሀገር ሲባል የማይበርደን፣ ጎጥ ስንባል ዘራፍ የምንል ትውልድ ነን።
የቱን ማንሳት የቱን መጣል እንዳለብን የማናውቅ። በመንጋ እንድናስብ የተገደድን፣ እውነትና ውሸት የተደበላለቀብን ምስኪን ግራ የገባን ትውልድን ነን።  በዓለም ፊት ከፍ ያደረጋችሁ መንፈሳችሁ ያልተጋባብን፣ ሰባራ ትውልድ።
ልባችሁ ደካማ ስለሆነ ነው እንዳትሉን። ልባችን ድምጽ የለውም። ምክንያቱም ስለ እርክክብም ሆነ ስለ ሽኝት የሚያውቀው ነገር ስለሌለ። ልባችን በተደረገልን እያንዳንዱ አቀባበል ይደማል፣ ያዝናል ያለቅሳል።
ቢሆንም ግን ደራሽ ትውልድ ነን። ምናልባት በአንድ አዲስ ኮከብ ላይ፣ አዲስ ሕይወት ላይ በምላት የተወለድን ትውልድ እንሆናለን። ከአዲስ ፀሐይ ስር፣ በአዲስ ልብ  በምላት የተወለድን። ምናልባት ለአዲስ ፍቅር፣ ለአዲስ ሳቅ። ለአዲስ አምላክ በምላት የተወለድን።
እርግጥ እርክክብ ያልተደረገልን ትውልድ ነን፣ ነገር ግን ሁሉም መዳረሻ የእኛ እንደሆነ እናውቃለን።
ነሻ ሃሳብ - ቮልፍጋንግ ብሮሸርት፣ "GENERATION OHNE ABSCHIED" (1947)

Read 1414 times