Saturday, 30 April 2022 13:41

ያ’መት በዓል ማግስት ትእይንቶች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የሞላ ሽንት ቤት
ጭር ያለ ቤተሰብ
የተጠረገ ድስት፥ ድርቅ የመታው ሞሰብ፥
ያደፈ ቄጤማ
በበግ በሰው እግር ፥የተደቀደቀ
ወዙ ባንድ ሌሊት፥ ተመጦ ያለቀ
መጥረጊያ ሚጠብቅ ፥ወድቆ ተበታትኖ
ትናንት ጌጥ የነበር፥ ዛሬ ጉድፍ ሆኖ፥
የተወቀጠ ፊት ፥ የነጋበት ድንገት
በዳንኪራ ብዛት፥ወለም ያለው አንገት ፡ :
የዞረበት ናላ ፥ጌሾ ያበከተው
እንኳንስ መገንዘብ፥ መጀዘብ ያቃተው ::
የወለቀ ወገብ፥ የዛለ ትከሻ
መኪና ይመስል፥ ብየዳ የሚሻ ::
የጠጅና የጢስ ፥ድብልቅ እስትንፋስ
ከሆድ ሸለቆ ውስጥ፥ የታፈነ ነፋስ
ባንጀት የታሰረው
እንደተከበበ አመጸኛ ሽፍታ፥ መውጫ የቸገረው ፥
የማይፈካ ሰማይ፥ የማይዘንብ ደመና
በላባና በፈርስ፥ ያደፈ ጎዳና
በበግ የራስ ምላስ የተልከሰከሰ
የጠገበ ውሻ
በመንፈቅ አንድ ጊዜ ፥ አጥንት የቀመሰ ፥
ሀንጎበር ያዛገው ፥ መሂና አሽከርካሪ
እግረኛ አስደንባሪ
በከፊል የነቃ፥ በከፊል የተኛ
ከሱ የማይሻል፥ የመኪና እረኛ
ካውራ ጎዳናው ዳር፥ ቆሞ ሚያንቀላፋ
ድብርትን ባናቱ፥ እንደቆብ የደፋ
….
የተድላ ማገዶ
ላጭር ጊዜ ነዶ
ላጭር ጊዜ ደምቆ
ላጭር ጊዜ ሞቆ
አመዱ ብዙ ነው ፥ አያልቅም ተዝቆ፤
(አዳምኤል ከተሰኘው መድብል የተወሰደ)

Read 1335 times