Tuesday, 26 April 2022 00:00

የሁለት ጄነራሎች ወግ... ጄነራል ፓቬል ግራይቼፍ እና ጄነራል አበባው ታደሰ

Written by  ጌታሁን ሔራሞ
Rate this item
(1 Vote)

  ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ
     የፖለቲካ አይዲዮሎጂን በተመለከተ የአንድ ሀገር መከላከያ ገለልተኛ መሆን እንዳለበት የማያምን አለ ብሎ መገመት አይቻልም፤ ልክ ነው ገለልተኛ መሆን አለበት። ነገር ግን ከሀገራት ታሪክ አንፃር መከላከያ ከፖለቲከኞቹ ሽኩቻና አይዲዮሎጂ ራሱን ለማግለል ጥረት ማድረጉ እውን ቢሆንም፣ ሰለባ ከመሆን ይተርፋል ማለት አይቻልም። የአያሌ ሀገራት የመከላከያ ኃይል የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ሰለባ (Victim) ሆኖ ያውቃል።
ከታሪክ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ በሶቪየት ሕብረት የኮሚኒዝም አይዲዮሎጂ ተንኮታኩቶ፣ አዲስ በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ አይዲዮሎጂ ብቅ ባለበት ቅፅበት፣ የታላቋ ሶቪየት ሕብረት ጦር የሚይዘውንና የሚጨብጠውን አጥቶ ነበር። የሶቪየት ሕብረትን አንድነት በሚያቀነቅኑ በእነ ሚካኤል ጎርባቾቭ እና የሩሲያን ብሔርተኝነት በሚያቀነቅኑ በእነ ቦሪስ የልሲን መካከል በነበረው ፍትጊያ፣ በቁጥር በአብዛኛው ስላቫክና ሩሲያዊ የሆነው የሶቪየት ጦር ሚናውን መለየት በእጅጉ ቸግሮት ነበር። The fact that the defense is believed to be neutral to political ideology doesn’t mean that it will be safe to be the victim of the ideological war between the elites!
ከላይ ባስቀመጥኩት ሐሳብ ዙሪያ “Eugene B Rumer” የተባለ ፀሐፊ “The Ideological Crisis in the Russian Military” በሚል ርዕስ እጥር ምጥን ያለ ባለ 27 ገፅ ሪፖርት እ.ኤ.አ በ1995 ፅፎ ነበር። ይህ ጥናታዊ ፅሁፍ አማዞን ላይ በ7 ዶላር የሚሸጥ ቢሆንም ከጎግል ላይ በፒዲኤፍ ፎርማት ስለሚገኝ በነፃ ማውረድ ይቻላል። በዚሁ ሪፖርት ውስጥ በሶቪየት ሕብረት መፈራረስ ወቅት የፖለቲካ አይዲዮሎጂው ለውጥ የመከላከያውን አቋም የቱን ያህል ተፈታትኖት እንደነበረ የተቀመጠው እንደዚህ ነበር፦
“In the absence of a new ideological paradigm, history, inextricably tied to nationality and ethnicity, was the only place to begin the search for new ideological reference points. For the predominantly Slavic and largely Russian ex-Soviet officer corps, no historical roots and military traditions exist other than those of the Soviet Army and its predecessor, the Imperial Russian Army.”
እናም የ”Eugene B Rumer” ሪፖርት ዋና ማጠንጠኛ ሐሳብ የሶቪየት ሕብረትን መፈራረስ ተከትሎ ቀደም ሲል የሶቪየት ጦር አባላት የነበሩ ሩሲያዊ የመከላከያ ኃይል አባላት በአይዲዮሎጂው ለውጥ ነውጥ ወቅት የገጠማቸውን አማራጮች የሚያመላክት ነው፤ አማዞን የሪፖርቱን ገለፃ እንደዚህ በማለት ነው ያስቀመጠው፦
“This report addresses the issue of Russian nationalism in the Russian military and examines the ideological choices available to the military institution in the aftermath of the Soviet breakup.”
የሶቪየት ሕብረት የመፈራረስ ጦስና መዘዝ እዚያው በሶቪየት ግዛቶች ተጀምሮ እዚያው የሚጠናቀቅ አልነበረም፤ ከሶቪየት ሕብረት መፈራረስና ከነጎርባቾቭ መፈንቅለ መንግስታዊ መፈንገል በኋላ የወቅቱን የሩሲያውን መሪ ቦሪስ የልሲንን በጣም ያሳስባቸው የነበረው የመከፋፈል ውሽንፍሩ ወደ ራሺያም ግዛቶች መዛመት ነበር።
ይህን ውሽንፍር በማራገብ ረገድም የብሔርተኛ ኤሊቶች ሚና ከፍተኛ ነበር። በወቅቱ ከቦሪስ የልሲን ጎን የነበሩና እ.ኤ.አ ከ1992-1996 የራሺያ አርሚ ጄኔራልና የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩ ጄኔራል ፓቬል ሰርጌይቪች ግራይቼፍ (1948 – 2012) የፖለቲካ ልሂቃኑ ሚሊተሪውን ለመከፋፈል የሚያደርጉት ሸርና ሴራ በእጅጉ አሳስቦአቸው እንደነበረ ከላይ በጠቀስኩት ሪፖርት የተቀመጠው በዚህ መልኩ ነበር፦
“General Grachev’s repeated appeals to the country’s competing political elite and factions not to involve the military in their struggles may be an implicit admission of his own lack of faith in the institution’s cohesion and his fear of its ultimate disintegration in the event of such involvement.”
እናም በቅርቡ በሀገራችን የመከላከያ ኃይል አባላት የማዕረግ ዕድገትን ተከትሎ በኢቲቪ ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት ምክትል ኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል አበባው ታደሰም፣ የብሔር ፖለቲከኞች መከላከያውን ከማዋከብ እንዲታቀቡ የሰጡት ማስጠንቀቂያ፣ ከሩሲያው ጄኔራል ግራይቼፍ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ ጄኔራል አበባው በዚሁ ገራሚ ማብራሪያቸው፣ መከላከያ ከፖለቲካ አይዲዮሎጂ ገለልተኛ እንደሆነ ቢነገርም ሰላባ ከመሆን ግን እንደማይተርፍ በግልፅ አስቀምጠዋል። ለምሣሌ ጄኔራል አበባው የደርግ ወታደር መበታተን የአይዲዮሎጂ ለውጥ ውጤት መሆኑን አስምረዋል፣ በቅርቡ በትግራይ ጦርነት መከላከያው የከፈለው ዋጋ በቀጥታ በኤሊቶቹ መካከል በተፈጠረው የዘር ፖለቲካ መዘዝ እንደሆነ አስቀምጠዋል።
The defense was the victim of the ethnic elites conflict. በተለይም በመከላከያ ውስጥ የብሔር ክፍፍል ቦታ እንደሌለውና ይህን የብሔር ካርድ መጫወት የሚፈልግ ሜዳውን እንዲቀይር በምሬት ያስቀመጡት እንደዚህ በማለት ነበር፦
“አማራ ነኝ ኦሮሞ ነኝ ካልክ፣ እሱ ሰፊ ሜዳ አለ መጫወቻ፤ እዚያው ይጫወት፤ እዚህ ላይ ጨዋታ የለም። ይሄን እንደ መከላከያ መርሮን ነው የምንናገረው፤ ለምን ካልከኝ ይሄ የዘር ጦስ ነው እኛን እየጠበሰ ያለው፤ ወንድሞቻችንን እያጣን ያለነው። ፖለቲከኛው ፊደል የቆጠረው ዞር ብሎ፣ ቆም ብሎ፣ ራሱ ጋ ቆሞ የሚያስብ፣ ኢትዮጵያዊነቱን የሚፈልገው ከሆነ፤ ይሄንን በደንብ አድርጎ ማሰብ መቻል አለበት። በዘር የተጠበስነው እኛ ነን። ዋጋ የከፈልነው እኛ ነን፤ ሕይወታችንን ያጣነው እኛ ነን። የተንከራተትነው እኛ ነን። የቀድሞ የደርግ ወታደር በዚህ ሂሳብ እኮ ነው ተበትኖ ለማኝ ሆኖ የቀረው። አሁን ያለው ደግሞ አሁን የምናካሄደው ጦርነት cause ምንድነው? ዘር አይደለም እንዴ? ስለዚህ ኢትዮጵያዊነታችን ላይ ምንም አንደራደርም።”
ለኔ ይህ የጄኔራል አበባው ታደሰ ማብራሪያ ምናልባትም በቀጣዩ ዘመን በታሪክነት የሚጠቀስ ነው። It strictly indicates how the defense is victimized by the crisis of elite political ideology. በተለይ ኤሊቱ የዘር ፖለቲካ ዕሳቤውን ቆም ብሎ እንዲፈትሸው ያስተላለፉት መልዕክት የቀውሱን ምንጭ የሚጠቁም ነው። ጄኔራል አበባው እንደጠቀሱት፤ በሌላው ሜዳ የብሔር ፖለቲካ ካርድ ሰፊ ሜዳ እየተሰጠው በተቃራኒው መከላከያው በብሔር እንዳይከፋፈል ማስገንዘቢያ መስጠት ምንጩን ትቶ ለወንዙ ትኩረት እንደመስጠት ይቆጠራል። የጄኔራሉን ምክር እኛም እንድገመው፦
“ፖለቲከኛው ፊደል የቆጠረው ዞር ብሎ፣ ቆም ብሎ፣ ራሱ ጋ ቆሞ የሚያስብ፣ ኢትዮጵያዊነቱን የሚፈልገው ከሆነ፣ ይሄንን በደንብ አድርጎ ማሰብ መቻል አለበት።”
መልካም ቀን!



Read 1521 times