Saturday, 23 April 2022 14:33

የሸዋሮቢትና የአጣዬ እጣ ፈንታ ምንድን ነው?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 በኢትዮጵያ ያለውን የሰላም ሁኔታ የሚከታተል “ኢትዮጵያ ፒስ ኦቭዘርቨር” የተባለ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት፣ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት የአራት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ በተደራጁ ሃይሎች 2ሺ827 ጥቃቶች  በመላው ኢትዮጵያ የተፈጸሙ ሲሆን በዚህም 15ሺ604 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 7ሺ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል። በአራቱም ዓመታት በተደጋጋሚ ችግር ውስጥ ሲወድቁ የምናገኘው ደግሞ ሸዋ ሮቢትና በአካባቢው የሚገኙ ወረዳዎች ናቸው። የኤፍራታ ግድም ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችው አጣዬም  ቀዳሚዋ ተጎጂ ናት።
መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም ግጭቱን በሚፈልጉ አካባቢውን ለማጥፋት ስራዬ ብለው በተነሱና በተዘጋጁ ሰዎች አንድ የአጣዬ ነዋሪ ሰው ተገደሉ። በእሳቸው ሞት የተቀሰቀሰውን ጠብ ለማብረድ ትግል በሚደረግበት ወቅት በአካባቢው በሚገኙ ድሃ አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት ተከፈተ። ጥቃቱ ሰንበቴን፣ ጅውሃን፣ ካራቆሬንና ሌሎችንም ከተሞች አዳርሶ፣ ወደ ውስጥ እስከ አንጾኪያ ድረስም ዘልቆ ነበር። በዚህ ጥቃትም 300 ገደማ ሰዎች ህይወታቸውን አጡ። አጣዬ ከተማም እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባት። ከሞት የተረፉት ነዋሪዎቿ በአቅራቢያቸው ወደሚገኙት ደብረ ብርሃን፣ ደሴና  ኮምቦልቻ ሸሹ።
አጥቂዎቹ “ኦነግ ሸኔ” እየተባለ የሚጠሩ ቡድኖች ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአካባቢው ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ከአዲስ አበባም ይሁን በቅርብ የሚገኝ  የደህንነት ተቋም የፌደራል ፖሊስ ወይም የመከላከያ ሃይል ተወርውሮ ህዝቡን ከሞትና ስደት፣አካባቢውንም ከውድመት አልታደጉትም፡፡ በየጊዜው "የመንግስት ያለህ; እያለ ከመጮህ ቦዝኖ የማያውቀው ህዝቡ፣ ሰሚ ባጣ ጊዜ “መንግስት አለ ወይ?” ብሎ ለመጠየቅ መገደዱም አይዘነጋም፡፡
የመንግስትን ቸልተኝነት በአጽንኦት ያጤነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ "ያለ ተጠያቂነት እየተፈጸሙ ያሉ ዘግናኝ ጥቃቶችን በዘላቂነት ማስቆም የሚያስችል እርምጃ መውሰድ የግድ ይላል” ሲል ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡  
የሰሜን ሸዋ አስተዳደርን፣ የደቡብ ወሎንና በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞንን እንዲሁም መከላከያን ያካተተ ኮማንድ ፖስት በወቅቱ የተቋቋመ ቢሆንም፣ ኮማንድ ፖስቱ ጥቃት አድራሾችን ለፍትህ እንደሚያቀርብ ቃል ቢገባም፣ እስካሁን ድረስ አንድም ሰው ለፍርድ አቅርቦ ስለማስቀጣቱ የተሰማ ነገር የለም።
ወንጀል ሰርቶ በደል ፈጽሞ አለመጠየቅ እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አንዳንዴም ወንጀለኞቹ በክልል ባለሥልጣናት ከለላና ሽፋን የሚያገኙበት ጊዜ እንዳለ ታዝበናል። የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈርያት ከሚል በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ “በዘረኝነት ስሜት ተነስተው ሌላው ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎችን የአካባቢው ባለስልጣናት ስለሚሸፍኗቸው ወይም ስለሚደብቋቸው የተፈለገውን ያህል መያዝና ለፍርድ ማቅረብ አልተቻለም” ብለው ነበር። ዛሬም  ችግሩ የቀጠለ ይመስላል፡፡  
በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም በሸዋሮቢት አካባቢ ተነስቶ እስከ ሞላሌ ድረስ በመዝለቅ፣ የሞላሌን ከተማ ለከፍተኛ ጥፋት የዳረገው ግጭት የተለኮሰው አንድን ከብት ጠባቂ ልጅ በጥይት በማቁሰል ነው።
በ2011 ዓ.ም ኦነግ ሸኔ ዘር ላይ ያተኮረ ጥቃቱን በሸዋ ሮቢትና በአካባቢው ህዝብ ላይ ከፈተ። የዘንድሮው ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። እንደ ክረምት እየተመላለሰ ጥቃትና ውድመት ቢፈጽምም፣ የፌደራልም ሆነ የክልሉ መንግስት ለመከላከል ተዘጋጅተው አልጠበቁትም። ወይም ፈጥነው ደርሰው ሕዝቡን ከሞት መንጋጋ አላላቀቁትም። ሁልጊዜም የሚሆነውና እየሆነ ያለው #ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ; ነው።
ከአንድም አራት ጊዜ አካባቢው የስጋት ቀጠና መሆኑ በግልጽ ታይቷል። ኦነግ ሸኔ "ሳላጠፋው እንቅልፍ አይወስደኝም" ብሎ ታጥቆ የተነሳበት አካባቢ ነው የሚመስለው። ግን መንግስት ዜጎችን ከተመሳሳይ ጥቃትና ጉዳት ለመታደግ በአካባቢዎቹ ላይ ቋሚ ሃይል የሚያሰፍረው መቼ ይሆን? የሸዋሮቢትና የአጣዬ የነገ እጣ ፈንታቸውስ  ምንድን ነው? ዛሬውኑ መልስ የሚሻ  አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡


Read 1580 times