Saturday, 16 April 2022 15:38

ሲዶርፍና የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በኢትዮጵያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

    • ስፖርትን ከስነጥበብ ያስተሳሰረው ቅፅበ  
      • ‹‹እግር ኳስ ህዝቦችን አንድ ያደርጋል›› - ሲዶርፍ
      • ‹‹ኢትዮጵያን በተጨማሪ ለማየት በእርግጠኝነት እመለሳለሁ!›› - ሲዶርፍ



             ከሳምንት በፊት ሆላንዳዊው ክላረንስ ሲዶርፍ ከ67ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ጋር በአዲስ አበባ ቆይታ ነበረው፡፡  የኢትዮጵያ እግር ኳስ አፍቃሪያን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫንና የጨዋታውን ኮከብ በቅርበት የማየትና የማግኘት እድል እንዲኖራቸው ሃይንከን ኢትዮጵያ በሸራተን አዲስ መርሃ ግብሩን አዘጋጅቷል፡፡ ክላረንስ ሲዶርፍ አስደናቂውንና ባለ ትልቅ ጆሮዎቹን ዋንጫ ወደ ላሊበላ አዳራሽ ይዞ ከገባ በኋላ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይስ ጅራና ከሃይንከን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡  በሃይንከን ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ሰስቴይንበሊቲ ስራ አስኪያጅ ፍቃዱ በሻህ  እንደገለፁት ዋንጫው ከአውሮፓ ውጭ የሚያደርገው ጉዞ በመላው ዓለም የሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪያን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በቅርበት እንዲያዩ፤ ክላረንስ ሲዶርፍን በከተማቸው እንዲያገኙት ስለሚያስችል ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡
በመግለጫው መክፈቻ ላይ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበራት ህበረት የገበያ ልማት ዲያሬክተር የሆኑት ጎይ ሎራንት ኢፒስተን ሲናገሩ ሻምፒዮንስ ሊጉ የዓለም ምርጥ ክለቦች ውድድር መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአፍሪካ የሚመጡ ተጨዋቾች በውድድሩ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ትዝታን በመጣል የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል ብለዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ደግሞ ወደ ዋንጫዋና ሲዶርፍ እየተመለከቱ “የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ በዚህ ደረጃ ጉዞ ሲያደርግ ቅናት ይሰማኛል። የአህጉራችን ሻምፒየንስ ሊግ በትልቅ ደረጃ ላይ የሚደርስበት ጊዜ ይናፍቀኛል፤ ኢትዮጵያም አንድ ቀን ትላልቅ የእግር ኳሱ አለም ዝነኛ ግለሰቦችን እንደምታፈራ እጠብቃለው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡  ክላረንስ ሲዶርፍ በበኩሉ  “ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት ለመምጣት ብዙውን ግዜ አስቤበታለሁ። በተለያዩ የአውሮፕላን በራራዎች በአዲስ አበባ ያለፍኩት በተደጋጋሚ ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በአግባቡ የመጎብኘት እድል ስላገኘው ደስተኛ ነኝ፤ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ይዤ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቴ ደስታ ይሰማኛል” ብሎ ከተናገረ በኋላ መድረኩ በእለቱ ለነበሩ የሚዲያ ባለሙያዎች ክፍት ሆኖ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውለታል፡፡
ልዩ የስነጥበብ ስጦታ ከመደመር አፍሪካ
 ከስፖርት አድማስ በቀረበለት ጥያቄ እግር ኳስ የዓለምን ህዝቦች አንድነት በመፍጠር የሚጫወተውን ሚና ሲዶርፍ ሲያስረዳ እግር ኳስ ህዝቦችን አንድ እንደሚያደርግና አዎንታዊ ለውጥ መፍጠር እንደሚችል የገለፀ ሲሆን የዋንጫዋ ኢትዮጵያ መምጣት ታዳጊዎች የሚያነቃቃ ነው  ብሏል።  ከዚህ አስተያየቱ  በኋላም የመድረክ መሪው አቶ ፈቃዱ በሻህ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ‹‹እግር ኳስ ለአንድነት›› በሚል ግዙፍ የስነጥበብ እቅድ ከሚንቀሳቀሰው መደመር አፍሪካ የስነጥበብ ስፍራ ለሲዶርፍ የተዘጋጀው ልዩ የስነጥበብ ስጦታ  እንዲቀርብ እድል ሰጥተዋል፡፡ ሰዓሊ ናትናኤል ምትኩ  በስነጥበብ ስፍራው የሰራውን ስዕል ወደ መድረኩ በመውጣት ስጦታውን ለሲዶርፍ አስረክቦታል፡፡  እግር ኳስ የሁሉም የዓለም ህዝብ  ባህል ሆኖ ይሰማኛል ሲልም ሹክ ብሎታል፡፡ ክላረንስ ሲዶርፍ ልዩ ስጦታውን በከፍተኛ ምስጋናና ደስታ ከተቀበለ በኋላ ወደ አገሩ  በሻንጣው ይዞት እንደሚሄድም ገልጿል፡፡
የስዕል ስጦታው በስነጥበባዊ ተሰጥኦ ስፖርቱን እንደሚያንፀባርቅ፤ የእግር ኳስ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት ደግሞ ስነጥበቡን በተለየ ጭብጥ እንደሚያዘምን ያረጋገጠ ነው፡፡ እግር ኳስ ለሰው ልጆች አንድነት ትልቁ ድርሻን መወጣት እንደሚችል፤ የዓለም ህዝብ  የጋራ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ስነጥበብ ልዩ ሚና እንደሚጫወትም ያመለክታል፡፡ በመደመር አፍሪካ የስነጥበብ ስፍራ ለሚካሄደው የስነጥበብ እቅድ መነሻ የነበረው በካሜሮን አስተናጋጅነት የተካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር። ሰዓሊ ናትናኤል ምትኩ ሐይለስላሴና  የስፖርት አድማስ አምደኛ  እኔ ግሩም ሰይፉ ባመነጨነው ሃሳብ 4 ስዕሎች የአፍሪካ እግር ኳስን በስነጥበብ ለማድነቅ ተሰርተዋል፡፡ የስፖርት ደጋፊዎችና ጋዜጠኞችን ወደ ካሜሮን ወስዳለው በሚል ለሰራው የፕሮሞሽን ተቋም የስነጥበብ ስራዎቹ ተበርክተዋል፡፡ ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን፤ በካሜሮን ለአፍሪካ ዋንጫው አዘጋጅ ኮሚቴ፤ በምዕራብ አፍሪካ ለሚገኙ የኢትዮጲያ ማህበረሰብና ለካሜሮን እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ኤቶ ስዕሎቹ በስጦታ እንዲደርሱ በእኛ በኩል ሃሳቡ ቀርቦ ነበር፡፡  ፕሮሞሽን ተቋሙ ሳቢያ ተግባሩ የሚፈለገውን ትኩረት እና የዜና ሽፋን እንደተጠበቀው አላስገኘም ነበር፡፡ ሆኖም ግን የመደመር አፍሪካ የስነጥበባት ስፍራ ዋና መስራች የሆነው ሰዓሊና የሂሳብ ሊቅ ጎሳ ገብረስላሴ 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት በማድረግ ስፖርትን ከስነጥበብ ለማስተሳሰር የስፖርት ጋዜጠኛ እና ሰዓሊ የፈጠሩትን ጥምረት አድንቆታል፡፡  በተለይ ከዓለማችን ኮከብ ተጨዋች አንዱ ለሆነውና በአሁኑ ወቅት የካሜሮን እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ለሆነው ሳሙኤል ኤቶ በሰዓሊ ናትናኤል የተሰራውን ስዕል ደግሞ ከማድነቅም በላይ እግር ኳስ ለአንድነት በሚለው የስነጥበብ እቅድ yሚሰራበትን ሁኔታ አሳምኖታል፡፡ መደመር አፍሪካ የስነጥበብ ስፍራ የዓለምን የእግር ኳስ ባህል ለማድነቅና ህዝቦችን አንድ ለማድረግ ይሰራል በማለትም ጎሳ ገብረስላሴ ወስኗል፡፡ ለስነጥበብ እቅዱ የመስርያ ቦታ፤ ከ120 በላይ ፍሬሞች በተፈለገው መጠን፤ ካንቫሶችና ቀለማት ለመደገፍም ቃል በመግባትም ስራውን አስጀምሮታል፡፡  በአሁኑ ወቅትም በመደመር አፍሪካ   እግር ኳስ ለአንድነት በሚል ርእስ ሰዓሊ ናትናኤል ምትኩ ከስነጥበብ ስፍራው ከሚሰሩ አባላት ጋር በመቀናጀት  በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮችና ጭብጦች የታቀዱትን ስዕሎች እየሰራ  ነው።
የሲዶርፍ ተጨማሪ ጉብኝቶችና አስተያየቶች
ክላረንስ ሲዶርፍ  በሸራተን ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ጋር ከሚዲያዎች አድርጎት ከነበረው   መርሃግብር በኋላ  የአንድነት ፓርክን በመጎብኘት ፎቶ የተነሳ ሲሆን፡ በአበበ ቢቂላ ስታድዬም በቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾችና በታዳጊ ቡድን መካከል የተካሄደ ጨዋታንም ተመልክቷል፡፡  በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ካቀረባቸው አስተያየቶች በኢትዮጵያና በአፍሪካ ላይ የተናገራቸውም ይገኙበታል፡፡
ስለ ኢትዮጵያ
ስለ ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይነት በቀረበለት ሌላ ጥያቄ ላይ ሲዶርፍ ምላሽ ሲሰጥ‹‹ ወደ ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ መምጣት ለእኔ ወደ አገር ቤት እንደመመለስ ነው፡፡ ሆላንድ ውስጥ ባሳለፍኩት የምህርት ቤት ህይወትና ወጣትነት ምርጥ ጓደኛዬ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ግን በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ታሪክ ልንገራችሁ። በጣም ልጅ እያለሁ ሆላንድ ውስጥ የአፍሪካን በተለይም የኢትዮጵያን ረሃብና ድህነት የሚያሳዩ ምስሎች ተቀርፀውብኛል። በመላው ዓለም እየዞርኩ እና አገራትን እየጎበኘሁ ለችግረኛ ህፃናትና ህዝቦች ድጋፍ የምንቀሳቀስበት ዓላማ የመጣው በዚያ ቁጭት ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ እድገት ውስጥ ሆና ስመለከት ደስ ብሎኛል፡፡››
ስለ አፍሪካ
በተጨማሪ የአፍሪካ እግር ኳስ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ በሰጠው አስተያየት‹‹ አፍሪካ በእግር ኳስ ብዙ ተሰጥኦዎችን ይዛለች፡፡ ዋናው በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ ያለው አመራር ሃላፊነቱን ወስዶ ያለውን አቅም በማጎልበት ሲሰራ ለውጥ መፍጠር ይቻላል፡፡ አፍሪካ በእግር ኳስ የራሷ ባህርያት አሏት ከሌላ ዓለም ቀድታ የምታመጣው ነገር የለም፡፡ በአፍሪካዊነት ስኬታማ መሆን ይቻላል፡፡
በእያንዳንዱ አገር ባህል እንዳለው በእያንዳንዱ ክለብም ባህል አለ፡፡ ኤሲ ሚላንና ኢንተርሚላን የአንድ ከተማ ክለቦች ናቸው፡፡ ለሁለቱም ተጫውቻለው፤ ምንም የሚያመሳስላቸው ነገር የለም፡፡ ስለዚህም በማንነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል፡፡ የታለመውን ግብ ለማሳካትም ብዙ ጥረት ያስፈልጋል፡፡...››የሚል ሃሳብ መናገሩ ይጠቀሳል፡፡
 ሲዶርፍ ከኢትዮጵያ በኋላ
ሲዶርፍ የኢትዮጵያ ቆይታውን አስመልክቶ በኢንስታግራም ገፁ ባሰፈረው አጭር ጽሁፍ ላይ ‹‹በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ጉብኝት ኢትዮጵያ  3ኛው ሀገር   ነበረች። አጭር ግን ስራ የበዛበት ቆይታ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ጊዜዎችን ከተከበሩና ውድ ከሆኑ ሰዎች ጋር አሳልፈናል። የአገሬው ስፖርት አፍቃ ሪዎች ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅር ወድጄዋለሁ። ኢትዮጵያን በተጨማሪ ለማየት በእርግጠኝነት እመለሳለሁ! ›› ብሏል፡፡
ለ67ኛ ጊዜ የሚካሄድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ለሚያሸንፍ የምትሸለመው ዋንጫዋ በአፍሪካ ያደረገችው ሽርሽር  በ4 አገራት አምስት ከተሞችን ያካለለ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በፊት  በሞዛምቢክ ዋንጫዋን ለእይታ ያቀረበው ሲዶርፍ ከኢትዮጵያ በኋላ ደግሞ በናይጄርያ ከተሞች አቡጃና ሌጎስ የሁለት ቀናት ጉብኝት አድርጓል፡፡ በዋና ከተማ አቡጃ ላይ ለሲዶርፍ አቀባበል ካደረጉት መካከል ዳንኤል አሞካቺና ጄጄ ኦካቻ ይገኙበታል። የወጣቶችና የስፖርት ልማት ሚኒስትሩ ሰንዴይ ዲሬይ ከዋንጫው ጋር አብረው በመነሳት፤ የናይጄርያ የሴቶች ሀ ቡድንን በመጎብኘት ያበረታታ ሲሆን የክላረንስ ሲዶርፍና የዋንጫዋ የአፍሪካ ጉብኝት የመጨረሻው ማረፊያ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ይሆናል፡፡



Read 21028 times