Friday, 15 April 2022 16:42

ተክለሐዋርያት ተክለማርያም - (ትንሹ የአድዋ ዘማች)

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ራኪ አንቀፅ
              
             በአዋቂነት ዕድሜያቸው “ፊውታራሪ” የሚል ማዕረግ የተሰጣቸውና በዘመኑ በጣም የተማሩ የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡ ስማቸው ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ይባላሉ። እኒህ ሰው ለሀገራቸው ብዙ ስራ የሰሩ ናቸው፤ ትምህርታቸውንም በጦር ሳይንስና በእርሻ ጥበብ፣ ለብዙ ዐመታት በውጭ ሀገር ተከታትለዋል። እኒህ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያንም ሕገ መንግስት ያረቀቁና የፃፉ ሰው ናቸው። ከዚያም  “ፋቡላ” የተባለ ርዕስ ያለው መፅሐፍ ፅፈው፣ በቴአትር መልክ ቀርቧል።…. "የእርሻ መፈተኛ” የተሰኘ መፅሐፍና ሌሎችም ፅሑፎችን አዘጋጅተዋል።
የተወለዱት በድሮ አጠራር ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ ሳያደብር በምትባል የገጠር ቀበሌ ነው። አባታቸው በዘመኑ ተፈላጊ የነበረውን የቤተክህነት ትምህርት የተማሩ፣ አርሶአደርና በቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ ካህን ነበሩ። በኋላ ደግሞ የመንግስት ሰራተኛ ሆነው በተለያዩ ስፍራዎች አገልግለዋል። እናታቸው ጠንካራ ሴት ስለነበሩ፣ ባላቸው ቢሞቱም ባል አላገባም ብለው፣ በፅናትና በትጋት ልጆቻቸውን አሳድገዋል።
ተክለሐዋርያት ትምህርታቸውን የጀመሩት ደብተራ ዐሊ የተባሉ የቄስ አስተማሪ ጋ ነበር። ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ ተምረው አስር ዐመት ሳይሞላቸው ዳዊት ደግመው ጨርሰዋል።
አብዩ ወይም ገብረፃዲቅ የተባሉት አጎታቸው፣ የቤተክህነት ትምህርት ቅኔና ዜማ የተማሩ ነበሩ። በተጨማሪም የስዕል ትምህርት ነበራቸው። ስለዚህ በጊዜው የሀረርጌ ገዢ የነበሩት የራስ መኮንን ምክትል ዋና ፀሀፊ በመሆን ያገለግሉ ነበር። ራስ መኮንን የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት የኃይለስላሴ አባት ናቸው።
እናም ተክለሐዋርያትን አጎታቸው አዲስ አበባ፣ ከዚያም ሀረር ይዘዋቸው ሄዱ። ያኔ አዲስ አበባ በሳር ቤቶች የተሞላች ነበረች።
ሀረር ከሄዱ በኋላ አጎታቸው ከራስ መኮንን ጋር አስተዋወቋቸው፡፡ እንደ ዘመኑ ልማድ ትልቅ ሰው ስለሚከበር እግራቸው ስር ወድቀው እግራቸውን ሳሟቸው፤ራስ መኮንንም ደስ አላቸው። ምን ያህል እንደተማሩ ሲጠይቁ፣ ዳዊት መድገማቸው አስገረማቸው። “ይቺ ታሪከኛ ማቲ ናት!” አሉ። “ማቲ” ማለት ትንሽ ልጅ ማለት ነው።
በተለይ የተማሩትን ትምህርት በቃላቸው ሲሉላቸው ራስ መኮንን እጅግ ተገረሙ፤ ተክለሐዋርያት ጎበዝ ልጅ እንደሆኑም አስመሰከሩ። በርግጥም ተግተው ይማሩና ያጠኑ ነበር፤ ከራስ ጋር ሲተዋወቁ ገና የዘጠኝ ዐመት ልጅ ነበሩ። ልጅ ሆነው አንዳንዴም የፈጠራ ስራ ይሰሩ ነበር፡፡ አንዴ በፈትል ስልክ ሰርተው ብዙዎችን አስደንቀዋል፡፡
የራስ መኮንን ሚስት ወይዘሮ የሺመቤትም ተክለሐዋርያትን ይወዷቸው እንደነበር ይነገራል፤ስለዚህም ወተት በየጊዜው እንዲሰጣቸው አደረጉ፡፡ በኋላ እንዲያውም አንዲት ላም ለራሳቸው ተሰጥቷቸው ነበር። ጎበዝ ስለሆኑ የማይወዳቸው ሰው አልነበረም።
በኋላም ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወርር ራስ መኮንን የሀረር ጦር መሪ ሆነው ዘምተው ስለነበር፣ ትንሹ ተክለሐዋርያት ወደ መቀሌና አድዋ ዘመቱ። ያኔ የመቀሌው ጦርነት አልቆ አድዋ ሲዘምቱ የአካባቢው ልጆች የጦርነት አዋጅ አስመስለው ሲጫወቱ፡-
በየካቲት
ጣጣችንን ክትት፤
በመጋቢት
እቤታችን ግብት፤
በሚያዝያሳ
ያገግም የከሳ።
…..ይሉ ነበር።
ጦርነቱ ሲጀመር፤ራስ ተክለሐዋርያት ወደ ግንባር እንዳይዘምቱ ነግረዋቸው ነበር። ተክለሐዋርያት ግን ጭር ያለው ድንኳን አካባቢ መቆየት ስላልፈለጉ ወደ አድዋ ጦር ግንባር ሄደዋል። ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ደርሰው፣ የተማረኩ ጣሊያኖችን አይተዋል። አንድ ኢትዮጵያዊ ቁስለኛም አግኝተው ቁስሉን በጨርቅ አስረውለታል። በጦር ሜዳ ከተጣለውና ጣሊያን ሲሸነፍ ካዝረከረከው ብዙ ዕቃ፣ስዕሎች ወስደው ለራስ መኮንን አሳይተዋቸዋል። ራስ ጦር ሜዳ በመምጣታቸው ሲቆጡ፤ “እናንተ ስትሞቱ እኔ ሰፈር ቀርቼ ምን አደርጋለሁ?” ብለው አስገርመዋቸዋል።
ተክለሐዋርያትን አፄ ምኒልክ ወደ ውጭ ሀገር የላኳቸውም በችሎታቸውና በአስተሳሰባቸው ተደንቀው ነው።
ጎበዝ ልጅ ጠንክሮ ከተማረ፣ የቤተሰቦቹንም ምክር ከሰማ፣ ራሱንና ቤተሰቡን ሀገሩንም የሚጠቅምና የሚያኮራ ይሆናል። ለዚህ ምስክር የሚሆኑን ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ናቸው።….ጎበዝ ልጅ ስለነበሩም እስከዛሬ በታሪክ ይታወሳሉ።
(ከደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ “ታላላቆቹ - ታላላቅ ሰዎች ላይ የሚያተኩር የልጆች መፅሐፍ; የተወሰደ)


Read 1553 times