Saturday, 09 April 2022 14:35

“ከዚህ በኋላ ግስጋሴያችን ከተፎካካሪነት ወደ መሪነት ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በቅርቡ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ካካሄዱ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው - ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፡፡ ፓርቲው በተመሰረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ በመቶዎች በሚቆጠሩ የምርጫ ክልሎች እጩዎችን በማቅረብ፣ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ተፎካካሪ ከነበሩት ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ተጠቃሽ ነው።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የራሱን የዋና ፅ/ቤት ህንጻ የመገንባት እቅድ የነደፈው ነእፓ፤ በመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤው ምን ውሳኔዎችን አሳለፈ? በቀጣይ ምን አይነት ተፎካካሪ ፓርቲ ለመሆን አልሟል? ከ5 ዓመት በኋላ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ምን አቅዷል? በብሔራዊ ምክክሩ ሂደት የያዘው አቋም ምንድን  ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የፓርቲውን ሊቀመንበር  ዶ/ር አብዱቃድር አደምን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል። እነሆ፡-


                 በዚህኛው ጠቅላላ ጉባዔያችሁ ምን ጉልህ ተግባራት አከናውናችኋል?
ይሄ ጠቅላላ ጉባኤያችን ፓርቲው መስራች ጉባኤ ካደረገ በኋላ የመጀመሪያው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤያችን ነው። ጉባኤ ያደረግነውም ልክ በሶስተኛ ዓመታችን ነው። አላማውም በዋናነት ሶስት ናቸው። አንደኛው በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሰረት የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ክለሳ መደረግ ነበረበት። ሁለተኛው የተጓደሉ የብሔራዊ ም/ቤት አባላትን ለማሟላት ሲሆን ሶስተኛው የፓርቲውን አጠቃላይ የ3 ዓመት እንቅስቃሴ ገምግሞ እስከ ቀጣይ ጉባኤ ድረስ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነበር። እነዚህን ሶስት አላማዎች በተሳካ ሁኔታ ፈጽመናል ማለት ይቻላል።
በተለይ ሁኔታ በጉባኤው ውይይት ተደርጎበት፣ አቋምና ውሳኔ የተላለፈበት ጉዳይ ይኖር ይሆን?
የጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ ባወጣነው የአቋም መግለጫችን ላይ በግልፅ ያስቀመጥናቸው ጉዳዮች አሉ። ከነዚያ ውስጥ ዋና ዋና የሚባሉትን ለመጥቀስ ያህል አንደኛ፣ ሃገራችን ያለችበት የሠላም እጦት ሁኔታ ነው። ባለፉት አራት የሽግግር ዓመታትና ከዚያም በፊት የነበሩ ችግሮች እየተንከባለሉ መጥተው፣ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ለህዝባችን  ችግር ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር  ቁልፍ ጉዳይ ብለን የለየነው፣ የኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት ጉዳይ ነው። ከምንም በላይ ሁሉም አካላት የኛን ፓርቲ ጨምሮ፣ ሰላም ለማምጣት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ለሰላምና መረጋጋቱ መምጣት  እንደ ቁልፍ ስትራቴጂ የወሰድነው ደግሞ ሊካሄድ የታሰበውን ሃገራዊ ምክክር ነው። ይሄ አጀንዳ ደግሞ ከፓርቲው ምስረታ ጀምሮ ብዙ የሰራንበት አጀንዳ ነው፡፡ አሁንም ለሂደቱ መሳካት የራሳችን ጠንካራ አዎንታዊ ሚና ሊኖረን እንደሚገባ ወስነናል። በተለይ ከመንግስት ባህሪ  ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች ሊኖሩበት እንደሚችል እንገነዘባለን፤ ነገር ግን ምክክሩ የግድ አስፈላጊና ወሳኝ ነው። ከኮሚሽኑ አወቃቀር ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ቢኖሩንም፣ በሂደቱ ግን ጠንካራ ተሳትፎ ልናደርግ  እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል። ሁለተኛው አቅጣጫ የተቀመጠበት ጉዳይ፣ በሃገሪቱ ሰሜናዊ  ክፍል የሚካሄደው ጦርነት ምንም እንኳን ጋብ ቢልም፣ አሁንም ቢሆን በተለይ በአፋር  አዋሳኝ ወረዳዎች ችግሮቹ አልቆሙም፡፡ ስለዚህ ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ  በአፋጣኝ ማመቻቸትና መስራት እንደሚገባ ፓርቲው በአቋም አስቀምጧል። ፓርቲያችን በተደጋጋሚ ጦርነት መፍትሄ እንደማይሆንና ሁሉም ወገን ጦርነት እንዲያቆም አቋሙን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ አሁንም ይሄ አቋማችን ይቀጥላል ማለት  ነው።
በአገሪቱ ግጭትና ጦርነት የሚቆምበት መንገድ ምንድን ነው ትላላችሁ?
እኛ ሃገር የጦርነት ወይም የግጭት ምክንያቶች የተወሰኑት የቅርብ ጊዜ ናቸው። በተለይ ከሽግግሩ ሂደት ጋር ተያይዞ የመጡ አሉ፤ ነገር ግን ፓርቲያችን በዋናነት ችግሮችን ከስረ መሰረቱ ለመፍታት ቢቻል ከምርጫ በፊት ነበር ሃገራዊ ውይይት ያስፈልግ የነበረው። ያ ቢሆን ኖሮ ጦርነትም የሚፈጠርበት እድል ጠባብ ነበር። ፓርቲያችን፤ በትግራይና በፌደራሉ መንግስት  መካከል የተፈጠሩት ችግሮች በንግግር መፈታት የሚችሉ ናቸው ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ መሰረታዊ የመፍትሄ ሃሳባችን ሃገራዊ ምክክር ማድረግ ነው።

ተነገደል ትርፉን ተቀበል - ዶ/ር አብዱልቃድር አደም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ... | Facebook
በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የምክክር ሂደት ላይ ፓርቲያችሁ ያለው አቋም ምንድን ነው? በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት የተንፀባረቀውን ሃሳብ እናንተም ትጋሩታላችሁ?
የፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ባሳለፋቸው  ውሳኔዎች ውስጥ በጋራ ተሳትፈናል። እነዛ ሃሳቦች የኛንም ሃሳብ ይገልጻሉ። ሁሉም የም/ቤቱ አባል ፓርቲዎች በሚባል ደረጃ ያለን አቋም ተመሳሳይ ነው። ይሄ ሃገራዊ የምክክር ሂደት እኔም በሚገባ የተሳተፍኩበት፣ እንደ ጋራ ም/ቤቱም ዋነኛ አጀንዳችን አድርገን የገፋንበት ነው፡፡  ሁላችንም ብዙ ለፍተንበታል። በመጨረሻ ሰዓት ነው መንግስት ወደ ራሱ ወስዶ ኮሚሽን ወደ ማቋቋም የገባው።  ይሄን ማድረጉ ክፋት የለውም፤ ነገር ግን መንግስት  በሂደቱ ውስጥ እጁ እንዳይረዝምና ሂደቱን እንዳያበላሽ ስጋታችንን ገልፀን ነበር። በተለይ በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደረጉ ውይይቶች  መንግስት ተቀብሎ ያስተካከላቸው ጉዳዮች አሉ። መጨረሻ ላይ ችግር የተፈጠረው በኮሚሽነሮቹ የምርጫ  ሂደት ላይ ግልፅነት የጎደለው አሰራር በመከተሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው የጋራ ም/ቤቱም አቋም የያዘው። እንደ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ እነዚህ ችግሮች እየታዩ እየተፈቱ፣ ሂደቱ መቀጠል አለበት የሚል ነው አቋማችን። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ዋነኛ መፍትሔ ውይይትና ምክክር ብቻ ነው። ይሄ ሃገር ከዚህ በላይ ጦርነትና ግጭት ሊሸከም አይችልም። ይሄ ምክክር  እንዲሰምር ደግሞ መንግስት በማንኛውም መልኩ እጁን ላለማስገባት መጠንቀቅ አለበት። አለበለዚያ ሂደቱ ይበላሻል።
ፓርቲያችሁ ከአምስት ዓመታት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ በምን መልኩ እናገኘዋለን?
የፓርቲያችን መለያ ብለን የምናስባቸው የትግል ስልቶች ሚዛናዊነትና ምክንያታዊነት ናቸው። ስንደግፍም ሆነ ስንቃወም፣ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር  ከገዥውም  ሆነ ከተቃዋሚዎች ጋር ዋነኛ የፓርቲያችን መርህ፣ ሚዛናዊነትና ምክንያታዊነት ይሆናል። ከፅንፈኝነት መራቅ፣ የሌላውንም ችግር በሌላው ጫማ ውስጥ ሆኖ ማየት ያስፈልጋል። በኛ ሃገር ወቅታዊ ሁኔታ የተለያዩ የቡድን ሳጥኖች አሉ። በማንነት ላይ ትኩረት ሰጥተው የሰሩ አሉ፤ በዜግነት ፖለቲካ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ አሉ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ጫማ ውስጥ የራስን እግር አስገብቶ ነገሮችን ማየት ያስፈልጋል። በመሰረቱ እኛ የዜጋ ፖለቲካን ትኩረት እናደርጋለን። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው አብሮነትን ነው። በብሔር በእምነት መገዳደልና መተራመስን አይፈልግም። ፓርቲያችን እንደ ፓርቲ፣ "ከተፎካካሪነት ወደ መሪነት" የሚል መሪ ቃል አለው።  ከዚህ በኋላ ግስጋሴያችን ወደ መጨረሻው ግባችን ይሆናል። 7ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ሩቅ አይደለም። ከወዲሁ ሰፊ እቅድ ነድፈን ዝግጅታችንን እንጀምራለን። ከዚያ በፊት ደግሞ የአካባቢና ማሟያ ምርጫ አለ። ይሄንንም  የምንንቀው አይሆንም፡፡ ለዚህም እቅዶችን አዘጋጅተን እየተንቀሳቀስን ነው ያለነው።

	  </div>
	  
		<div class=

Read 3246 times