Saturday, 09 April 2022 13:47

የጎንደር ዩኒቨርስቲ አስደንጋጭ የጥናት ውጤት - በወልቃይትና አካባቢው

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)


           “የህወኃት ታጣቂ ቡድን የፈፀመው ወንጀል ከናዚው የዘር ፍጅት ጋር ተመሳሳይ ነው”
           “ከአካባቢው ማህበረሰብ 75 በመቶው የሽብር ቡድኑ ጭፍጨፋ ሰላባ ሆኗል” ።
           “በአካባቢው 12 የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል
                   

              በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወኃት ታጣቂ ኃይል፤ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች ላይ የፈፀመው ወንጀል ከናዚው የዘር ፍጅት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው የጎንደር ዩኒቨርስቲ ይፋ ባደረገው አዲስ ጥናት አመለከተ። ዩኒቨርስቲው በአካባቢው 13 ወራትን የፈጀ ምርመራና ጥናት ማካሄዱን አስታውቋል።
በማይካድራ የተፈፀመውን የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ተከትሎ፣ ዩኒቨርስቲው 21 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን አቋቁሞ፣ ላለፉት 13 ወራት ሰፊ ጥናት ሲያካሄድ መቆየቱን ጠቁሞ፤ በጥናቱም ባለፉት አርባ ዓመታት  በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አካባቢዎች  በሚኖሩ ህዝቦች ላይ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጅል ተፈፅሟል- ብሏል።  የህወኃት ቡድን ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አካባቢው በመዝለቅ የአካባቢው ነዋሪዎችን ማነንት በመግፈፍ ሌላ ማንነት እንዲላበሱ አድርጓቸዋል ብሏል ጥናቱ።
ህወኃት ስልታዊ  በሆነ መንገድ ህብረተሰቡ ማንነቱን እንዲያጣ፣ ከመኖሪያው እንዲፈናቀል፣ እንዲሰደድና እንዲሰቃይ አድርጎታል ያለው የጥናቱ ውጤት፤ የጅምላ ግድያ፣እስርና ጭፍጨፋም ፈፅሞበታል ብሏል።
አሸባሪው ቡድን በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢ ያልፈፀመው ግፍ የለም ያለው ጥናቱ፤ ሰው በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ  ከነሕይወቱ መቅበሩንም በምርመራው ማረጋገጡን አመልክቷል።
 በጥናቱ ውጤት መሰረትም ከአካባቢው ማህበረሰብ 30 በመቶ የተገደሉ፣ 26 በመቶው ታፍነው የተወሰዱ፣ 19 በመቶ አድራሻቸው የጠፋ ሲሆኑ በአጠቃላይ ከነዋሪው ማህበረሰብ 75 በመቶ ያህሉ  የሽብር ቡድኑ ጭፍጨፋ ሰለባ መሆናቸውንም ተጠቁሟል። በጥናቱ 12 የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውንና ይህንንም ለአለማቀፍ ማህበረሰብ ምልከታ ማድረግ እንደሚችል ጠቁሟል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ 1949 ድንጋጌን የጠቀሰው የዩኒቨርስቲው ጥናት፤ በዚህ ድንጋጌ መሰረትም የህወኃት ታጣቂ ቡድን የፈፀመው ጭፍጨፋ በዘር ፍጅት ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው ብሏል።


Read 21004 times