Print this page
Saturday, 02 April 2022 12:09

ነብር አዳኝዋ እቴጌ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የእቴጌዋ ፍላጎት አንድና አንድ ነው - ነብሮን መግደል፡፡ ያንን ማድረግ የፈለገችው ደግሞ  የዱር እንስሳ የመግደል አባዜ ኖሮባት ወይም ደሞ ነብሩ ሰው እየበላ አስቸግሮ፣ እሱን ገድላ ህንዶቹን ከስጋት ለመገላገል አይደለም፡፡ እንደ አንድ አስፈሪ አውሬ ለመቁጠር እንኳ የሚያዳግት ያረጀ ነብር ገድላ ምንም የምትፈይደው ነገር እንደሌለ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከዚያ ይልቅ እቴጌይቷን ያሳሰባት ‘ነብር ገዳይዋ’ እየተባለች ለጉድ ስትወደስ የከረመችው ሉና፤ እንደዚያ ትልቅ መነጋገሪያ መሆን ነው። እናም ጋዜጦች ሁሉ የገደለችውን ነብር ቆዳ ለብሳ በተነሳቻቸው የሉና ፎቶግራፎች ሲጥለቀለቁ አይታ ነው፣ እኔም እንደዚያ ማድረግ አለብኝ ብላ የተነሳችው፡፡
መጀመሪያውኑም ይህንን እቅድ ስታወጣ ነብሩን ገድላ ወደ ሃገሯ እንደተመለሰች ሉናን የክብር እንግዳ አድርጋ በመኖሪያ ቤቷ የምታዘጋጀውን በአይነቱ የተለየ ትልቅ የምሳ ግብዣ በአእምሮዋ እየሳለች ነው። ልደቷን አስመልክታ የምትገለውን ነብር ጥፍር በስጦታ መልክ ለሉና ስታበረክትላት፣ ግብዣው ላይ የሚገኙት የታወቁና የተከበሩ ትላልቅ ግለሰቦች ብሎም ያገሬው ሰው በሙሉ ሉናን እረስተው የሷን ገድል በመደነቅ ሲያወሩ ሁሉ ይታያት ነበር፡፡
ሰዎች በረሃብና በፍቅር እጦት እየተንገበገቡ በሚኖሩባት ምድር ላይ እቴጌይቷን ከምንም በላይ የሚያስጨንቃት ና የሚያሳስባት ጉዳይ ሌላ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በሉና ላይ ትቀናለች ብቻ ሳይሆን እንደውም እንደሷ የምትጠላው ሰው የለም፡፡ እናም ነገረ ስራዋ ሁሉ ከሷ ጋር መፎካከር ብቻ ነው፡፡ ከሉና በልጣ ለመታየት የማትፈነቅለው ድንጋይ  የለም። በቃ የሷ ትልቁ ህልምና ቅዠቷ ያ ነው። ሉናን የምታስንቅ አይነት ሰው ሆና ከመገኘት የበለጠ የሚያስደስታት ነገር የለም፡፡ ለዚህም ነው በጣም ብዙ ገንዘብ መድባ ነብር ልትገድል ቆርጣ የተነሳችው፡፡
በተያዘው ፕሮግራም መሰረት፤ እቴጌ ነብሯን ለመግደል ሃገር አቋርጣ ቦታው ላይ ስትደርስ፣ ህይወቷን ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ ግዳይዋን መጣል ትችል ዘንድ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተገቢው ገንዘብ ተከፍሎ ሁሉ ነገር ተመቻችቶ ነው የሚጠብቃት፡፡ እርግጥ ነው ነገርዬው የገቢ ምንጫቸው ለደረቀባቸው የመንደሩ ሰዎችም በጣም ጥሩ መላ ነበር የሆነላቸው፡፡ በዚያ ላይ ከማርጀቱ የተነሳ ለራሱም አድኖ መብላት አቅቶት ፊቱን ቀለል ወደሚሉት ትናንሽ የቤት እንስሳት ያዞረ አንድ ጨምባሳ ነብር ነው የምትገለው፡፡ እናም ደግሞ በተሰጣቸው ዳጎስ ያለ ገንዘብ የተደሰቱት ያገሬው ሰዎች፣ ከተቻለ እንደውም በዚያ አጋጣሚ መንደራቸውን ለማስተዋወቅና ሌሎች መሰል አዳኞችን ለመሳብም ጭምር በማሰብ የአደን ትርኢቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ በከፍተኛ ሞራል ነው የተንቀሳቀሱት፡፡ እናም የሰፈሩ ልጆች በሙሉ መንደራቸው አፋፍ ላይ ወዳለው ጫካ ሄደው፣ ነብሩን ከጠዋት እስከ ማታ እንዲጠብቁ ተደረገ፡፡ የልጆቹ ተልእኮ - ምንም እንኳ እንደዚያ የማድረግ እድሉ የሞተ ቢሆንም፣ እንዲያው ግን ምናልባት ወደ ሌላ ቦታ እንዳይሄድ - ነብሩን በብልሃት ጠብቆ ማቆየት ሲሆን ለዚህ ደግሞ በየቀኑ ልክ እንደሱ ሙትት ያሉ፣ አንድ ሃሙስ የቀራቸው ፍየሎችን እያመጡ፣ በግብር መልክ ለሱ አመቻችተው ማቅረብ ነበረባቸው፡፡ ያለዚያ  አዳኝዋ  እመቤት ሳትመጣ ነብሩ ቀድሞ እጃቸው ላይ ሊሞትባቸው ይችላል፡፡ የነብሩ ሁኔታ በጣም ያሳሰባቸው ከመሆኑ የተነሳ ማገዶ የሚለቅሙ እናቶች ሳይቀሩ በዚያ በኩል ሲያልፉ ያን ያረጀ ነብር ላለመበጥበጥ የሚጥም ዘፈን ያንጎራጉሩለታል፡፡
በዚህ መልክ ነው ነብሩን እየተንከባከቡ በህይወት ጠብቀው ያቆዩት፡፡ እናም ያው መቼስ አይደርስ የለምና የተቆረጠለት ቀን ደርሶ አዳኝዋ እቴጌ ዝናሯን ታጥቃ ከተፍ አለች፡፡ እሷን ለመቀበል የነበረው ሽርጉድ ታዲያ ልዩ ነበር፡፡ በተያዘው ዕቅድ መሰረት፤ እቴጌ ግዳይዋን የምትፈፅመው በዚያው ምሽት ስለሆነ፣ ነዋሪዎች የሚጠበቅባቸውን የመጨረሻውን ወጥመድ አዘጋጁ፡፡ ምንም እንኳን በቅጡ የማይሰማ ሙትቻ ነብር ቢሆንም፣ እንዳይስታት አመቻችተው ፍየል አምጥተው ዛፍ ስር አሰሩለት፡፡ ደግነቱ የምሽቱ ጨረቃም ደማቅ ነበረች። ይኸኔ ነው ነብር አዳኟ  አንዳንድ ነገሮችን እንድታግዛት የተቀጠረችላትን ብላቴና አስከትላ፣ ከተባለችው ዋርካ ስር ተኝታ፣ መሳሪያዋን ደግና የነብሩን መምጣት መጠባበቅ የጀመረችው፡፡
‘እትዬ - እኔ ግን ይሄ ነገር አልጣመኝም! እንጃ ብቻ የሆነ ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡’ አለች ብላቴናዪቷ፤ ድምፅዋን ዝቅ አድርጋ። እውነት ነብሩ አሳስቧት ሳይሆን ዝም ብላ ስታካብድ ነው እንደዚያ ያለቻት፡፡
‘ባክሽ ዝም ብለሽ የማይመስል ነገር አታውሪ፡፡ በጣም ያረጀ ነብርም አይደል እንዴ? እንደው ደርሶ ልሞክር ቢል እንኳ በፍፁም ሊደርስብን የሚችል አይነት አይደለም፡፡’ በማለት ነገሩን አቃለለችባት  እቴጌ፡፡
‘አይ እትዬ! እንደምትዪው በጣም የጃጀ ነብር ቢሆን ኖሮ፣ ያን ያህል ብዙ ገንዘብ ያስከፍሉሽ ነበር ብለሽ ነው?’
ብላቴናዪቷ በጥቅሉ ገንዘብን ወዳጇ አርጋ የያዘች ብልጣ-ብልጥ ፍጡር ነች። ገንዘብ ለማግኘት የትም ትገባለች፣ ምንም ታደርጋለች፡፡ ብትችል  ለሃገሯ ልጆች የሚወረወሩትን ጉርሻዎች ሳይቀር ብትቆረጭም ደስታዋ ነው፡፡
የሆነው ይሁንና የተፈጠረው ነገር በየቦታው ሲለፈፍ የምትሰማውን የነብሮች ቁጥር ማሽቆልቆል በውኑ ደርሶባት ቀብሩን እያየች እንዳለች አይነት ስሜት ነው የፈጠረባት፡፡
ነብሩ የታሰረችውን ፍየል እንዳየ ብቻ በደረቱ ነው ለጥ ብሎ የተኛው፡፡ አኳኃኑ ግን ቀስ ብሎ አድፍጦ ሳይታይ መሬት ለመሬት እየተሳበ ሄዶ ሊቀጭማት ሳይሆን፣ የትም የማታመልጠው ግዳዩ ላይ ከመውደቁ በፊት ትንሽ ማረፍ ፈልጎ አይነት ነው፡፡
‘ኧረ! ይሄ ነብር በጣም አሞታል መሰለኝ’ አለች ብላቴናዋ - በህንድኛ፡፡ ለእቴጌዋ ሳይሆን ከነሱ ትንሽ እራቅ ብሎ እየተሽሎከለከ ለነበረው የጎበዝ አለቃ ነው መልእክቷ፡፡
‘እሽሽሽ ዝም በይ!’ አለቻት እቴጌዋ፡፡
በዚህ መሃል ነው ነብሩ የተጣለለት ፍሪዳው ላይ ሊሰፍር ብድግ ያለው፡፡
‘አሁን ነው! ይሄኔ ነው ማለት - በዪው! በዪው!’ አለች ልጂት፤ ‘አሁን ብትገድዪው እኮ የፍየሏን ዋጋ ማስቀነስ እንችላለን፡፡’ - የራሷን አየር እያመቻቸች ነው፡፡
እቴጌ ጥይታቸውን ተኮሱት፡፡ ነብሩ ጥምልምል ብሎ ወደቀ፡፡ ወዲያው ያገሬው ልጆች በደስታ እየተጯጯሁ አካባቢውን ወረሩት፡፡ በመቅፅበት ውስጥ ነው ዜናው መንደራቸው የደረሰው፤ እናም ነዋሪዎቹ ወጥተው ጡሩምባቸውን እየነፉ የምስራቹን በእልልታ ማስተጋባት ጀመሩ፡፡ ነብር ገዳይዋ እቴጌ ግን በዚያ ጩኸትና ጭፈራ መሃል ሆና ታስብ የነበረው ሃገሯ ተመልሳ ቤተ መንግስት በመሰለው መኖሪያ ቤቷ ውስጥ የምታዘጋጀውን ድል ያለ ድግስ እና የሚጠብቃት ቸበርቻቻ ነበር፡፡
በጥይት የተመታው ነብሩ ሳይሆን ፍየሏ እንደሆነች መጀመሪያ ያየችው፣ ያቺ ተንከሲስ ብላቴናይት ነበረች፡፡ እንዳለችውም - ሲታይ የቆሰለችው ፍየሏ እንጂ ነብሩን ጥይት የሚባል ነገር አልነካውም፡፡ እሱ ለራሱ እንዲሁ ጫፍ ላይ ነበርና፣ በጥይቱ ድምፅ ደንብሮ ወድቆ ነው፣ በዚያው ፀጥ ያለው፡፡
ክስተቱ ገድሏን በእጅጉ የሚያኮስስባት ነገር ስለሆነ የአደን ትርኢቱ በዚያ መልክ መቋጨቱ እቴጌዋን በእጅጉ አበሳጭቷታል። ቢያንስ ግን የሞተው ነብር እጇ ላይ ስለወደቀ በዚያ እየተፅናናች ነው፣ ያገሬው ሰው ‘ነብር ገዳይዋ’ እያለ በዘፈን እያወደሰ ሲጨፍርላት ትሰማ የነበረው፡፡
እንዲያም ሆኖ እቴጌይቱ በነብሩ ሬሳ ላይ እየተኩነሰነሰች፣ እልፍ ፎቶዎችን ተነሳች፣ እናም ዜናው በስፋት ተሰራጨ። ጋዜጦችና መፅሄቶችም የአዳኟን እቴጌ ጀብዱ የሚያዳምቁ ዘገባዎችን ይዘው ወጡ። በተራዋ የእቴጌ ዝና እንዲህ መናኘት ያላስደሰታት ሉናን ብቻ ነበር፡፡ በቅናት እርር ድብን ከማለቷ የተነሳ ለተወሰኑ ሳምንታት ራሷን ከጋዜጣና መጽሄቶች አገደች፡፡ ይሁንና እቴጌ የነብሩን ጥፍር በስጦታ መልክ ለልደቷ ስለላከችላት ሳትወድ በግዷም ቢሆን - የምንተ እፍረቷን፣ የምስጋና ደብዳቤ መፃፏ አልቀረም፡፡ በግብዣው ላይ ግን ለመገኘት አልደፈረችም፡፡
እቴጌ የነብሩን ቆዳ አገልድማ በኩራት እየተምነሸነሸች እቤቷ ስትገባ የተደረገላት አቀባበል ጉድ የሚያሰኝ ነበር፡፡ አጀባና ከበርቻቻው በጣም የሚገርም ነው። ሰዉ ሁሉ በሆይታው ከመዋጡ የተነሳ የቆዳውን ሁኔታ የሚያስተውልበት ቀልብ አልነበረውም፡፡ ታዲያ እቴጌዋም ኮራ ብላ ነው፣ በቄንጥ እየተሸከረከረች ስትሸልልባቸው የነበረው፡፡ የነብር ቆዳዋን ተጎናፅፋ ልክ እንደ ታላቋ ዳያና በክብር ተሞሽራ፣ በታወቀው የሃገረ ገዢ እልፍኝ አዳራሽ እየተንፈላሰሰች ስትዘባነን፣ የሆነች ለየት ያለች አስደማሚ ግርማዊት ንግስት ነበር የምትመስለው፡፡ እንደውም አንድ ወዳጇ እንዳላት፣ ዝግጅቱን ልክ እንደ ጥንቱ ዘመን ስርአተ-ጭፈራ፣ ታዳሚዎቹ በሙሉ ያላቸውን የአራዊት ቆዳ ለብሰው የሚገኙበት፣ በአይነቱ የተለየ አስደናቂ ዝግጅት ለማድረግ ሁሉ ታስቦ ነበር፡፡
‘እንደዛ ሲያዳንቁና ሲጨፍሩ የነበሩት ሰዎች ግን በትክክል የሆነውን ነገር ቢያውቁ እንዲያው ምን ይሉ ይሆን?’ ነገሩ ሁሉ ካለቀ በኋላ በሁለተኛው ቀን ነበር፣ ብላቴናዋ የጠየቀቻት፡፡ ‘ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?’ አለች እቴጌዋ፤ ቆምጨጭ ብላ፡፡
‘ማለቴ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ አይነት እኮ ነው ያደረግሽው፤ በጣም ይገርማል። እንደው ግን ፍየሏን መትተሽ ነብሩን በድንጋጤ ፀጥ እንዳደረግሽው ቢያውቁ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ሳስበው ይገርመኛል፡፡’
‘እንዲች ብለሽ እንዳታስቢያት! በጭራሽ የሚያምነኝ ሰው ይኖራል ብለሽ እንዳትጠብቂ! ማንም ያንቺን ወሬ አምኖ እንደማይቀበልሽ ነው የምነግርሽ፡፡’ የእቴጌዋ ፊት ፍም መስሏል፡፡
‘ቢያንስ ግን ሉና አትቀበለኝም ብለሽ ነው?’
‘ያን ያህል ጨክነሽ አሳልፈሽ ትሰጪኛለሽ ብዬ አላስብም፡፡’ ከመደራደር ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት ገብቷታል፤እቴጌ፡፡
‘ኧረ እትዬ እኔም እንደዛ የማድረግ ፍላጎት የለኝም፡፡ ግን አንዳንዴ እየሄድኩ አረፍ የምልበት - ሃገር ቤት ልገዛው የምፈልገው አንድ ቦታ አለ፡፡ ደግሞ ያን ያህል እንደምታስቢው ብዙ ገንዘብ አልጠይቅሽም። የሆኑ ሺዎች ብቻ ጣል ካደረግሽብኝ በቂዬ ነው፡፡’
ብላቴናዋ እንዳለችው በኋላ ላይ ‹አለ የተባለ› ጉደኛ ቤት ነው ሃገሯ ላይ የሰራችው። ከምንም በላይ ያገሬውን ሰው በጣም ያስገረመው ግን ቤቱን የሰራችበት መንገድ ነው፡፡
በእቴጌዋ በኩል ደግሞ አንድ የተገነዘበችው ነገር ቢኖር፣ እንደዚህ ያሉ ያልታሰቡ ወጪዎች ሰውን ምን ያህል እንደሚያሰክሩና አደጋ ላይ እንደሚጥሉ ነው። አደን የሚባለውን ነገር እርግፍ አድርጋ የተወችውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡


Read 2474 times
Administrator

Latest from Administrator