Saturday, 26 March 2022 09:59

ቢጂአይ ለስንቅ ሱቅ ባለቤት እናቶች “ስንቅነሽን” አስረከበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ቢጂአይ ኢትዮጵያ ከትላንት በስቲያ በእንጦጦ ፓርክ በተከናወነ ስነ-ስርዓት ለ”ስንቅ” ሱቆች ባለቤት ለሆኑ እናቶች የምርቶች ማከማቻና ተጓዳኝ ስራዎችን በጋራ የሚሰሩበትን መጋዘን ቁልፍ ያስረከበ ሲሆን መጋዘናቸውን የሚሸጧቸውን ምርቶች ማከማቻ ለማድረግ እንዲችሉ ታልመው የተዘጋጁ ናቸው ተብሏል። የስንቅ ሱቅ ባለቤት ለሆኑ እናቶች የተበረከተው መጋዘኑ “ስንቅ ነሽ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
ቢጂአይ ኢትዮጵያ የእንጦጦ ፓርክ ስራ ተጠናቆ እንቅስቃሴ ሲጀምር፣ ከሌሊት እስከ ሌሊት፣ ከዓመት እስከ ዓመት፣ በበጋ የፀሃይ ሀሩር፣ በክረምት ዶፍ ዝናብ ሳይበግራቸው ህይወትን ለማሸነፍና ልጆቻቸውን ለማሳደግ ዳገት ቁልቁለቱን በመውጣት በመውረድ መራር ህይወት ሲመሩ ለነበሩ 200 እናቶች፤ በፓርኩ ውስጥ የሥራ እድል እንዲከፈትላቸው ከማድረጉም ሌላ የዓመት ደሞዛቸውን በመክፈል እፎይታን እንዲያገኙ በማድረግ፣ ለነዚያ ታታሪ እናቶች ያለውን አክብሮት አሳይቷል።
ድርጅቱ እንጦጦ ፓርኩ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ “ስንቅ” በምትባው ከአልኮል ነፃ በሆነች መጠጡ የሰየማቸውን ሱቆች ሰርቶ ከመስጠቱም በተጨማሪ፣ ለሱቅ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በነፃ በማቅረብ ሌሎች ተጨማሪ እናቶች በማህበር እየተደራጁ የሚሰሩበትና በቋሚነት ገቢ የሚያገኙበትን የስራ እድል ፈጥሮላቸዋል-ተብሏል።
ከአንድ ዓመት በፊት ስራውን የጀመሩት እናቶች ከአዲሱ ስራ ጋር ተለማምደው በቅልጥፍና ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ ያለው ኩባንያው እንደወትሮው ሁሉ ይህን ተግባር ለወገኑ በተለይ የሀገር ምሰሶ ለሆኑ ሴቶችና እናቶች በማረጉ ኩራትና ክብር ይሰማዋል ብሏል።
ቢጂአይ ኢትዮጵያ እርካታ የሚያገኘው ማህበረሰቡን የሚጠቅም ስራ በመስራቱ ብቻ ሳይሆን የፈጸመው መልካም ተግባር ፍሬ አፍርቶ ለማየት ሲችልም ጭምር ነው። የልብ ህሙማኑ ህጻናት ታክመው፣ የመንፈስ ጉዳት የደረሰባቸው ህጻናት ከጭንቀት ተላቀው ሲስቁ፤ በትምህርት ቤታቸው ግቢ በደስታ ሲቦርቁ፣ እናቶች ወልደው ልጆቻቸወን ሲስሙ ሲያይ እንደሆነም ተጠቁሟል። ቢጂአይ አንዴ የስራ እድል ከፍቻለሁ ብሎ ዝም አይልም፣ ይከታተላል። ለዚህ ነው እንጦጦ ፓርክ ያሉ እናቶችን ችግር ተመልክቶ በየሱቆቻቸው የሚሸጧቸውን ምርቶች በማመላለስ እንዳይቸገሩ በማሰብ፣ ሁሉም በጋራ የሚሰሩባት የምርት ማከማቻ መጋዘን “ስንቅነሽ” በሚል ስያሜ ገንብቶ ያስረከባቸው-ብሏል።
“ስንቅነሽ” የምርት ማከማቻ መጋዘን ብቻ ሳትሆን ሴቶቹ በህብረት ሆነው ጎን ለጎን ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎችን እንዲሰሩባት ታስባ የተሰራች ናት” ያለው ኩባንያው፤ “የቢጂአይ ኢትጵያ የስኬት ትርጉም ብቻውን ያሰበውን አሳክቶ የሚያገኘው ሳይሆን ከሀገሩና ከህዝቡ ጋር ተደጋግፎ የሚደርስበት ከፍታ ነው” በማለት አብራርቷል።

Read 11467 times