Saturday, 19 March 2022 10:56

የአድዋ ድል - አተያይ ሁለት

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  “--ጥቁር ሕዝብ በቆዳ ቀለሙ ብቻ እንደ ከብት ይሸጥ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎች ሰው በቆዳ ቀለሙ አይመዘንም፤ ሰው ሰው ነው ብለው ተነሱ፡፡ ጣሊያኖች ከፍተኛ መሳሪያ ነበራቸው፤ በእሱ ተማምነዋል፤ ኢትዮጵያዊያኖች ደግሞ ከእነሱ የበለጠ መሳሪያ ነበራቸው፡፡ እሱም ኢትዮጵያዊነታቸው፤ ማንነታቸው፤ ክብራቸውና አንድነታቸው ነበር፡፡--;
                
              የአድዋ ድል 126ኛውን ዓመት ለማክበር “ሐበሻ እስታር መልቲ ሚዲያ; ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተደረጉ ንግግሮችን ባገኘሁት መጠን ባለፈው ሳምንት ማቅረቤን አስታውሳለሁ፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ “አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይመንት” ባዘጋጀው ተመሳሳይ ፕሮግራም ላይ የተደረጉ ንግግሮችን ለማስቃኘት እሞክራለሁ፡፡ በዚህ መድረክ ላይ አርቲስት አለምፀሐይ ወዳጆና ኡስታዝ አቡበከር  አህመድ ተናጋሪዎች የነበሩ ቢሆኑም፣ ንግግራቸውን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ከተናጋሪዎች አንዱ በነበረው ደራሲና ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት ልጀምር፡፡
አቶ አያልነህ ፈረንጅ የሚባል ፍጡር ሲያስተምሩት የማይማር መሆኑን ጠቁመው፣መቀሌ ምሽግ ውስጥ በውሃ ጥም እያለቀ የነበረውን የጣሊያን ወታደር ምሽጉን ለቆ እንዲወጣ ሲስማማ፣ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ጓዙን የሚያነሳበትን አጋሰስ ሰጥተው “ሂድና ከወገኖችህ ጋር ሆነህ ውጋኝ” ብለው እንደላኩት አስረድተዋል፡፡ ጣሊያኖችን በወቅቱ መጨረስ ይቻል እንደነበር ያውሱት አቶ አያልነህ፤ በ1928 ዓ.ም በሁለተኛ ወረራቸው ጊዜ፣ ሁለት ወጣቶች ቦንብ ወረወሩ ብለው በሶስት ቀን ውስጥ ሰላሳ ሺህ ሰው እንደጨረሱ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፤ ፈረንጅ ሰው ነወይ? የሚል ጥያቄ በማቅረብ ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡
በአስር ዓመት አካባቢ የሚገመተው ህፃን ቅዱስ እንቁ ባህሪ፣ "ዛሬ እኛ የአድዋን ድልን በደስታ ስናከብር ጣሊያኖች ምን እየሰሩ ነው?" የሚል ጥያቄ ለታዳሚው አቅርቧል። ጣሊያኖች የራስ መንገሻን ጦር ደጋግመው ስላሸነፉ ሁሉን የሚያሸንፉ መስሏቸው እንደነበር፣ መጀመሪያ አምባላጌ ላይ ቀጥሉ መቀሌ ከዚያም አድዋ ላይ መሸነፋቸውን ዘርዝሯል፡፡ ከጦርነቱ በፊት ወደ ኢትዮጵያ የከብት በሽታ እንዲገባ በማድረግ አገሪቱን ለማዳከም መጣራቸውን ጠቁሞ፣ የእነሱ ሃሳብ እንዲህ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የሰራዊታቸውን ሞራል በቀረርቶና ፉከራ በመገንባት፣ የጣሊያንን ሞራል በማድቀቅ እንደተወጡት ተናግሯል፡፡  
ጀነራል በራቴሪያ እንዴት ወደ ጦርነት እንደገባና በጦርነቱ ላይም ለማሸነፍ እንደበቃ የዘረዘረው ሕፃን ቅዱስ፤  ከ1928-1933 በነበረው ጦርነት ኢትዮጵያ ማሸነፏን፤ ሮም ላይ መሶሎኒ በራሱ ዜጎች ተዘቅዝቆ መሰቀሉን አስታውሷል፡፡ “እኛ ያሸነፍነው በአውሮፓ አለች የተባለች ኃያል አገር ጣሊያንን ነው፤ ልንኮራ ይገባል” ብሏል ህጻን ቅዱስ፡፡
ዶ/ር ወዳጄነህ መሐረን፤ የእንግሊዝኛው “ሬነሰንስ” በአማርኛ ሕዳሴ የሚል ትርጉም እንደተሰጠው፤ሕዳሴ ማለት ደግሞ ወደ ነበሩበት ክብር መመለስ ብቻ ሳይሆን፣ በክብር ላይ ክብር ጨምሮ ከቀደመውም በልጦ መገኘት መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የብርሃኑ ዘሪሁንን፣ የሃዲስ ዓለማየሁን፣ የበዓሉ ግርማን ሥራዎች በማንበባቸው፣ እነዚህ ጸኃፍጽ ደግሞ  የሥነ ፅሑፉን ደረጃ ወደ ላይ ስለሰቀሉት፣ የዛሬ ደራሲያንን ሥራ ለማንበብ መቸገራቸውን አልሸሸጉም፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲን ደረጃ ከፍ አድርጎ የሰቀለው ከመሆኑ አንጻር፣ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን የሚመሩ ወገኖች እዚያ ደረጃ ለመድረስ እግዚአብሔር ይረዳቸው ዘንድም ተመኝተዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ፣ንጉስ ነገስቱ አሜሪካን በጎበኙ ጊዜ ባደረጉላቸው አቀባበል፤ “እርስዎን በተቀበልንበት ክብር የምንቀበለው ሌላ የአገር መሪ እንደማይኖር ላረጋግጥልዎ እፈልጋለሁ” ሲሉ መናገራቸውን፤ ዶ/ር ወዳጄነህ አስታውሰዋል፡፡  በዲፕሎማሲው መስክ ሕዳሴ የሚሆነው ከዚህ ከላቀ  ብቻ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡  አድዋን ስንዘክር የምናስበው በዚያን ጊዜ የነበረው ሕዝብ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ ሳይል አገሬ ተነካች ብሎ የተመመ በመሆኑ፣ የሕብረትንና የአንድነትን ጉዳይ አባቶቻችን ከፍ ካለ ቦታ ላይ ሰቅለውታል፤ እኛ ግን በብሔር ምክንያት ተከፋፍለናል፤ሲሉ ቅሬታቸውን ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡
በአፈ ታሪክ የትግራይ ሽማግሌዎች፣ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ጣሊያኖች፣ ወደ ሰባ  ሺህ የሚጠጉ ሰው መሆን አለመሆናቸው የማይታወቅ ፍጥረታት ይዘው መምጣታቸውን፣ እነዚህ ፍጥረታት ጠዋት እየወጡ ማታ ወደ ማደሪያቸው ሲገቡ እንደነበር እንደሚናገሩ የጠቆሙት ሌላዋ ተናጋሪ ዶ/ር መስከረም ለቺሳ፤ በአድዋ ጦርነት የተሸነፈው የጣሊያን ጦር ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዓይነቱ መንፈስ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያሰቡት በ15ኛው መቶ ዓመት የጣሊያን ህዳሴ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደነበር ያወሱት ዶ/ር መስከረም፤ በክርስቶስ ስም መጥተናል ብለው  ኢየሱሳዊያንን መላካቸውን፤ በአፄ ሱስኒዮስ መንግስቱን የካቶሊክ እምነት ተከታይ አድርገውት፣ እሱም በብዙ ደም መፋሰስ መወገዱን አስገንዝበዋል፡፡ “በኦሪት ብዙ ጣኦታት ነበሩ፤ የዚህ ዘመን ጣኦት ደግሞ ገንዘብ ሆኗል” ያሉት ዶ/ር መስከረም፤ ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ምድር ሴተኛ አዳሪነትና መጠጥ ቤት እንዲስፋፋ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
“አፄ ምኒልክ በገሃድ የመጣውን ጦር ብቻ ሳይሆን ስውሩን የጨለማ መንፈስ አሸንፈው፣ የጥቁር ሕዝብ በነጮች ላይ ለነፃነት እንዲነሳ እንዳደረጉ ሁሉ፤ አሁን ኢትዮጵያውያን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ቀርበን ድል ብናደርግ፣ በዚህ ድላችን ነፃ የምናወጣው ደግሞ ነጮችን ከጨለማው መንፈስ ይሆናል።" ብለዋል ዶ/ር መስከረም፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው፤ በአድዋ ድል በዓል ላይ እየተገኙ ንግግር ሲያደርጉ 14 ዓመት እንደሆናቸው፤ ድሉ የአንድነትና የክብር ድል እንደሆነ፤ ሰዎችም ለዚህ ድል መስዋዕነት መክፈላቸውን አስታውሰው፤ የጦርነቱ ምክንያትም ማታለል እንደነበር አውስተዋል፡፡
“ጥቁር ሕዝብ በቆዳ ቀለሙ ብቻ እንደ ከብት ይሸጥ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የነበሩት ሰዎች ሰው በቆዳ ቀለሙ አይመዘንም፤ ሰው ሰው ነው ብለው ተነሱ፡፡ ጣሊያኖች ከፍተኛ መሳሪያ ነበራቸው፤ በእሱ ተማምነዋል ኢትዮጵያዊያኖች ደግሞ ከእነሱ የበለጠ መሳሪያ ነበራቸው፡፡ እሱም ኢትዮጵያዊነታቸው፤ ማንነታቸው፤ ክብራቸውና አንድነታቸው ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ ለጦርነቱ ክተት ሲያውጁ፣ ያገሬ ሰው ብለው ነው ያወጁት፡፡ ከአራቱ  ማዕዘን ሁሉም ወደ ጦርነት ግንባር ዘመተ” ብለዋል አቶ ኦቦንግ፡፡
አቶ ኦቦንግ፤ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን “በሕግ አምላክ” የሚለው ቃል፣ ከዛሬው ክላሽ ጠመንጃ፣ ከፖሊስና ከመከላከያ በላይ ይፈራ እንደነበር፣ ያ ትውልድ ለህግ ከፍተኛ ቦታ ይሰጥ እንደነበር አውስተው፣ ዛሬ ህግ የሚያከብር ጠፍቶ እርስ በእርስ እየተገዳደልን ወገኖቻችን እየተፈናቀሉ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም፤ ከወለጋ ተፈናቅለው ጃንሜዳ ሰፍረው የነበሩ ወገኖች፣ በአውቶብስ ወደ ደብረብርሃን መላካቸውን፣ እነሱ አንቀበልም ስላሉ ወደ ባሌ እንዲሄዱ መደረጉን ጠቅሰው፤ "የአድዋ ጦርነት የተደረገውና ድሉ የተገኘው ለዚህ ነወይ? እኛስ ምን እየሰራን ነው?" ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
“መልኬን ያገኘሁት መርጬ አይደለም፤ ኢትዮጵያዊነትን የወሰድኩት ከማንም ሰው አይደለም፤ ከፈጣሪ የተሰጠኝ ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያዊነት ስለ አብሮነት እቆማለሁ” ያሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ፤ አንድ የቡና ጀበና አንስተው ለታዳሚው ካሳዩ በኋላ፣ ጀበናውና የኢትዮጵያ ካርታ ያላቸውን  መቀራረብ በማስረዳት፤ የጀበና ቡና ሰዎችን ከቅርብም ከሩቅም እንደሚያገናኝ ገልጸዋል። ዛሬ በጀበናው አብረን እየጠጣን ሳይሆን እየተጣላንበት መሆኑን፣ ቡናውን የያዙት ደግሞ ባለስልጣናት መሆናቸውን አነፃፅረው ወደ ራሳቸው በመመለስ “ይህን ጀበና የያዘው ኦባንግ ነው፤ የያዘው በማስመሰል ከሆነ ጀበናው እንዲህ ይሰበራል” በማለት ጀበናውን ጥለው ሰብረውታል፡፡ “አንዴ ከወደቀ በኋላ መመለስ አንችልም፤ ሰው ሆናችሁ ኑሩ.፤ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!” ሲሉ በማስጠንቀቂያ የተጠቀለለ ምክር ለግሰዋል፡፡  
"ኢትዮጵያ አትፈርስም" የሚለው ንግግር ያልተዋጠላቸው መጋቢ ሐዲስ እሸቱ፤ የክርስቲያኗ አገር ሶሪያ፣ ሀብታሟ ሊቢያ መፈራረሳቸውን በማስታወስ እሳቤውን  ሞግተዋል፡፡ መጋቢ ሀዲስ፤ አፄ ምኒልክ ያንን ሁሉ ሠርተው አድዋ ላይ ማሸነፋቸውን፣ ኢትዮጵያዊያን አርባ ዓመት ሙሉ ስለ ድሉ ግጥም ሲደረድሩ፣ ጣሊያኖች መድፍና አይሮፕላን  ሰርተው ዳግም መውረራቸውን፤ አርበኞች አምስት ዓመት ታግለው ግን ነፃነት ማስጠበቃቸውን አስገንዝበዋል። ሆኖም አሁንም የቀጠለው ያው የጦርነት ትረካ መሆኑ ያሳዝናል ያሉት መጋቢ ሃዲስ፤ አባቶቻችን ተዋግተው ሲያሸንፉ እኛ ሳንዋጋ መሸነፋችንን በምጸት ተናግረዋል፡፡
"የድሮ ኢሕአዴግ  27 ዓመት ሙሉ ስለ 17 ዓመቱ ትግል ሲያወራ ከረመ። የአሁኑ ስለ 27 ዓመቱ እያወራ ነው፤ በዚህ ሌላ 27 ዓመት እንዳይባክን፤ ብዙዎች ሥልጣን ሲይዙ ማንበብ ያቆማሉ፤ በዚህም አእምሮአቸው ባዶ እየሆነ ቀፈታቸው እየገፋ ይሄዳል" ብለዋል፤ መጋቢ ሀዲስ፡፡
“እግዚአብሔር የለም የሚል ሰው በሰማይ ይጠቃል፤ ኦርቶዶክሶች፣ ሙስሊሞች፣ ፕሮቴስታንቶች፣ ካቶሊኮች ወይም እምነት የሌላችሁ ወንድሞች፤ ኢትዮጵያ የለችም ማለት አትችሉም፡፡ እኛ ስለምንቀጣበት ያንገበግበናል፡፡ ይህን የምናገረው ለሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ብዬ አይደለም፡፡ ዛሬ በሰላም ወጥተን በሰላም መግባት ስላለብን ነው” ሲሉ አስረድተዋል፤ መጋቢ ሀዲስ በንግግራቸው፡፡
መምህር ዘበነ ለማ በበኩሉ፤ ጥቁርን ሕዝብ በሙሉ “ኢትዮጵያዊያን” እያለ የሚጠራ የአንድ ደራሲ ስም ጠቅሰው፤ ይህ ሰው ኢትዮጵያዊያኑን "ለእውነት ለፍትህና ለድል አይናችሁን ክፈቱ" እያለ ይጣራ እንደነበር አስታውሰዋል። እሳቸውም፤ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ለፍትህ ለእውነትና ለጥበብ አይናቸውን እንዲከፍቱ አሳስበዋል። ብዙዎች አዛኝ ሩህሩህ ናቸው ብለው የሚሏቸውን አፄ ምኒልክ፣ "ጡት ቆረጡ" ብሎ የፃፈው ማነው? ሲሉ ጠይቀው፣ ፀሐፊው ጣሊያናዊ መሆኑ በመግለጽ መልሱን ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም፤ በሰው ላይ እንስሳዊ ባህሪው በሰለጠነ ጊዜ የሚናገረው የሚያስደነግጥ እንደሚሆን ጠቁመው፤ አንዳንድ ጊዜ #ሊቅነት ሊጥነት; ይሆናል፤ ብለዋል፡፡
በአይሁድ እምነት ውስጥ የኢትዮጵያ ሃሳብ መኖሩን፣ በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ የግዕዝ ቃላት እንደሚገኙ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ  ሃይማኖቱን ለመመስረት በተነሳ ጊዜ፣ ጴጥሮስ የሚባለውን ኢትዮጵያዊ ማማከሩን መምህር ዘበነ ጠቅሰው፤ ፈረንጆች ኢትዮጵያን ማጥፋት የሚፈልጉት እነሱ እንዳሻቸው የሚያደርጓት አገር ባለመሆኗ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያዊያን ክብራቸውን ማሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ሥልጣን ስላላቸው ብቻ ህዝብ የሚከተላቸው መሪዎች እንዳሉ ሁሉ፤ በጥቂት ሰዎች የሚወደዱ መሪዎችም መኖራቸውን፣ አንዳንድ መሪዎች ደግሞ ሰዎችን በዘር በቀለም ወይም በእምነት ሳይለዩ፣ ሁሉንም በእውቀቱ በብቃቱ የሚለኩ፣ በሥራው እንዲያድግ  የሚያደርጉ ለሰብአዊ ልማት ቦታ የሚሰጡ መሆናቸውን አመልክተው፣ ከፍተኛው የመሪነት ደረጃ  “ፒናክል” ተብሎ እንደሚጠራ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር ለመሪነት ደረጃ የደረሰ መሪ አለመኖሩን መሆኑን ጠቁመዋል። በመቀጠልም ዛሬ ኢትዮጵያን እየጎዳ ያለው ዘረኝነት መሆኑን፣ "እኔ አማራ ኦሮሞ፣ትግሬ፣ ጉራጌ ወዘተ ስለሆንኩ፣ የእኔ ወገኖች ሥልጣን ማግኘት አለባቸው" የሚለው እሳቤ ከአድዋ መንፈስ ጋር የሚጣጣም አለመሆኑን መምህር ዘበነ አስገንዝበዋል፡፡
የሰው ንቃተ ህሊና  እጅግ ከፍ ወዳለው (ሱፐር-ኮንሺየስ) ደረጃ ሲደርስ ለሰው ሁሉ የሚያስብ የሚጨነቅ እንደሚሆን መምህር ዘበነ አውስተው፤ ያኔ ከትግሬ እናት ጋር፣ ከአማራ እናት ጋር፣ ከጉራጌ እናት ጋር ወዘተ አብሮ  ማልቀስ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
አድዋን ሲያስቡ የሚመኟት ኢትዮጵያን የገለጡት፤ “በአስመራ ማንም አያልቅሱብሽ፤ በሐረር በወለጋ በትግራይ ማንም አያልቅሱብሽ፣ የሰማኒያ ዓመት ባልቴት አያልቅሱብሽ፡፡ ወደዚሁ ዓለም ለመኖር የሚመጣ ሕፃን አያልቅስብሽ--- ኢትዮጵያ፤ የቂል በርሽን (ፉሊሽ ኮርነር) ዝጊልን። በዚህ በር ከመሪዎች አንደበት የሚወጣ መጥፎ ቃል ነው ህዝቡን የሚያጋድለው። ኢትዮጵያ እንደ ጀበናው አትሰባበሪም፤ የሚውድቁብሽም የምትወድቂባቸውም ይጠፋሉ” ብለዋል፤ መምህሩ፡፡ የመጨረሻ ተናጋሪዋ አርቲስት አስቴር በዳኔ ትመስለኛለች፡፡ አስቴር ወደ አዳራሹ ለመርሃግብሩ ስትመጣ፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ለብሳ እንድትሄድ የመከሯት እንደነበሩ ጠቅሳ፤ አለብስም እንዳለቻቸው  ለታዳሚው ገልጻለች፡፡ በመቀጠልም፤ ብዙ ሰው  "ወራጅ አለ" እያለ ከኢትዮጵያዊነት እየወረደ መሆኑን፣ በኢትዮጵያዊነት ፀንተው የዘለቁት  ጥቂቶች መሆናቸውንም  ገልጻለች፡፡
የአድዋ ድልና ክብር በ1983 ዓ.ም መሞቱን፣ በዚህ ሰዓት የአድዋ ድልን ለማክበር የማንመጥን መሆናችንን ሳታድበሰብስ ሃቁን ያፈረጠችው ሲሆን  በአሁኑ ጊዜ አገር አልባ ትውልድ መፈጠሩን፣ መኖሪያ አጥተው የሚንከራተቱ ወገኖች እንዳሉም በምሬት ተናግራለች፡፡ መድረኩ ላይ ቆማም አፄ ምኒልክን፣ እቴጌ ጣይቱን እንዲሁም ኢትዮጵያን  ይቅርታ የጠየቀችው አርቲስቷ፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ የምትለብሰው ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ብቻ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
የዘንድሮ የአድዋ ድል በዓል አከባበርን በተመለከተ ለሁለት ሳምንት ያቀረብኩላችሁን ቅኝት በዚሁ ቋጨሁ፡፡ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁበት እምነቴ ነው፡፡ የከርሞ ሰው ይበለን!

Read 4874 times