Saturday, 05 March 2022 04:09

“የማይሰበረው” በድጋሚ ታትሞ ለገበያ ቀርቧል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው የተጻፈውና በበርካታ አንባብያን ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የተሰኘው የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ በድጋሚ ታትሞ ከሐሙስ ጀምሮ በገበያ ላይ ውሏል፡፡

“የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” በአዳዲስ የቢዝነስና የስራ ፈጠራ ሃሳቦች አፍላቂነታቸውና በፈር-ቀዳጅ ኢንቬስተርነታቸው በሚታወቁት ኢትዮጵያዊው ኢኮኖሚስትና ባለሃብት በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የሕይወት ታሪክና ስራዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን፣ ለብዙዎች ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ የሚሰጥ ተወዳጅ መጽሐፍ ነው፡፡

የአቶ ኤርሚያስ አመልጋን የልጅነት ሕይወትና አስተዳደግ፣ የወጣትነት ዘመንና የትምህርት ቆይታ እንዲሁም ወደ አሜሪካ አቅንተው ከዘበኝነትና የዩኒቨርሲቲ ተማሪነት እስከ ግዙፉ የአለማችን የፋይናንስ ማዕከል ዎልስትሪት የኢንቨስትመንት ባንኪንግ ስመጥር ባለሙያነት የዘለቁበትን የረጅም አመታት ጉዞ የሚያስቃኝ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ከ20 አመታት በላይ የተጓዙበትን በስኬትና በውድቀት የታጀበ፣ ፈተናና ውዝግብ ያልተለየው ረጅም የሕይወት ጎዳናም በዝርዝር ይዳስሳል፡፡   

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተለይም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የወጠኗቸውን አዳዲስና ሰፋፊ የፋይናንስ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕቅዶቻቸውን ከዳር ለማድረስ ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ጉዞ ውስጥ ያጋጠሟቸውን እሾህ አሜካላዎች፣ የተጋፈጧቸውን ፈተናና እንቅፋቶች በዝርዝር የተረኩበት መጽሐፉ፣ ከባለታሪኩ የግልና የስራ ሕይወት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ተሰምተው የማይታወቁ በርካታ አዳዲስና አነጋጋሪ መረጃዎችን ያካተተ ነው፡፡

በሁለት ክፍሎች ተከፋፍሎ የቀረበውና 12 ዋና ዋና ምዕራፎች ያሉት “የማይሰበረው - ኤርሚያስ አመልጋ” የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፣ “ማረፊያ አንቀጾች” እና “ድህረ-ታሪክ” የሚሉ ተጨማሪ ንዑሳን ክፍሎችን ጨምሮ አጠቃላይ የገጽ ብዛቱ 394 ሲሆን፣ በድጋሚ ታትሞ ከሐሙስ ጀምሮ በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ መጽሐፍት መደብሮችና በአዟሪዎች ከአርብ ጀምሮ በገበያ ላይ ውሏል፡፡


ጸሃፊው ደራሲና ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው ከዚህ ቀደም “መልስ አዳኝ” እና “ባቡሩ ሲመጣ” የተሰኙ የአጫጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን፣ ለ54 ተከታታይ ሳምንታት በፋና ኤፍ ኤም 98.1 የተላለፈውንና “ስውር መንገደኞች” የተሰኘውን ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ በደራሲነትና በተዋናይነት ለአድማጭ ማብቃቱም ይታወሳል፡፡

Read 11963 times