Saturday, 12 February 2022 12:02

ፍየል - አላቢ ጡት አለስላሽ ቀጠረች!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     አንድ የዐረቦች ተረት አንዲህ ይላል።     
አንዲት ቆንጆ ሚስት የነበረችው ነጋዴ ነበር ይባላል። ነጋዴው የንግድ ሥራውን ለማከናወን ከአገር አገር ይዞር ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ለስራ ሲወጣ፣ ቆንጆ ሚስቱን ለመወዳጀት ይፈልግ የነበረ አንድ ሌላ ዐረብ በቤቱ አካባቢ ይንጎራደዳል።
ለካ ሚስቲቱም ይህንኑ ዐረብ በሰፈር ውስጥ ስታየው፣ በዐይኗ ወዳው፣ በልቧም ፈቅዳው ነበርና ቤቷ በረንዳ ላይ ሆና ታስተውለው ነበረ። ዐረቡ ሲንጎራደድ ውሎ ይሄዳል። ቆንጅዬቱም ስታየው ውላ ትገባለች።
መቼም ከሴት ብልሃት አይጠፋምና በተለመደው የመተያየት ክንዋኔ ወቅት ትንሹን ወንድ ልጇን “የማን ቤት ጠፍቶህ ነው” ጠርታ፤ በልና ጠይቀው” ትለዋለች።
ልጇም፤
“ቤት እንደጠፋበት በምን አወቅሽ?” ሲል ይጠይቃታል። እናትየውም፣
“ሰው እንዲህ ሰፈር ለሰፈር የሚንከራተተው ቤት ጠፋበት ነው” ስትል ትመልስለታለች።
ልጇም፣ “እንግዲያው ሄጄ ልጠይቀው”  ብሎ ወደ አረቡ እየሮጠ ሄደና፤
“የማን ቤት ጠፍቶብህ ነው?” አለፈ ዐረቡን ጠየቀ። ዐረቡም፣
“የአንድ ቆንጆ ዘመዴ ቤት ጠፍቶብኝ ነው” አለ። ልጁም፤ ይህንኑ መልሶ ይዞ ሄደ፣ ለእናቱም ነገራት።
እናትዬውም፣ “እንግዲያው ጥራው። እኔ አመለከተዋለሁ። የቆንጆይቱን ስም መጥቶ ይንገረኝ።” አለችና ልጇን ላከችው።
ልጁ የታዘዘውን አደረገ። ዐረቡ ከልጁ ጋር እየተመቸው ሳለ ለልጁ ከረሜላ ሰጠው። ´አመሰግናለሁ´ እንደማለት ነው። ልጁ ከረሜላውን እየላጠ ወደ ጓዳቸው ገባ።
አረቡን ሴትዮዋ እንዲህ ስትል ጠየቀችው።
“እኔ ስሜ አልማዝ ይባላል፤ ያንተ ዘመድስ ስሟ ማነው?”
“ስሟን አላውቀውም። ስም ያላትም አይመስለኝም”
“እንዴት? ታዲያ በምን ትለያለች?”
“በቁንጅናዋ”
“ብዙ ዓይነት ቆንጆኮ ነው ያለው። ቢያንስ ልዩ ምልክት ያስፈልጋል?”
“ልዩ ምልክትማ አላት”
“ምን መሳይ?”
“አንቺን መሳይ!”
ይሄ የመግባባታቸው መጨረሻ ሆነና አብረው አመሹ፤ አብረው አደሩ። ወዳጇ ሆነ!
ከዚህ ቀን ጀምሮ ባሏ በወጣ ቁጥር ልጇን ወደ ወዳጇ ትልከዋለች።
አንድ ቀን እንደ ልማዱ ወዳጇ መጥቶ እያለ፣ ባሏ እቃ እረስቶ ኖሮ ተመልሶ መጣ። ዐረቡ የሚገባበት ጠፋው። ሴትዮይቱም በጣም ደነገጠች። አንድ ዘዴ መፍጠር ነበረባትና ወዳጇን ወደ ጓዳ ይዛው ገባች። ከዚያም አንድ ቁምጣ (ከረጢት) ስንዴ አምጥታ፤
“በል ይሄን እየፈጨኽ ቆይ” አለችው።
የፈረደበት ውሽማ መፍጨት ጀመረ።
ባል ግን ወደ ቤት ገብቶ በቶሎ አልወጣም። “ቡና አምሮኛል፣ እስቲ ቡና አፍይ!” አላት።
የፈረደበት ወዳጅ ዐረብ ስንዴ መፍጨቱን ቀጠለ። ላብ በላብ ሆኗል። ሴትዮዋም ቡና ማፍላቷን ቀጠለች። ባል እስከ ሶስተኛ ቡናውን ጠጥቶ፣ ዕቃውን ይዞ ወደ ገበያው ሄደ። ወዳጇም አንድ ቁምጣ ስንዴ ፈጭቶ፣ በላብ ተጠምቆ ከጓዳ ወጣ። እንደ ማጽናኛ ጥቂት አጫውታው፣ ባሌ ድንገት ተመልሶ እንዳይመጣ ብላ አሰናበተችው።
እንደጠረጠረችው ነጋዴው ባሏ ተመልሶ መጥቶ ሰነባብቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ሚስቲቱም ፈጥና ልጇን ወደ ወዳጇ ላከችው።
ልጁም ዐረቡን “እማዬ ና ብላሃለች” አለው።
ዐረቡ ውሽማም፤
“አሃ ያልማዝ ሊጅ! የፈጨሁት ስንዴ አለቀ?” አለ ይባላል።
*   *   *
በድንገቴና በሰፍጥ በሌብነት” የምንሰራው ስራ ሁሉ መጨረሻው አያምርም። በአጋጣሚ በመጠቀም የሌላውን ሐቅ መውሰድ ያስከፍለናል። ሀቅ የሕዝብና የአገር ሲሆን ደግሞ የበለጠ ዋጋ ያስከፍለናል። “የሰው ሚስት ይዞ የተኛ እንቅልፍ የለውም” የሚለውን ተረት አንርሳ!
“ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” የሚለውንም ተረትና ምሳሌ አንዘንጋ። አንዱ የገነባውን ሌላው ካፈረሰውም፣ ጉዳቱ ዞሮ ለአገር ነው! አንዱ ለውጥ ሲቆፍር፣ የሌላውን የስልክ ኬብል ከበጠሰው ጉዳቱ የሁላችንም ነው!
ልማት የሁላችንም ጥቅም እንደሆነ አይካድም። ሆኖም ልማት ሐቀኛ ልማት የሚሆነው ለሁሉም/ታስቦ የተሰራ እንደሆነ ነው። አድልዎ የሌለበት ዕድገት ሲሆን ነው እኩል የሀብት ክፍፍል የሚኖረው።
እንጂ አንዱ የበኩር-ልጅ፣ አንዱ የእንጀራ-ልጅ ተደርጎ ከታየ፤ ወገንተኝነት፣ የዘር- መድልዎ፣ ኢ-ፍትሐዊነትና ከኢዲሞክራሲያዊነት በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚየዊም መልኩ አፍጦ መታየቱ አሌ አይሉት ነገር ነው። በዚያ ላይ ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት ይወጣ አንጂ ሌላ ወገናዊ ድጋፍ የሚሻ ከሆነ፣ ሌላ ካድሬ የሚመለምል ከሆነ፣ ሙያዊ ብቃት ሳይሆን የአድር-ባይና አሸርጋጅ፣ “የሆያ ሆዬ” አውራጅና የጎሽ-ጎሽ ኮሚቴው ብዛት፣ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየቢሮካራሲያዊ ተቋሙ፣ በየግል ሴክተሩ ይናጥጣሉ! እጅና ጓንት፣ አፎትና ስለት፣ ሙሽራና ሚዜ፣ እየሆኑ በየስራ ዘርፉ ውስጥ ያሉ አያሌ የድል አጥቢያ አርበኞች፣ ብቅ ማለት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። በብዛት የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ ሆኗል የየሸንጎው፣ የየስራ ቦታው፣ የየስብሰባው ቅኝት! ከሁሉም የባሰው ግን ራሱ መስራት ያለበትን ስራ ሌላ ዘመድ አምጥቶ፣ ሌላ አቻ- ጋብቻ አስገብቶ፣ የሚኖረው አለቃ ነው።
እንግዲህ ያለውን ሁኔታ አንድ ተረት ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል፡- “ፍየል አላቢ ጡት አለስላሽ ቀጠረች!”



Read 11335 times