Monday, 14 February 2022 00:00

ነፃ ቃላት፣ በነጠላ - ያግባባሉ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

ብዙ የፖለቲካ ቃላት፣ ስሞችና ቅጽሎች፣ ለወትሮ አስቸጋሪ ናቸው። ቢሆንም፣ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ አላማቸውን ለይተው ለማሳወቅ፣ ሃሳባቸውን በግልፅ ለማወጅ፣ ወደ ቃላት ሽሚያ መሽቀዳደማቸው አልቀረም። ስያሜና ለማሳመር መፈክር ይፎካከራሉ። የፓርቲያቸውን ስም ሲመርጡ፣ የፖለቲካ ሃሳባቸውን ሁሉ ጠቅልሎ እንዲገልፅላቸው የሚመኙ ይመስላል። ቅፅሎችን ይደራርባሉ።
ዲሞክራሲያዊ፣ ፌደራላዊ፣ ሪፑብሊካዊ፣ ሕዝባዊ፣ ሶሻሊስታዊ፣ ማርክሳዊ፣ ብሔራዊ፣ ሶሻል፣ ሊበራል፣ ወዛደራዊ፣ …የተራማጅ፣ የአንድነት፣ እኩልነት፣ የፍትህ፣ የብልጽግና።
የፓርቲ ስም ውስጥ፣ ብዙ ቅፅል ማግበስበስ ካልተመቻቸው፣ መፈክሮች ላይ ጥማታቸውን ይወጡታል።
በእርግጥ፣ አንዳንዱ ቅፅል፣ እንዲሁ ለስም ያህል የሚደርቱት፣ የአላዋቂዎች ወግ ነው። ፋሽን የሚመስላቸውን ይኖራሉ።
አንዳንዶቹ ግን፣ ዝንባሌያቸውን ለመግለጽ ነው- የፖለቲካ ቃላትን የሚመርጡት። ለስያሜና ለመፈከር፣ ቅፅሎችን ያወዳድራሉ። አማርጠው፣ ለስያሜና ለመፈክር፣ የተለያዩ ቃላትን ሲጠቀሙ ለክፉም ለደጉም ነው። ጥሩም ሆነ መጥፎ፣ አላማና ሃሳባቸውን ለይተው ለመግለፅ ነው።
የሚጓዙበት መንገድና መድረሻ ከወዲሁ ለማሳየት፣ ለማስጎምጀት ወይም ለመዛት ነው። የሚፈልጉትን የለውጥ አይነትና ውጤት፣ ምንን እንደሚገነቡ፤ ምንም እንደሚያፈርሱ ለማወጅ፤ እወቁልኝ ለማለት ነው። ነባሩ ወይም ያረጀው ስርዓት ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚያስወግዱት፤ ወደየትኛው አይነት ስርዓት እንዴት እንዴት እንደሚለውጡት፣ ወይም በምትኩ ምን የመሰለ አዲስ ስርዓት እንደሚፈጥሩ ለማስረዳት ይጣጣራሉ።
ይሄ መጥፎ አይደለም።
ሃሳባቸውን፤ አላማቸውንና መንገዳቸውን በግልፅ ከተናገሩ፣ ጥሩና መጥፎን ለመለየት፣ ክፉና ደጉን ለመዳኘት ይጠቅመናል። ለመደገፍም ለመቃወምም፤ ስህተትን ለመተቸትም፣ የማስተካከያ ሃሳብ ለማበርከትም፣ ለመምረጥም፣ …. በቅድሚያ ሃሳባቸውን፣ አላማቸውንና መንገዳቸውን በግልፅ ማወቅ ያስፈልጋል።
እናም የፓርቲዎች ስያሜና የፖለቲከኞች መፈክር ውስጥ፣ ብዙ ቅፅሎች ቢደራረቡ፤ መጥፎ አይደለም።
በእርግጥ፣ የፓርቲዎች ስም ላይ ቅጽል በተጨመረ ቁጥር፣ መጥፎ ምልክት ሊሆንብን ይችላል። ብዙ ጊዜ አጋጥሞናል።
ሪፐብሊክ በሚለው ቃል ላይ፣ ሕዝባዊ ወይም ሶሻሊስት የሚል ቅጽል ለጥፎ የሚመጣ ፓርቲ፣ ጥሩ አላማ የያዘ ፓርቲ አይሆንም።
ግን፣ ለዳኝነት እንዲመች፣ የአላማውን ምንነት የሚጠቁም ቅጽል፣ በፓርቲው ስያሜ ወይም በመፈክሮች ላይ በግልፅ ማሳየቱና ማወጁ ጥሩ ነው።
 አንዳንዴ፣ “ምናለ፣ ቅፅሉን በተወው!” ሊያስብለን ይችላል። ቅፅል ማብዛት ራሱ፣ ዋናው ጥፋት መስሎ ቢታየን አይገርምም።
“ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ” የሚለው ስያሜ፤ ከመነሻው፣ ለብቻው፣ በነጠላው ከታየ፣ ምርጥ መልዕክት የያዘ አይደለም። ህግ የማይገዛው የስርዓት አልበኝት ትርምስን ያስከትላል። የእለት ተእለት የሕዝብ ስሜት ምንኛ እንደሚገለባበጥ ታውቁ የለ! ወዲህ በኩል ሲንደረደር የዋለ ናዳ፣ ወዲያ በኩል የሚንጋጋ መንጋ ሆኖ ይመሻል። “ዲሞክራሲ” በነጠላ፣ ያለ ቅጽል፣ የዘፈቀደ ቀውስን ይጋብዛል የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው።
በእርግጥም በለዘብታ የሚተረጉሙት መኖራቸው አይካድም። የዜጎች ምርጫ፣ የህዝብ ፍላጎት፣ የብዙሃኑ ፍቃድ፣ …. የሚሉ ትርጉሞችን ሊይዝ ይችላል። ቅጽል ሲታከልበትስ?
 “ሊበራል ዲሞክራቲክ ፓርቲ”፣ የሚል ስያሜን ተመልከቱ። …. ድሮ ድሮ፣ የግለሰብ ነፃነትን (ማለትም የግለሰብ) የዒኮኖሚ እና የህሊና ነፃነትን ለማስከበር ያለመ፣ የዜጎችን ፈቃድ የሚያንፀባርቅ የምርጫ አሰራርን የሚከተል የፖለቲካ ሃሳብ፤ “ሊበራል ዲሞክራሲ” የሚል  ስያሜ ነበረው።
“ዲሞክራሲዊ” በሚለው ቃል ላይ ሌላ ቅጽል ቢጨመርበትስ?
“ሶሻል ዲሚክራቲክ ፓርቲ”፣ … የ150 ዓመታት ታሪክ ያለው ስያሜ ነው- በጀርመኑ አንጋፋ ፓርቲ የተጀመረ። መልዕክቱስ? የሕዝብን ፈቃድ የሚያንፀባርቅ የምርጫ አሰራርን በመጠቀም፣ ሶሻሊዝምን ማስፈን የሚል መልዕክት አለው። “በምርጫ ወደ ሶሻሊዝም” የሚል ሃሳብ የፓርቲው አላማ እንደሆነ በይፋ ለመግለፅ ነው ስያሜው የተመረጠው። የግል ንብረት የሚወረስበት፣ የግል ነፃነት የሚታፈንበት የአምባገነንነት ስርዓትን መፍጠር ነበር- አላማው። “ቅፅል” ችግር አመጣ ያሰኛል። ግን፣ ቅፅሉ አይደለም፣ ክፉ አላማን ጎትቶ የሚያመጣው። አላማውን የሚገልፅ ነው- ቅፅሉ።
“ዴሞክራሲያዊ” የሚለውን ቃል በሌጣው ከመጠቀም “ሊበራላዊ ዲሚክራሲያዊ” የሚል ባለድርብ ቅፅል  ይሻላል ብለናልኮ። በቀድሞ ትርጉሙ ማለቴ ነው። ዛሬማ “ሊበራል” የሚለው ቃል፣ ከግል ነፃነት ጋር የነበረው ፅኑ የትርጉም ቁርኝት ላልቷል፤ በአመዛኙም ተበጥሷል።
በእርግጥ፤ “ሶሻል” የሚለው ቅጽልም፤ ከድሮ ትርጉሙ ይልቅ፣ ዛሬ ላላ ለዘብ ብሏል። የሶሻሊዝም መጥፎ ዝንባሌው ባይለወጥም፤ “የግል ንብረትን እወርሳለሁ፤ የወዛደሩን አምባገነንት እመሰርታለሁ” የሚለው አላማ ግን ዛሬ ተዳፍኗል። መጥፎ አላማ ሲለዝብ ጥሩ ነው- ስያሜው ባይለወጥም።  
በእርግጥ የቃላትን ትርጉም ማለዘብና ማደብዘዝ፣ ለጊዜው ቢመች እንኳ፣ ለዘለቄታው ሁነኛ መፍትሄ አይሆንም።
ዛሬ፣ የፖለቲካ ቃላት፤… ትርጉማቸው እየላላ፣ በዘፈቀደ የሚለጠጡ የሚተጣጠፉ፣ እንደ እለቱ የአየር ሙቀት የሚዋዥቁ ሆነዋል። ፓርቲዎችና ፖለቲከኞችም፣ በየራሳቸው ስያሜና መፈክር አማካኝነት፣ ….አላማቸውን እና መንገዳቸውን ለማሳየት የሚፈልጉ አይመስሉም።  የፖለቲካ ቃላት፣ ስሞችና ቅጽሎች፣ እንደጉም ሆነዋል። አይጨበጡም። ብዥታ ድንግዝግዝ ሆነዋል። አቅጣጫቸው በግልጽ አይታይም።
 እንዲህ አይነት አዝማሚያ በርካታ ዓመታትን እንዳስቆጠረ ይታወቃል።
 ነገር ግን፣ ባራክ ኦባማ እንደ ዋና ምሳሌ ይጠቀሳሉ።
ለምርጫ የተጠቀሙበትን መፈክር አስታውሱ። “የምናምንበት ለውጥ” በሚል መፈክርና ዲስኩር፣ የብዙዎችን ስሜት ማርከዋል። ነገር ግን፣ ለውጥ የሚለው ቃል፣ የፖለቲካ  አላማቸውን፣ ግባቸውንና መንገዳቸውን ጨርሶ አይገልጽም። “ለውጥ” የሚል መፈክር፣ ምን አይነት ለውጥ እንደሆነ፣ እንዴትና በምን መንገድ እንደሚለወጥ፣ ቅንጣት ፍንጭ አያሳይም።
ቢሆንም፣ ሚሊዮኖችን አግባብተዋል፤ ተመርጠዋል።
“የምናምንበት ለውጥ!” በሚል መፈክር አማካኝነት ብቻ መስማመትና መግባባት መቻል፣ …በጣም አስገራሚ ክስተት ነው። ታዲያ፣ በአሜሪካ ብቻ ያጋጠመ አይደለም።
በአገራችንም፤ “ለውጥ” የሚል መፈክር፤ ስንቶችን እንዳግባባ አስታውሱ። ምን ዓይነት ለውጥ? የትኛውን መንገድ የሚከተል ለውጥ? በህጋዊ ወይም በነውጥ መንገድ? ስርዓት ባለው ሂደት ወይስ በቁጡ የዘመቻ ጥድፊያ?
ደርዘን ፓርቲዎች፣ እልፍ ፖለቲከኞችና ምሁራን፣ ሚሊዮን ዜጎች ዘንድ፣ ….ስንትና ስንት የለውጥ አይነቶች እንደሚቀነቅኑ፣ ማወቅም መግለፅም አያስፈልግም። “ለውጥ” በሚል ቃል ብቻ መግባባት እየተቻለ! እንደሚያግባባ ደግሞ አይተናል። በእርግጥ፤ ብዙ አያራምድም። ቢሆንም ለጊዜው ይሰራል።
ዘመነኛ የፓርቲዎች ስያሜም እንደዚያው ነው፤ መድረሻ አላማቸውንና መንገዳቸውን አይገልጽም። በደፈናው “ንቅናቄ”፣ “ድርጅት”፣ “እንቅስቃሴ” የሚሉ ስያሜዎች መጥተዋል። መሪዎችም. ራሳቸውን፣ “አደራጅ”፣ “አንቀሳቃሽ፣ ነቅናቂ” “አመቻች” እያሉ ይሰይማሉ። “Activist” “Organizer” `Facilitator`”

Read 11016 times