Print this page
Saturday, 29 January 2022 00:00

“ሞኝ የዕለቱን ብልህ የዓመቱን”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከኦዞፕ ተረቶች አንዱ በተዛምዶ ስንተረጎመው የሚከተለውን ይመስላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን የሰውነት ክፍሎች ሁሉ ተሰባስበው በሆድ ምክንያት ስለሚደርስባቸው በደል እየተመካከሩ ነው አሉ፡፡
ኩላሊት ተነሳና፡-
“በዕውነቱ እኔ ስንት የማጣራት፣ አካባቢን የመቆጣጠርና፣ የምግብና የመጠጠጥ ሚዛን የመጠበቅ ነገር በሃላፊነት ስሰራ የኖርኩኝ ነኝ፡፡ ስለሆነም የአቶ ሆድን ነገር ጠንቅቄ አስተውያለሁ።
አያ ሆድ፤ ምንም ሳይሰራ፣ በጌትነት ተቀምጦ እኛን ባሪያው አድርጎናል፡፡ ከእንግዲህ ይህ እንዲቀጥል ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ አለበለዚያ የራሴን እርምጃ እወስዳለሁ” አለ፡፡
ጉበትም በበኩሉ፡-
“ኩላሊት ያለው ዕውነት ነው፡፡ እኛ ደከመን፣ ታከተን፣ሰለቸን ሳንል ሌት ተቀን መከራችን እያየን እንፈጋለን፡፡ አብዬ ሆድ ግን ተንቀባርሮ ያላንዳች ሀሳብ ጎተራውን እየሞላ፣ ሲዝናና ይኖራል።” አለ
ሳምባም በተራው ብድግ ብሎ፡-
“ወንድሞቼ እህቶቼ ሆይ! እኔ ደግሞ እንደ ወናፍ ጧት ማታ እያቃሰትኩና፣ እያፋጨሑ፤ የዓለም ሁሉ እስትንፋስ እንደሆንኩ የመተንፈሻ ቱቦ ያለው ሁሉ ያውቃል! ጠግቦና ቁንጣን ይዞት የሚያድረው ግን አያ ሆድ ነው፡፡ በዛ ላይ የሆድ- አባል ቅርንጫፎች  
አሉት፡፡ ይሄ ነገር ለረዥም ጊዜ ሲኮረኩረኝና ሲከነክነኝ የኖረ ሐቅ ነው፡፡ ህመሜ ነው!  ዛሬ እንኳን አነሳችሁት፡፡ ሆድ ለምን ብቻውን በላ ብዬ ሳይሆን ተቃውሞዬ ለምን እኔ ጠግቤ አላድርም? እያልኩ ነው፡፡” ብሎ እየተርገፈገፈ ተቀመጠ፡፡
በመጨረሻ ልብ-ልብ ነውና የበኩሉን ሊናገር ግራውን  ቀኙንም አየ፡፡ ትከሻውን ከፍ ዝቅ አደረገና፤
“ውድ የስራ ባልደረቦቼ ሆይ! መቼም ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ፈጣሪ ያለ እንቅልፍና ያላነዳች እፎይታ እንድፈጋ ያደረገኝ አካለ-ሰብ እኔ ነኝ፣ አሁን ግዴለም ለሥራ የተፈጠርኩኝ በመሆኔ በመስራቴ አላዝንም፣ አልፀፀትምም፡፡ ግን የልፋቴን ያህል አግኝቼ እንደማላውቅ ታውቃላችሁ ያ ደግሞ የየአንዳንዱ አበሻ ትክለ -ሰውነት የሚያረጋግጠው ነው፡- የቅኔውን ሰምና ወርቅ ስናስብ! አሁንማ ኑሮንም መቋቋም አቅቶኛል፤ ስለዚህ የእናንተ አቋም የእኔም አቋም ነውና፣ ከእንግዲህ ሆድን ለመተባበር ፈቃደኛ አይደለሁም!
አንድ አደራ የምላችሁ ነገር ግን፣በሆድ ምክንያት ምንም ዓይነት ችግር ቢመጣ እንዳንካካድ ነው አደራዬን ለማጥበቅ ነው፡፡ ይልቁንም አንዳችን ስንደክም ሌሎቻችን በመተጋገዝ እርዳታችንን መለገስና እንድንጠናከር ማድረግ ነው!”
የልብን ንግግር ሁሉም በጥሞና አዳምጠው ሲያበቁ፣ በከፍተኛ ጭብጨባ መቀበላቸውን አረጋገጡ “እነ ጡንቻ መሀል-አገዳ፣ህብሊ-ሰረሰር ጉልበትና እግር ሁሉ ድጋፋቸውን በጭብጨባ አረጋገጡ፡፡
ከዚህ ቀን ወዲህም ሁሉም እንቅስቃሴያቸውን ሊያቆመው ቃል ገቡ፡፡ ሆድን ለማስራብ ምንም ዓይነት እህል ውሃ ወደሱ  እንዳይጓዝ ተስማሙ፡፡
በመካከል ግን የሐሞት ከረጢት እጁን ያነሳና፤ “እኔን በድምፁ ተዓቅቦ ብታልፉኝ ይሻላል፡፡ ከእናንተ ጋር አቋም መውሰድ አይመቸኝም” አለ፡፡
“ምክንያትህ ምንድን ነው?” ተባለ
“እንዲህ ያለ እርምጃ ባንዴ የሚወሰድ አይደለም፡፡ ቀስ በቀስ የበቃ አቅም ባለው አካል ተጀምሮ ወደ መተባበር ብናመራ ጥሩ ነው፡፡ በዚያ ላይ ትላልቆቹ የሰውነት ክፍሎች ተናግረው፤ እንደ እኔ፣ እንደ ጣፊያ እና እንደ ዘርፍ፣ ያሉ አካላትን ድምጻችንን እንኳን አልጠየቃችሁንም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ጭንቅላት ያልገባበት እንቅስቃሴ ዘለቄታ እንደማይኖረው አረጋግጥላችኋለሁ! በመጨረሻ የምለውም፤ ለመሆኑ ሆድ ያጠራቀመው እህል ከሌለ፣ሌሎቻችን ምን ፈጭተን እናድራለን? የሚል ስጋት አለኝ” አለና ተቀመጠ፡፡
ይገርማል! የሰውነት ዋና ዋና አካላት የሐሞት ከረጢትን ንግግር አወገዙ!ወረዱበት!
“የፈሪ፣ የቡከን፣የወላዋይና የከሀዲ ሀሳብ ነው!” አሉ፡፡ “በዚያ ላይ  ጭንቅላትን አናስገባው ብንል፣እንዴ በኢኮኖሚ አንጻር፣አንዴ በፖለቲካ አንጻር፣ አንዴ ደግሞ በማህበራዊና ባህል አንጻር፤እያለ ከትግላችን ያዘናጋናል፡፡ ዓላማችንን በተግባር መተርጎም ብቻ ነው ያለብን፡”፡ አሉ ከዚያች ቅጽበት ጀምረው ሥራቸውን አቁመው ሆድን ማስራብ ጀመሩ፡፡
ብዙም ጊዜ ሳይቆይ ግን የሰውነት አካላቱ እየዛሉ አንድ በአንድ እየተንጠባጠቡ፣እየተዝለፈለፉ የሁሉም አቃፊ ዋርካ ዋናው ሰውነት አቅመ ቢስ ሆኖ ወደቀ! የሰውነት አካላት በሙሉ ሆድም ጭምር ተባብረው ካልሰሩ፣ ሰውነት የመንቀሳቀስ ዕድል እንደሌለው አካላቱ ሁሉ የማታ ማታ ተረዱ፡፡
*   *   *
በረዥም አገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እያንዳንዱ ለሁሉ ሁሉ ለእያንዳንዱ በሚያደርገው አስተዋጽኦ ነው ምሉዕ መሆን የሚቻለው፡፡ ሁሌ በቅጡ ለማስተዋል እንደሚቻለው ጭንቅላት ያልተሳተፈበት ጉዞ መንገድ ላይ ይሽመደመዳል፡፡
ትንሹም ትልቁም እኩል ድምጽ ያልሰጠበት ስብሰባ ፍትሐዊነት የጎደለውና ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንደሆነ አንዘናጋ፡፡ ሂደቱንና ውጤቱን በውል ያላጤነውና የጥቂቶች ድምጽ ብቻ የሚደመጥበት ስብሰባ ኮንፈረንስ ወይም ጉባኤ ለጊዜው ሞቅ ያለ ይመስላል እንጂ ከመድረሻና ግቡ አኳያ ሲጤን ፍሬ  አልባ ሊሆን እንደሚችል ብሎም ለአገርና ለሕዝብ እንደማይበጅ ማስተዋል ታላቅ ቁም ነገር ነው፡፡ በጠላት ድክመት ላይ የተመሰረተ ድልም የእንቧይ ካብ መሆኑን አንተርሳ፡፡ በማንኛው የህይወት መስክ የምናወግዘውን የምንደግፈውን ለይተን ማወቅ፣ ካወቅን በኋላም እንዴት አድርገን ውጤት ልናፈራበት እንደምንችል ማጤንና በመጨረሻም እንዴት ለእንቅስቃሴያችን ግብዓት በማድረግ የትግላችን አካል አድርገነው እንደምንጓዝ መወሰን ተገቢ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጠንቃቃ ውሳኔ ለአገርና የህዝብ ጥቅም መቀነቻ ነው፤ ያለ ትክክለኛ መርህ መጓዝም ሆነ ያለ ሰዓቱ መጓዝ “ተንጋለው ቢተፉ ተመልሶ ባፉ” ነው፡፡
ከዚህ ጋር መነሳት ያለበት አንድ ጉዳይ፣ የሃሳብና የአፍአዊ መፈክር ግትልት፣ የትም አያደርስም የሚለው ነው፡፡ ከአንደበት ይልቅ ተግባርን መሳሪያ ማድረግ ብልህነት ነው፡፡ በአገራችን ደጋግመን ያየነው የድርጅቶች ታሪክ  የሚያመላክተን፤ አብዛኛው ድርጅት ፓርቲ ወይም ፖለቲካዊ ተቋም ትኩረቱ ብዛት ላይ እንጂ ጥራት ላይ አለመሆኑን ነው፡፡ ጥራት ሲኖር አቅም እንደሚጠነክር ልብ እንበል፡፡ በብዛት የሚያምን ኃይል ችግር በገጠመው ጊዜ በቀላሉ  የሚበታተን ነው፡፡ ከፍሬ እንክርዳዱ  ከተዓማኒ አባሉ ሠርጎ ገቡ እየበዛ ጥሞና እየጎደለው፣ ሆይ ሆይ ባዩ እየበረከተ እንደሚሄድ፣ ውሎ አድሮም እጅ እግሩን ሽባ እንደሚያደርግ እናስተውል፡፡ ነባሮችም ሆኑ አዲስ መጥ ድርጅቶችና ፓርቲዎች በጊዜያዊ ድል አማን -ዘራፍ ማለት የውድቀት መንደርደሪያ መሆኑን ልብ ማለት ይገባቸዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ሲመሽም እንረዳው ሲነጋ፣ ካፍ ካፍንጫ ባልራቀ አሸናፊነት መኩራራት ሳይሆን ገና በረዥሙ መንገድ እንደሚቀር መመልከት እጅግ ወሳኝ ነገር ነው፡- የዕለቱን የበላይነት ሳይሆን ዘላቂውን ዓላማና ዒላማ፤ እንጂ! “ሞኝ የዕለቱን ብልህ የዓመቱን” ይሏል ይሄው ነው፡፡

Read 3687 times
Administrator

Latest from Administrator