Saturday, 29 January 2022 00:00

ብርሃንና ሰላም 100ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የህትመት ዋጋ መናር በጋዜጦች ህልውና ላይ አደጋ ጋርጧል


           በሰው ጉልበት በሚንቀሳቀሱ ማሽኖችና ከ15 ባልበለጡ ሠራተኞች በ1914 ዓ.ም ሥራ የጀመረው ብርሃንና ሰላም  ማተሚያ ድርጅት፤ የተመሰረተበትን የ100ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው፡፡
ባለፈው ማክሰኞ  ጥር 17 የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ፣ በኢሊሌ ሆቴል የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን መድረኩ የተዘጋጀው ማተሚያ ቤቱ የአንጋፋነቱን ያህል ጥራት ያለው አገልግሎት እየሰጠ አይደለም በሚለው ቅሬታ መነሻነት መሆኑ ተነግሯል፡፡ በፓናል ውይይቱ ላይ የማተሚያ ድርጅቱን የመቶ ዓመት ጉዞ የሚያስቃኝ ጥናታዊ ፅሑፍ የቀረበ ሲሆን ደንበኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በድርጅቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያላቸውን አስተያየትና ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ኃይለሚካኤል ብርሃንና ሰላም  ለ100ኛ ዓመት በዓሉ ባሳተመው መፅሔት ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ድርጅቱ በህትመት ዘርፍ በሃገሪቱ ቀደምት የሆነና በአሁኑ  ወቅት 100ኛ ዓመቱን እያከበረ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ቢሆንም፣ የዕድሜውን ያህል ወቅቱን እየተከተለ ራሱን በቴክኖሎጂና ዘመናዊ አሰራር አብቅቷል ብሎ መናገር አይቻልም፡፡; ብለዋል፡፡
  #ትርፋማ ሆኖ የዘለቀው አመራሮቹና ሰራተኞቹ ኋላቀር የማተሚያ ድርጅቱን ማሽኖች በውስጥ  አቅም በመጠገንና ፈጠራን አክለው ያላሰለሰ ጥረት በማድረጋቸው ነው፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡
የብርሃና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ በበኩላቸው፤ #ድርጅታችን ካስቆጠረው ዕድሜ አንጻር፣ ራሱን በቴክሎጂና በአሰራር በማዘመን የደንበኞቻችንን ፍላጎት ከማርካትና የተሟላ የህትመት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ውስንነቶች ይታዩበታል; ብለዋል፤ በመፅሔቱ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፡፡”
የማተሚያ ቤቱ  የረዥም ጊዜ ደንበኞችም ድርጅቱ የዕድሜውን ያህል ዘመኑን የሚመጥን ጥራት ያለው አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለው እንደማያምኑ ይገልጻሉ፡፡ ከድርጅቱ የሚፈልጉትን አገልግሎት በጥራትና በወቅቱ ማግኘት አልቻልንም የሚሉ ደንበኞችም ሌሎች አማራጮችን ለማየት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡
የ80 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረውን “አዲስ ዘመን” እንዲሁም ሌሎች ከ6 የማያንሱ የፕሬስ ውጤቶችን የሚያሳትመው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሰጡት አስተያየት፤ የህትመት ዘግይቶ መውጣት፣ የቀለም ህትመት የጥራት ችግርና በተለይም በየጊዜው እየናረ የመጣው የህትመት ዋጋ በህልውናቸው ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ገልጸዋል።
 አንድ ጋዜጣ ከ21 ብር በላይ እያሳተሙ በ10 ብር ለገበያ እንደሚያቀርቡ የጠቆሙት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ማተሚያ ድርጅቱ በቅርቡ ሌላ የህትመት ዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርግ ማስታወቁን  ጠቅሰው፤ የዋጋ ጭማሪው ተግባር ላይ ከዋለ የፕሬስ ህትመቶችን  ሊያቆሙ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በሳምንታዊው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ #ካፒታል; ላይ የሚሰራ አንድ ጋዜጠኛ በበኩሉ፤ የህትመት ዋጋ ጭማሪው ተግባራዊ  ከተደረገ ከ25 ዓመታት በላይ የዘለቀው ጋዜጣቸው ከገበያ ውጪ እንደሚሆን ስጋቱን ገልጧል። በቀለም ህትመት ላይ ባለው ከፍተኛ የጥራት ችግር የተነሳም ባለቀለም ማስታወቂያ የሚያወጡ ደንበኞች እንደራቋቸው  ጠቁሟል - ጋዜጠኛው፡፡
ከ25 ዓመታት በላይ በህትመት የዘለቀው የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ እንዳልካቸው ይማም በሰጡት አስተያየት፤ ማተሚያ ድርጅቱ ቀደም ሲል የቀለም ህትመት ላይ ከፍተኛ ችግር እንደነበረበት ጠቁመው፤ በተለይ ብጫ ቀለም ያለው ማስታወቂያ እንዳይመጣ የሚመኙበት ጊዜ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡
 ሌላው አሁንም ችግር ሆኖ የዘለቀው የማስረከቢያ ጊዜ ነው- ይላሉ አቶ እንዳልካቸው፡፡  “ጋዜጣ በሰዓቱ አይደርስም፤ አንዳንዴ የእሁድ ጋዜጣ መሆኑ ቀርቶ ማክሰኞ ወይም ረቡዕ ይወጣ ነበር። አሁን ያን ያህል ባይዘገይም፣ መዘግየቱ ግን ጨርሶ አልቀረም።; ሲሉ ስለ ሁኔታው ገልፀዋል፡፡
ሳምንታዊውን “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ የሚያሳትመው የአድማስ አድቨርታይዚንግ ሥራ አስኪያጅ ወ/ት ገነት ጎሳዬ፤ሌሎች የፕሬስ ተቋማት ያቀረቧቸውን ቅሬታዎች ከሞላ ጎደል ይጋራሉ፡፡ በተለይ የህትመት ዋጋ በየጊዜው እየናረ መምጣት በድርጅታቸው ህልውና ላይ ከባድ ስጋት መጋረጡን የሚገልጹት ሥራ አስኪያጇ፤ ማተሚያ ቤቱ በቅርቡ ያስታወቀውን የዋጋ ጭማሪ ተግባራዊ ካደረገ በህትመት መቀጠል አዳጋች እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል።
“በየጊዜው የሚደረጉ የህትመት ዋጋ ጭማሪዎችን እስካሁን ተቋቁመን መቀጠል የቻልነው ከማስታወቂያ በምናገኘው ገቢ ወጪያችንን በመሸፈን ነበር፤ አሁን ግን ከኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ ማስታወቂያ በእጅጉ በመቀነሱ ህልውናችን አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡” ብለዋል፤ ወ/ት ገነት ጎሳዬ፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽታሁን ዋለ፤ የህትመት ዋጋ ጭማሪውን የሚያደርጉት በዓለም አቀፍ ገበያ የወረቀት ዋጋ በመጨመሩ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት አቶ ይታገሱ ጌትነት፤ “ማተሚያ ድርጅቱ አሁን እየተጠቀመባቸው ባሉ አሮጌ የህትመት ማሽኖች ሳቢያ የሆነ ጊዜ  የፕሬስ ህትመት ቢያቆም እንዳትደነግጡ” ሲሉ ከወዲሁ አሳስበዋል፡፡
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የ100ኛ ዓመት በዓል ለሦስት ቀናት በሚቆይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን እየተከበረ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን ኤግዚቢሽኑ የማተሚያ ቤቱን የምዕተ ዓመት ጉዞ ያስቃኛል ተብሏል፡፡  

Read 2311 times Last modified on Friday, 04 February 2022 05:33