Saturday, 22 January 2022 00:00

የአለም አገራት ኢንተርኔት በመዝጋት 5.45 ቢ. ዶላር አጥተዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአመቱ 486.2 ሚሊዮን ሰዎች በኢንተርኔት መዘጋት ተጽዕኖ ደርሶባቸዋል

           ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 ብቻ በመላው አለም የሚገኙ የተለያዩ አገራት የኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋታቸው ሳቢያ በድምሩ 5.45 ቢሊዮን ዶላር ያህል ማጣታቸውን አንድ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ቶፕ ቪፒኤን የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፣ የኢንተርኔት መዝጋት እርምጃዎች ባለፈው አመት በአለማቀፍ ደረጃ የ36 በመቶ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን በአመቱ በመላው አለም የሚገኙ 486.2 ሚሊዮን ሰዎች የኢንተርኔት መዘጋት ተጽዕኖ እንደደረሰባቸው ይታመናል፡፡
በ2021 የኢንተርኔት አገልግሎትን በመዝጋት ከፍተኛ ገንዘብ ያጣችው ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ማይንማር ስትሆን 2.8 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን የጠቆመው የተቋሙ ሪፖርት፤ ናይጀሪያ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ያህል በማጣት ሁለተኛ፣ ህንድ በ582.8 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
በመላው አለም የኢንተርኔት አገልግሎት በድምሩ ለ30 ሺህ ሰዓታት ያህል የተዘጋ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜያት ኢንተርኔት በመዝጋት ደግሞ ማይንማር በ12 ሺህ 238 ሰዓታት፣ ኢትዮጵያ በ8ሺህ 864 ሰዓታት፣ ናይጀሪያ በ5ሺህ 40 ሰዓታት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን መረጃው ይጠቁማል፡፡
ለኢንተርኔት መዘጋት ቀዳሚው ምክንያት ተደርጎ የተቀመጠው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሲሆን፣ ፖለቲካዊ ውጥረትን መቀነስና የመረጃ አፈናም በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
በአመቱ በመላው አለም ለ10 ጊዜያት ወይም በድምሩ ለ12 ሺህ 379 ሰዓታት የተዘጋው ትዊተር በብዛት በመዘጋት ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን ዋትሳፕና ኢንስታግራም ይከተላሉ፡፡


Read 981 times