Print this page
Saturday, 22 January 2022 00:00

የወይብላ ማርያምን ታቦት በማስገባት ሥነ ሥርዓት ላይ በተከሰተ ግጭት የሰዎች ሕይወት ጠፋ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ሐሙስ ዕለት የወይብላ ማርያምን ታቦት በማስገባት ሥነ ሥርዓት ላይ በምእመናንና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋቱና  የአካል ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡
የወይብላ ማርያምን ታቦት በማስገባት ሥነ ሥርዓት ላይ ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ግርግርና አለመግባባት፣ የፀጥታ ኃይሎች ጥይትና አስለቃሽ ጋዝ መተኮሳቸውንና በዚህም ሳቢያ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን በሥፍራው የነበሩ ምዕመናን ተናግረዋል፡፡  
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመላው አገሪቱ የተከበረውን የጥምቀት በዓል አስመልክቶ ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ በሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን በዓሉ በመላው ኢትዮጵያ በደመቀና በሰላማዊ መንገድ መከበሩን ጠቁሞ፤ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማና በቡራዩ አዋሳኝ ወይብላ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በተፈጠረው ችግር በዓሉ መስተጓጎሉንና በሰዎች ላይም ሞትና ከባድ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ገዳመ እየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሰባኪ ወንጌል የሆኑት መምህር እሱባለው፤ የወይብላ ማርያምን ታቦት ካደረበት ወደ መንበሩ ሲመልሱ መንገድ ላይ በወጣቶችና በፀጥታ አካላት አታልፉም ተብለው መከልከላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሺ ደበሌ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ አታልፉም ብለው የከለከሉት የመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች፤ ካህናትና መዘምራን እንዲያልፉ ፈቅደው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉባቸውን አልባሳት የለበሱትን ግን እንደማያሳልፉ ተናገሩ ብላለች፤ ንግስት የተባለች ምዕመን ለቢቢሲ፡፡  
“አብዛኛው ምዕመን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ያለበት ቀሚሶችን፣ ቲሸርቶችን ለብሷል። እነሱ ደግሞ መርጠን እናስገባለን አሉ። አስተባባሪዎቹ አልተስማሙም። ከዚህ ንግግር በኋላ አስለቃሽ ጭስ መተኮስ ተጀመረ። የወደቁና የተረጋገጡ አሉ”ስትል ሁኔታውን አስረድታለች።
“ከሰንደቅ አላማ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተመሳሳይ ችግሮች ሲከሰቱ ነበር፤ እኔ እንኳ በማውቀው ይሄ ለሦስተኛ ጊዜ ነው። በጉዳዩ ላይ ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ሲሞከር ‘ከላይ ነው የታዘዝነው’ የሚል ምላሽ ብቻ ነው የሚሰጡት”ብለዋል፤መምህር እሱ ባለው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን፤ በተከሰተው ችግር ምክንያት በዓሉ በመስተጓጎሉ  እንዲሁም በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጾ፤ ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለአካል ጉዳት ምክንያት የሆነውን ክሥተት በማጣራት ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለሕግ እንደሚቀርቡም በመግለጫው አመልክቷል።
ሐሙስ በተፈጠረው ግርግር  ቀራንዮ መድኃኔዓለም ያደረችውን ወይብላ ማርያም ታቦትን ለማስገባት አርብ ጠዋት በርካታ ምዕመናን በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ታቦቱን ሸኝተው በሰላም ሥነሥርዓቱ መጠናቀቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡



Read 701 times
Administrator

Latest from Administrator