Sunday, 09 January 2022 00:00

ጎንደር ለጥምቀት 1.5 ሚሊዮን እንግዶችን ትጠብቃለች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ጎንደር ከ10 ቀን በኋላ ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ከ1.5 ሚሊዮን በላይ እንግዶችን እንደምትጠብቅ ተገለፀ፡፡ በዓሉን  በተሳካ ሁኔታ ለማክበር የፀጥታና የደህንነት ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠውም ታውቋል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ቻላቸው ዳኘው ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ጥምቀትን በድምቀት ለማክበር ከወትሮው በተለየ ሁለንተናዊ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ የሆቴል አገልግሎትን በተመለከተም እያንዳንዱ ሆቴል ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት አቶ ቻላቸው፣የመኝታ እጥረት እንዳያጋጥም ደረጃቸውን የጠበቁ ድንኳኖች እንዲያዘጋጁ መመሪያ የተላለፈ ሲሆን አሁን ላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስለሌሉ የጎንደር ዩኒቨርስቲ በሁሉም ካምፓስ ያሉ መኝታዎች ለእንግዳ ዝግጁ  መደረጋቸውን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ዲያስፖራው ማህበረሰብ ወደ ጎንደር ከተማ እየገባና እየተስተናገደ መሆኑን የገለፁት ሀላፊው፤ የፀጥታ ችግር እንዳያጋጥም በእያንዳንዱ ቀበሌ ውስጥ ለህልውና ዘመቻው የነበረው አይነት አደረጃጀት ተዘርግቶ  በተናበበ ሁኔታ እየተሰራም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለፀጥታው ጉዳይ የተቋቋመው ራሱን የቻለ ኮሚቴ፣ ለእያንዳንዱ አደረጃጀት መመሪያ በማውረድ፣ ከወዲሁ የፀጥታውን ጉዳይ አስተማማኝ ማድረግ እንደተቻለም ነው አቶ ቻላቸው የጠቆሙት፡፡
“ጎንደር ከተማ ከዚህ በፊት በወያኔ ስርዓት ሚደርስባት ጫና ብዙ አስከፊ ጊዜያትን በፅናት ተወጥታ የጥምቀትን በዓል ሳታስተጓጉል አክብራለች” ያሉት ሀላፊው፤ አሁንም ያንን ተሞክሯችንን በመጠቀም ከ3 ሺህ በላይ ወጣቶችን በመመልመል የደህንነቱን ጉዳይ  በንቃት  ለመከታታል ተሰልፈዋል ብለዋል፡፡ የራሳቸው መለያ ልብስና ባጅ የተዘጋጀላቸው እነዚሁ ወጣቶች ከፀጥታ  መዋቅሩ ጋር በመናበብ ከዚህ ቀደም ይሰሩ እንደነበረው አሁንም በዓሉ ያለ አንዳች  ኮሽታ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ዝጅግት ተደርጓል ብለዋል ሃላፊው፡፡
የጥምቀት በዓል መድረሱ በፊት ያለው የባህል ሳምንትም እንደተጠበቀ ነው ያሉት አቶ ቻላቸው፣ ከጥር 1 ቀን ጀምሮ በርካታ የጎዳና ላይ ፌስቲቫሎች ስፖርታዊ ውድድሮች፣በምሑራንና በባለስልጣናት፣ በባለሃለቶችና በዲያስፖራዎች መካከል የሚካሄድ ውድድር፣የግጥም በመሰንቆ የአደባባይ ምሽት፣ጥር 6 ቀን የሚከበረው የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 203ኛ ዓመት የልደት በዓል፣ በጎንደርና በአካባቢው የሚገኙ የአለባበስ፣ የአጋጌጥ፣ የአመጋገብ፣ የጋብቻና መሰል ባህሎች ትርኢት፣የጎንደርና አካባቢውን የጀግንነት ታሪክ የሚያሳይ ሁነት፣ጥር ዘጠኝ በፋሲል ቤተ መንግስት ውስጥ የሚከናወን የንጉስ እራትና “ለፋሲል እሮጣለሁ” የሩጫ ውድድሮችን ጨምሮ በዓሉን የሚያደምቁ በርከታ መርሃ ግብሮች እንደሚከናወኑም ተናግረዋል፡፡ ጎንድር ከተማ ያላትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች ጥቅም ላይ አውሎ ከተማዋንና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ጋር ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም ዲያስፖራውና የሚመለከታቸው አካላት በሚገኙበት ትልቅ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም እንደሚካሄድም አቶ ቻላቸው ገልፀዋል፡፡
ሀላፊው በዚህ ደማቅና እጅግ አጓጊ በሆነው የጎንደር ጥምቀት በዓል ላይ ሁሉም ተገኝቶ በጥሩ ሁኔታ እንዲያሳልፍ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን በመግለፅ ሁሉም መጥቶ በዓሉን በጋራ  እንዲያከብር ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

Read 7161 times