Saturday, 08 January 2022 00:00

“ከሞትና ከህይወት የቱን ትመርጣለህ? ቢሉት፤ ሲያስብ ዘገየ”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን ሶስት ሰዎች አንድ ጫካ  በማቋረጥ ላይ ነበሩ። በመንገድ ላይ ሳሉ አንዲት የወፍ ጫጩት ከዛፍ ላይ ከሰራችው ጎጆዋ ወድቃ ኖሮ፣ እመሬት ላይ ያገኙዋታል።
አንደኛው መንገደኛ፤
“ይቺን የወፍ ጫጩት ቤቴ ወስጄ እንደ ዶሮ ጫጩት አሳድጋታለሁ” አለ።
ሁለተኛው መንገደኛ፤
“ይቺ ጫጩት ለጥናትና ምርምር ትጠቅማለች። ወደ ላቦራቶር ወስደን ለባለሙያ እናስረክባት” አለ።
ሦስተኛው መንገደኛ ደግሞ፤
“የለም የለም፤ ጎበዝ! ወደ ገበያ ወስደን እንሽጣት” አለ።
በዚህ ሲከራከሩና ሲሟገቱ ብዙ ጊዜ ከቆዩ በኋላ፣ በዚያው በአካባቢያቸው የሚኖር አንድ ፈላስፋ ነበርና፤ “አሁን እዚህ ከምንጨቃጨቅ” “ለምን ወደዚያ ፈላስፋ ሄደን ምክር አንጠይቀውም?” ብለው በአንድ ድምጽ በሀሳቡ ተስማሙ።
ወፊቱን ይዘውም ወደ ፈላስፋው ቤት ሄዱ።
ፈላስፋውም፤
“ወዳጆቼ ምን እግር ጣላችሁና መጣችሁ? ምን ልርዳችሁ?” አለና ጠየቃቸው።
መንገደኞቹም፡-
“ከዛፍ ጎጆዋ የወደቀች የወፍ ጫጩት አግኝተን ምን እናድርጋት? በሚለው ሀሳብ ላይ ብዙ ተከራከርን።
በመጨረሻም ወደ አንተ መጥተን ምክር በመጠየቅ ላይ ተስማማን። አንዱ፤ ወደ ቤቴ ወስጄ ላሳድጋት አለ። አንዳችን ለቤተ- ምርምር እንሰጣት አልን። አንዳችን ደግሞ ገበያ ተወስዳ ትሸጥ አልን። ማንኛችን ትክክል ያሰብን ይመስልሃል?
ፈላስፋው እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡-
“ወዳጆቼ ሆይ! በመጀመሪያ  በውይይት አምናችሁ ሀሳባችሁን በመለዋወጣችሁ፣ ጥሩ ባህል ጀምራችኋልና ሳላደንቃችሁ አላልፍም። ሁለተኛ መፍትሔ ለመሻት እኔን ለማማከር በመወሰናችሁ አመሰግናችኋለሁ። ወዳጆቼ! ለዶሮ ጫጩት የሚሆነው ኑሮ ለወፍ ጫጩትም ይሆናል ብሎ ያሰበው ተሳስቷል። ሁሉም የየራሱ ኑሮ አለውና። አሳድጎስ ምን ሊያደርጋት ነው? ዓላማ ቢስ ያደርገዋል። ቤተ-ምርምር እንውሰዳት ያለውም ተሳክቷል። ለወደፊቱ የሚጠቅማት ነገር የለምን ወደገበያ ወስደን እንሸሽጣት ያለውም፣ ከዚች ጫጩት ሽያጭ ማንኛችሁ ምን ያህል ትጠቀሙና ነው? የሱም ሀሳብ አይበጅም። የማያዋጣ ጥቅም ከመፈለግ አለማድረጉ የሚሻል ነገር ነው።
“እንግዲውያስ ምን አድርጉ ትለናለህ?” አሉና ሁሉም ጠየቁት።
ፈላስፋውም ረጋ ብሎ፤
“ከሁሉም የሚሻለው ወፊቱን ወደ ጎጆዋ መመለስ ነው።
ኑሮዋን መልሱላት። ሰላሟን ስጧት። የተፈናቀለን ሰው እንደምታቋቁሙ ሁሉ፣ ለወፊቱም እንደዚያ አስቡላት።” ብሎ አሰናበታቸው።
*   *   *
 ያለ ዓላማ ጉዞ ከንቱ ነው። ያለ ቅርስና ያለ በቂ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ነጻ ገበያን መመኘት የጫጩት አትራፊነት ምኞት ብጤ ነው። ያለ ብስለት ጥናትና ምርምር፣ ያለ ብቁና አስተዋይ ባለሙያ ዕድገት ዘበት ነው። ሰው የትላንቱ ኑሮው ካልተመለሰለት፣ ደሀ ለጎጆው ካልበቃ፣ ልማቱ  ከደረቀ፣ ጓዳው ካልሞቀ ተስፋው  ይሞትበታል። ኑሮው በየትኛውም መልኩ መለወጥ አለበት። ወጪና ገቢው ቢያንስ በመካከለኛ ደረጃ መመጣጠን መቻል አለበት። እየዋለ ሲያድርም ገቢው እየገዘፈ መምጣት ይጠበቅበታል።
ዛሬ እንደ ፋሽን የተያዘው ህገ- ወጥ ብልጽግና ነው። ሀገራዊ ስሜት እየቀጨጨ ነው። ድህነትን መቀነስ እንደ አፍ-ዓመል ይነገራል እንጂ ገና ሥር- ነቀል ፈውስ አላገኘም። በበሰለ መልካም ህዝብ ውስጥ አልሰረጸም።
ግማሽ- ጎፈሬ ግማሽ- ልጩ የሆነ ካፒታሊዝም ከፋይዳው ማነስ ግራ- ማጋባቱ ይከፋል። የምሁሮቻችን በዚህ ረገድ ከልብ ዝግጁ አለመሆን፣ ከሥራ-አጥነት መዘዝ ጋር ተዳምሮ፣ ከአዙሪቱ እንዳንወጣ አግቶናል። እጅግ ጥምዝምዝና ተደጋጋሚ አጣብቂኝ ወጥሮ ይዞናል። ሀብት እኩል ባልተከፋፈለበት አገር፣ ምርጫ መቶ በመቶ ተሳክቷል ማለት የይስሙላ ይሆናል። ከዚህ ይሰውረን ማለት ደግ ነው።
የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከሁሉ አስቀድሞ መድልዎን ይጻረራል። በአያሌው ቀናነት ይፈልጋል። የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደት የፓርቲዎችን በእኩል ደረጃ የመንቀሳቀስን መብት ግድ ይጠይቃል። የተሸናፊ ፓርቲዎችን መብት በብርቱ ያረጋግጣል። እርስ በርስ የመወዳደር ባህላቸው መቼም የማይገሰስ ልማድ በማዳበር፣ የሰለጠነ አካሄድ መሆን ይገባዋል። ሁሉም ያለ ጭቦ መወከላቸውን ማረጋገጥ አግባብ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ምርጫ ባለቀ ማግስት ጀምሮ ለሚቀጥለው ምርጫ መዘጋጀት እጅግ ብልህነት ነው! እንደ ዱሮው አገር ጎብኚዎች እንደሚያሾፉብን ዛሬም  “I Came From” እሺ ነገ Country”  መባል የለብንም። ነገ እሠራዋለሁ የምንልበት ጊዜ አይደለም። ከእሺ ነገ አገር ነው የመጣሁት” ብሏል አንድ አሜሪካዊ።
 ኑሮ ዛሬ ነው። ትግል ዛሬ ነው። በእጃችን ባለው ሰዓት ካተጠቀምንበት ወደ ትላንት ልንሳብ እንችላለንና የከመርነው ይናድብናል። ህይወት ዝንጋኤ ላይ እንድንጋደም አትፈቅድልንም። ቸልተኝነት ለሀገር ፀር ነው።
    “ካልተሳፈሩበት ፣ ቶሎ ተሽቀዳድሞ
    ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ!”
የሚባለው ለዚህ ነው። “ከሞትና ከህይወት የቱን ትመርጣለህ? ቢሉት፣ ሲያስብ ዘገየ” የሚለው ተረት የሚነግረንም ይሄንኑ ነው!
የገና በዓል እንደገና እንድናስብ፣ እንደገና እንድንወለድ መንገዱን ጥርጊያ ያድርግልን። መልካም በዓል!!

Read 8866 times