Sunday, 02 January 2022 20:44

ሮኬት ሰሪው፣ ቢሊዮን ዶላር ይከምራል

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

ፖለቲከኞች ደግሞ፣ ትሪሊዮን ዶላሩን “ብትን ብትን!”
                        
              በሮኬት ፍጥነት - ቢሊዮን ዶላሮችን በክምር በክምር። የአለማችን አዲሱ ቁጥር 1 ቱጃር።
ኢሎን ሞስክ ሃብት - በቢሊዮን ዶላር።
Mar 2017    $ 14
Oct 2017    $ 21
Mar 2018    $ 20
Oct 2018    $ 20
Mar 2019    $ 22
Oct 2019    $ 20
Apr 2020    $ 25
Sep 2020    $ 68
Apr 2021    $ 151
Oct 2021    $ 190
Dec 2021    $ 275
ትሪሊዮን ዶላሮችን - ብትን ብትን - እንደጠላት ገንዘብ። የአሜሪካ መንግስት ብደር።
እዳ በትሪሊዮን ዶላር።
2010    13.6
2011    14.8
2012    16.1
2013    16.7
2014    17.8
2015    18.1
2016    19.6
2017    20.2
2018    21.5
2019    22.7
2020    26.9
2021    29.5
ጨዋታው፣ ወደ ቢሊዮን፣ ወደ ትሪሊዮን ዶላር ቢሸጋገርም፤ ነገሩ ከብዷል ማለት አይደለም።
የዓለማችን ቁጥር 1 ቱጃር፣ ኢሎን ሞስክ የሚሉት ሰውዬ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ቢሊዮን ዶላር አልነበረውም። በስደት ከደቡብ አፍሪካ ሲወጣማ፣ በባዶ ኪስ ነበር ማለት ይቻላል። ከሁለት ዓመት በፊትም፣ በ20 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ነበር የሚያንዣብበው።
ከመቼው የ100 ቢሊዮን ዶላር አጥር አልፎ፣ በምን ፍጥነት የ200 መቶ ቢሊዮን ዶላር ጌታ እንደሆነ፣ በጥቂት ወራት ልዩነትም፣ ሩብ ትሪሊዮንን በመበጠስ ረከርድ ሰብሯል። አዲሱንም ዓመት፣ በ275 ቢሊዮን ዶላር ለመቀበል መብቃቱን አስቡት። ግን፣ ቆም ብሎ ለማሰብ መች ጊዜ ይሰጣል? በሮኬት ፍጥነት ነው የሰውዬው ሃብት የሚበረክተው።
ለነገሩ፣ ሌሎች ያልደፈሩትና ያልደፈሩትን ነገር፣ ኢሎን ሞስክ ሰርቷል። በስኬትም ልቆ ሄዷል። አዳዲስ የሮኬት ቴክሎጂዎችንና ቢዝነሶችን የፈጠረ ተዓምረኛ ሰው ነው። ሰሞኑን ለታክስ ክፍያ ጥቂት አክሲዮኖችን ሸጧል። 20 ቢሊዮን ዶላር ነው ታክሱ። የቢሊዮን ዶላር ጥሪ፣ እንዲህ ቀላል ሆኗል? የሮኬት፣ የሳተላይትና የጠፈር ጉዞ ኩባንያውን ለማቋቋም፣ ከዚያም ለማሳደግ፣ ባለፉት 15 ዓመታት፣ ሃብቱን አሟጥጦ ከማፍሰስ አልተቆጠበም። ቢሆንም ግን፣ ገንዘቡን አይበትንም። ቁጥብ ነው። ቁጥብነቱንም ለመግለፅ፣ በኪራይ ቤት ነው የምኖረው ይላል። በእርግጥ በገዛ ገንዘቡ፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ሚሊዮን ዶላሮች ቢያወጣ፣ ምን ጥፋት አለው።
ከራሳቸው ኪስ የማያወጡ፣ በሌላ ሰው ኪስ በሚወጣ ገንዘብ የሚደራደሩ ፖለቲከኞች ሞልተው የለ!
ትሪሊዮን ዶላሩን፣ ብትን ብትን!
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ እና የሴናተር ጆ ማንቺን ፍልሚያ፣ የእጅ በእጅ ትግል አይደለም። የ2 ትሪሊዮን ዶላር ፍልሚያ ነው። አዎ፤ ለማሰብ ይከብዳል። የኢትዮጵያ የ500 ዓመት የኤስፖርት ሽያጭ እንደ ማለት ነው። ቢሰጡን፤ ምን እንደምናደርግበት ጠፍቶን፣ ግራ ተጋብተን በጭንቀት ማለቃችን ይቀራል? በሽሚያ መጠፋፋትም አለ።
ደግነቱ፣ ነገሩ በኢትዮጵያ ላይ የተነጣጠረ የገንዘብ ዶፍ አይደለም።
በየዓመቱ እየተለጠጠ የመጣው የአሜሪካ መንግስት በጀት፣ ሌላ ተጨማሪ በጀት እንዲደረብለት የታሰበ ነው - ነገሩ። ማለትም 2 ትሪሊዮን ዶላሩ። ነባሩ በጀት ያነሰ አይመስልም? በጀከቱ ከመብዛት የተነሳ፣ በጀቱን (ወጪውን) መሸፈን እያቃተው፣ በየዓመቱ ትሪሊዮን ዶላር እየተበደረ ነው።
ዘንድሮማ 3 ትሪሊዮን ይሆናል ብድሩ። እዳው እየተከማቸ ወደ 30 ትሪሊዮን ተጠግቷል። ቢሆንም፣ ትንሽ ቆጠብ የማለትና አደብ የመግዛት ምልክት አይታይም።
ተጨማሪ በጀት ለኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ… ለድጋፍና ለድጎማ ትሪሊዮን ዶላር፣… እንደገና ተደራቢ ትሪሊዮን ዶላር፣… እንደቀላል ነገር። ለመሰረተ ልማት፣ ለድልድይና ለመንገድ እድሳት፣ ለኢንተርኔት ድጎማ፣… ትሪሊዮን ዶላር ተጨማሪ በጀት። ይህ ከወር በፊት ጸድቋል።
መች ይህ ብቻ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን፣ ሌላ የ2 ትሪሊዮን አዋጅ አለ። ለህጻናት እንክብካቤ፣ ለሴቶች ድጎማ፣ ለተጎሳቆሉ መንደሮች የስፖርት ማዘውተሪያ፣… ዝርዝሩ ብዙ ነው።
አዋጁ፣ የ2100 ገፅ አዋጅ ነው። ሙሉውን ያነበበ ሰው ማግኘት ያስቸግራል። ያነበበ ቢኖር እንኳ፣ በየእለቱ፣ በየሳምንቱ፣ አንቀጾችና አባሪ ገጾች ይጨመሩበታል፤ ይከለሳል። በድርድር ደርዘን ገጾች ወጥተው፣ በሌላ ይለወጣሉ።
የገጹ እና ገንዘቡ ብዛት፣ የጉዳዩን ክብደት ማሳየት ነበረባቸው።
ግን፣ አዋኪ. እንደ ትልቅ ጉዳይ በረዥም ዲስኩሮች አልታጀበም፤ በትችት ትንታኔዎች አልተጥለቀለቀም።
ጆ ባይደን፣ አዋጁን “Build Back Better” በሚል ስም ነው ያዋለዱት። ተቀናቃኞች ደግሞ “BBB” ብለው ይጠሩታል - አሳጥረው አሳንሰው።
ቢሆንም ግን፣ የባይደን ዲስኩርም አጭር ነው። “መልሶ ግንባታው እውን ይሆናል” ከሚል መፈክር ያለፈ ነገር አይናገሩም - በአብዛኛው። የሚቀርብባቸው ትችትም፣ የዚያኑ ያህል ነው - በአጭር በአጭሩ።
ብዙም ሳይቆይ ደግሞ፤ ሌላ ማሳጠሪያ ዘዴ ተገኘለት።
የ2 ትሪሊዮኑ ጉዳይ፣ የጆ ባይደንና የጆ ማንቺን ጉዳይ ሆነ። የሁለት ጆ ፍልሚያ። እንዴት? በነገራችን ላይ፣ ሁለቱም የዲሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች ናቸው። ታዲያ ምን አፋለማቸው?
አንዱ ጆ ወዲህ፣ ሌላው ጆ ወዲያ!
ኮንግረስ ውስጥ፣ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተመራጮች ቁጥር ስለሚበልጥ፣ አዋጁ ተከልሶም ተቦክቶም መጽደቁ አልቀረም። ነገር ግን፣ 100 አባት ባሉት ሴኔት ውስጥም ማልፍና መጽደቅ አለበት። እዚህ ላይ ነው፤ አስገራሚው ግጥምጥሞሽ የተከሰተው።
50ዎቹ ሴናተሮች የዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ 50ዎቹ ደግም የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ናቸው። በዚህ ምክንያት፣ የድጋፍና የተቃውሞ ድምጽ እኩል በእኩል ከሆነ፣ የሴኔቱ ሰብሳቢ፣ የመለያ ድምጽ ይሰጣሉ። የሴኔት ሰብሳቢ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንቷ ናቸው። የጆባይደን ምክትል፣ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተመራጯ ካማላ ሃሪስ።
ድጋፍና ተቃውሞ፣ እኩል በእኩል ቢሆን፣ በሰብሳቢዋ አንድ ተጨማሪ የድጋፍ ድምጽ፣ አዋጁ ሊጸድቅ ይችላል ማለት ነው።
ድጋፍና ተቃውሞውን እንቃኛ።
ሁሉም ሪፐብሊካን ሴናተሮች፣ አዋጁን ይቃወማሉ። 50 ተቃውሞ ማለት ነው።
የዲሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮችስ? 50ዎቹ ቢደግፉ፣… የጆ ባይደን መፈክር ሰመረ ማለት ነው።
ነገር ግን፣ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ፣ በፓርቲ ጎራ መተማመንና ድጋፍ ማግኘት ቀላል አይደለም። በተለይ ሴናተሮች፣ ያስቸግራሉ። ድጋፋቸውን ለመስጠት፣ አብዛኞቹ ሴናተሮች የራሳቸውን ቅድመ ሁኔታ ያቀርባሉ። በየፊናቸው፣ ማሻሻያ ወይም ተጨማሪ አንቀጽ ያመጣሉ፤ አዋጁ ውስጥ ይካተትልኝ ይላሉ። በጀት በዛ፣ በጀት አነሰ፣፣ አዋጁ ተለጠጠ፣ አዋጁ ከረረ፣ በጣም ለዘበ… እያሉ ቅሬታ ይደረድራሉ። እናም የሴናተሮችን ድጋፍ ለማግኘት፣ በተለይ የዋና ዋናዎቹን ሴናተሮች ሃሳብና ቅሬታ፣ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንኳ፣ በከፊል ማስተናገድ የግድ ነው። እንደ ድርድር ቁጠሩት።
የሆኖ ሆኖ፣ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በድርድርና በተፅዕኖ መንገዶች የፓርቲያቸውን ሴናተሮች አግባተዋል። 49 የዲሞክራቲክ ሴናተሮች፣ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። ግን በቂ አይደለም። የአንድ ሴናተር ድጋፍ ይጎድላል። እኚሁ ሴናተር፣ ጆ ማንቺ ይባላሉ። የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባ ናቸው።
ጆ ማንቺን ከደገፉ፣ አዋጅ ይጸድቃል። ካልደገፉ፣ አዋጁ ይወድቃል።
በሌላ አነጋገር፣ የ2 ትሪሊየን ዶላር ከባድ ጉዳይ፣ ዞሮ ዞሮ፣ እንደ ቀላል ነገር፣ የጆ ባደንና የጆ ማንቺን ቀላል ጉዳይ መስሏል።
አንዱ ጆ፣ “የመልሶ ግንባታ አዋጅ እውን ሆናል” ብለው ይናገራሉ።
ሌላኛው ጆ፣ “አሁን ባለው ይዘት አዋጁን አልደግፍም” ይላሉ።
ለምን አይደግፉም? አዋጁ የተለጠጠ ነው። በጀቱ ብዙ ነው። በጥቂት ዓመታት የሚጠናቀቅ ወጪ ሳይሆን፣ በየዓመቱ ገንዘብ የሚመደብለት ቋሚ ወጪ ነው። የብድር እዳን፣ የታክስ ጫናንና የዋጋ ንረትን ያባብሳል ይላሉ - ጆ ማንቺን። ከዚህ ያለፈ ማብራሪያ ብዙም አይተነትኑም።
በቃ፤ “አሁን ባለው ቅርጽ፣ አዋጁን አልደግፍም” የሚል ነው የዘወትር ምላሻቸው።
ሴናተር ጆ ማንቺን በዚህ መፈክራቸው ከቀጠሉ፣ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መፈክር ቀልጦ ይቀራል።
በቃ፣ ይሄው ነው፤ የ2 ትሪሊዮን ጉዳይ? ትሪሊዮን እንዲህ ከቀለለ፣ ከ2 የቲውተር መልዕክት ያነሰ ከሆነ፣ የቢሊዮን ዶላር ጉዳይ፣ ቀላል ጨዋታ መሆኑ ይቀራል?
ባለፉት 2 ዓመታት፣ “የኮቪድ ጫናዎችን ለመቋቋም” በሚል ምክንያት፣ የ3.4 ትሪሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦ አልነበር? በከፊል ድጎማ፣ በከፊል ብድር ነው።
ከዚሁ ውስጥ ብዙ ገንዘብ እንደተዘረፈ የዘገበው ዘታይምስ፣ ከ900 በላይ የወንጀል ምርመራዎች እየተካሄዱ ናቸው ብሏል።
እስካሁን በተደረገው ምርመራ ግን፣ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደተዘረፈ፣ እንደተሰረቀና እንደተጭበረበረ ተረጋግጧል ብለዋል - የምርመራው አስተባባሪ ባለስልጣን።
ብትን ብትን ማለት ይሄም አይደል። ቢሆንም ግን፣ ገንዘብ ይባክናል ብለው የአለማችን መንግስታት፣ ከብድር አይታቀቡም።
የአሜሪካ መንግስትም፣ እንደሌሎቹ ሆኗል። ያለ ብድር፣ ከአመት አመት መሻገር አይችልም። ባለፉት 20 ዓመታት፣ አንድም ጊዜ ከብድር “አልቦዘነም”። ለነገሩ ከጥቂት አገራት በስተቀር፣ በብድር ሱስ ያልተያዘ መንግስት የለም ማለት ይቻላል።
ከሌሎች ይሻል የነበረው የአሜሪካ መንግስትም፣ ከአመት አመት የብድር ጥድፊያውን አፍጥኖታል። ብትን ብትን በትሪሊዮን ዶላር… ሆኗል ነገሩ።
አዎ። የተለያዩ የብድር ምክንያቶች ይኖራሉ። በየአገሩ የተለያዩ ሰበቦች የመኖራቸው ያህል፣ በአሜሪካም የብድር ሰበብ ሞልቷል። ዋናው ምክንያት ግን፣ በሁሉም አገራትና ዘመናት፣ ተመሳሳይ ነው።
መንግስታት፣ ማለትም ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች፣ “እንዲህ እንሰራላችኋለን፣ እንዲህ እንሰጣችኋለን”፣ እያሉ ቃል ይገባሉ። ታዲያ፣ ከኪሳቸው በሚያወጡት ገንዘብ አይደለም፤ የድጎማና የፕሮጀክት መዓት የሚፈለፍሉት። በቃ፣ ቀላል ነው። የራሳችሁን ገንዘብ የማታወጡበት ከሆነ፣ ምን ችግር አለ? እንዲያውም፣ የህዝብ ድጋፍ ሊያስገኝ ይችላል፤ ለመመረጥም ያገለግላል።
ግን ችግር አለ። ከድጎማና ከፕሮጀክት ብዛት ጋር፣ የመንግስት ወጪ ይለጠጣል (በጀቱ ያብጣል)። እንደተለመደው፣ ልጓም ያጣውን የመንግስት ጪው ለመሸፈን፣ በህዝብ ላይ፣ የታክስ አይነት እየጨመሩ ኑሮውን ያከብዱታል።
ሁለተኛ፣ ገንዘብ እያተሙ፣ የዋጋ ንረት ያመጡበታል።
ይህ አልበቃ ሲልም፤ የብድር እዳ ያከማቹበታል። በ2011 የአሜሪካ ገበያ ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረው የዶላር ኖት፣ አንድ ትሪሊዮን ገደማ ነበር።
አሁን በ2021 የመጨረሻ ወር ላይ፣ ከ2.2 ትሪሊዮን ዶላር በልጧል። የአውሮፓ የዩሮ ሕትመትም በተመሳሳይ ጊዜ በእጥፍ ጨምሯል። ከዚህም ጋር ቀስ በቀስ፣ የዋጋ ንረት እያሻቀበ ነው። በዓመት ከሁለት በመቶ የባሰ የዋጋ ንረት በማይፈጠርባቸው የአሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት፣ ዛሬ ወደ 4% ወደ 5% ፕርሰንት እየጋሸበ ሄዷል።
አዎ፣ በአገራችን እንደሚታየ የ10% ወይም የ20% አይደለም - የዋጋ ንረቱ። ምንጩ ግን ተመሳሳይ ነው። በኢትዮጵያ፣ ከ10 ዓመት በፊት በገበያ ውስጥ የነበረው የብር ኖት 40 ቢሊየን ብር ገደማ ነበር። ዛሬ ግን ከ160 ቢሊየን ብር በላይ ሄዷል። 4 እጥፍ መሆኑ ነው። የዋጋ ንረቱም እንደዚያው ከብዷል።
እንዲያም ሆኖ፣ መንግስታት፣ ወጪያቸውን ካልገሩ (በጀታቸውን አደብ ካላስያዙ) በቀር፣ በታክስና በገንዘብ ህትመት ብቻ ሊያሟሉት አይችሉም። እናም ይበደራሉ።
በእርግጥ፣ አንዳንዴ እየተንከባለለ የመጡ ችግሮችን በአጭር ጊዜ መፍታት ይከብዳል። በዚያ ላይ፣ ለብድር የሚዳርጉ፣ ፈታኝ ችግሮች አያጋጥሙም ማለት አይደለም።
በጆርጅ ቡሽ ዘመን፣ ከሽብር ጥቃት ጋራ ተያይዞ የመጣው የአፍጋኒስታንና የኢራቅ ጦርነት፣ ሀብትን የሚበላ ከባድ ፈተና መሆኑ አያከራክርም። ቶሎ አለመጠናቀቁና በጊዜ አለመቋጨቱ፣ ደግሞ የህይወትና ከአካል ጥፋት በተጨማሪ፣ የሀብት ኪሳራን አስከትሏል። ጦርነት፣ የግድ ካልሆነና ሌላ አማራጭ ካልጠፋ በቀር፣ እንደቀላል ጉዳይ የሚገቡበት አይደለም።
ከተቻለ በሩቅና በጅምር ማስቀረት ይመረጣል። የግድ ሆኖ ከገቡበት ደግሞ፣ በጊዜ ይገቱታል፤ መቋጫ ይበጅለታል። አለበለዚያ ጉዳቱ፣ ክፉ ነው። እንኳን ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ ድሃ አገራት ይቅርና፣ ለእነ አሜሪካም፣ ከባድ ሸክም ነው።
በጆርጅ ቡሽ ዘመን፣ በ8 አመታት ውስጥ፣ የአሜሪካ ማዕከላዊ መንግስታት፣ ከ2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ብድር ተከማችቶበታል። አለማቀፍ የኢኮኖሚ ቀውስ የተፈጠረ ማግስት፣ በባራክ ኦባማ ዘመን ደግሞ፤ ከ8 ትሪሊዮን በላይ ተጨማሪ የብድር ዕዳ ተጨምሮበታል - በ8 ዓመታት ውስጥ።
በዶናርድ ትራፕ ዘመን ደግሞ- ከ5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ እዳ (በ4 ዓመታት)። ምን ይሄ ብቻ።የኮረና ቫይረስ ቀውስ ተጨምሮበት የብድር ጥድፍያው ተባብሷል።
ጆ ባይደን ከመጡ ወዲህ፣ በአመት ውስጥ 3 ትሪሊዮን ዶላር ብድር ተደርቦበታል።
የማዕከላው መንግስት ዕዳም 29.5 ትሪሊዮ ዶላር ደርሷል። በየዓመቱም፣ መንግስት፣ ለወለድ ብቻ፣ አራት መቶ ቢሊዮን ዶላር ይከፈላል።
የአገራችን የውጭ እዳስ? 29 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው። ለወለድ ደግሞ፣ በዓመት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይከፍላል።
በእርግጥ ባለፉት 3 ዓመታት፣ የውጭ ብድር ላይ ቆጠብ የማለት፣ ጠንካራ ጥረቶች መታየታቸው መልካም ነው። የእድ ክምችት ግስጋሴው ገታ ተደርጓል።
ከጥሩ የቁጥብነት ጥረት ጋር፣ ለኢንቨስትመንትና ለስራ እድል ፈጠራ የሚመቹ ማሻሻያ ሲጨመርበት፣ እንዲሁም ሰላም የመፍጠር መላና ጥረት ሲታከልበት፣ ችግሮችን በጊዜ የማቃለል እድል ይሰፋል።

Read 3110 times