Saturday, 22 September 2012 10:58

ይድረስ ለኢህአዴግ (ኧረ ንቃ ኢህአዴግ!)

Written by  አለምሰገድ አ.
Rate this item
(8 votes)

ኢህአዴግና ፌስቡክ

የኢህአዴግ ካድሬዎች በተለይ ሚዲያው አካባቢ የተሰማሩቱ እንደ ፌስቡክ “አቢዩዝ” ያደረጉት የቴክኖሎጂ ውጤት ያለ አይመስለኝም፡፡ ፌስቡክን አያውቁትም ግን ይፈሩታል፣ ይሸሹታል፣ ተጠቃሚዎቹንም “አብዮተኞች” በሚል ድፍርስ ስም ይጠራሉ፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ በፌስቡክ አማካኝነት ማግኘት የሚገባውን ጥቅም መቶ በመቶ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡  ኢህአዴግ የፌስቡክንና የኢትዮጵያን ዝምድና አያውቅም። በዚህም የተነሳ የፌስቡክ አብዮት ይነሳብኛል ብሎ ሰግቶ ነበር፡፡ (የምዕራብ አፍሪካ ህዝባዊ አብዮት የተቀሰቀሰ ሰሞን) በማህበራዊ  ድረ-ገጾች ላይ በጃሚንግ ዘመተ፡፡

በመጨረሻም “የፌስቡክ አብዮተኞች” ሲል አደገኛ ታፔላ ይለጥፏል፡፡ እስቲ በሞቴ ይታያችሁ… ይቺ ሀገር በፌስቡክ አብዮተኞች ኢህአዴግን ከስልጣን ስታባርር? ይሄ ብዥታ እና የእውቀት ማነስ ኢህአዴግን እንደፓርቲ፣ ኢትዮጵያንም እንደ ሃገር ከማህበራዊ ድረ-ገጾች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡ (ወይ ነዶ!) እናም ኢህአዴግን ልመክረው እፈልጋለሁ፡፡ ፌስቡክን እንዳይፈራ!

የፌስቡክ አብዮተኞች ከየት?

ይኸውልህ ውዱ መንግስታችን… በፍጹም አትስጋ! ኢትዮጵያውን በፌስቡክ አብዮት ያነሳሉ፣ ጐዳናውን በአመጽ ያሸብሩታል ብለህ በአስቂኝ የቀትር ብርድ እራስህን አትምታ፡፡ “አብዛኛው” የፌስቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊ ያንተ ቢጤ ነው። የፌስቡክን ጥቅም በቅጡ አልተረዳም፡፡ ምናልባትም የጅንጀና አብዮት፣ የሽሙጥ አብዮት፣ የወሲብ አብዮት፣ የስድብ አብዮት ወዘተ ከቀሰቀሰ እንጂ የፖለቲካውንስ ነገር ተወው! (ያውም የኢትዮጵያ?)

ኢህአዴግ… የምሬን ነው የምነግርህ፡፡ ከፈለግህ እገሌ እባላለሁ ብለህ “ቆንጅዬ” የአራዳ ስም ለራስህ ስጥና (ዴቭ፣ ናሂ፣ ኤቢ፣ ጃ፣ . . ምናምል ልትለው ትችላለህ) አካውንት ክፈት። ከዚያም የአንድ ሸበላ ጐረምሳ (ፀጉሩን ፈረዝረዝ ያደረገ) ፎቶ ፈላልግና “ኘሮፋይል ፒክቸር..”ህ አድርገው፡፡ ከዚያ ቢያንስ 1000 ለሚሆኑ የሃገርህ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች .. “ፍሬንድ ሪኩዌስት” ላክላቸው፡፡ ያው ያልተፃፈው የሃገራችን የፌስቡክ  ህግና ደንብ እንደሚያዘው፤ አንድ እንደ አንተ ያለ ሸበላ ኢትዮጵያዊ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ 90 በመቶ ጓደኞቹ ሴቶች መሆን አለባቸው፡፡ እናም “ፍሬንድ ሪኩዌስት” ከምትልክላቸው 1000 ሰዎች 900ዎቹ ሴቶች እንደሚሆኑ አትጠራጠር፡፡ መቶ ወንድ አይበቃህም? (ያውም ከተገኘ ነው) ከዚያ በኋላ በቃ ቻትህን ማጧጧፍ ነው። በተአምረኛው የፌስቡክ መስኮት በኩል ከ20 እና ከ30 የሃገርህ ልጃገረዶች ጋር በአማር-ላቲኖ (በላቲን በሚፃፍ አማርኛ) አሊያም በዝርክርክ እንግሊዝኛ ጨዋታህን ማድራት ነው፡፡ ስልክ ቁጥር መለዋወጥ፣ ኬክ ቤት መቀጣጠር ፣ በሃሜት መቦጫጨቅ፣ ተረብ መወራወር፡፡

ደሞም አትርሳ በሞቀው የቻት ወግህ ከልጃገረዶቹ ጐን ለጐን በሰፊው “ዎል”ህ ላይ ልጆች የሚያስቁ ፎቶዎችን በብዛት ፖስት አድርግ፡፡ ወዲያው መአት ኮሜንቶች ይጐርፉልሃል፡፡ ትደነቃለህ፣ ትሞገሳለህ፡፡ ፖስት ያደረካቸው ፎቶዎች እኮ ምን አይነት መሰሉህ… የአርሰናሉ አሰልጣኝ የሙሽሪትን ቬሎ ለብሰው፣ የማንቼው ደግሞ በሙሉ ሱፍ አጊጠው በሰርግ ሲጋቡ፣ ሮኒ ቫንበርሲን እንደህፃን አዝሎት፣ ቴዲ አፍሮ እጮኛውን ቀና ብሎ ሲያያት ወዘተ… አይነት ናቸው፡፡ ኢህአዴግ ሆይ… ይሄ ትውልድ የትኛውን መንበርህን ይሆን በአብዮት የሚያንቀጠቅጠው?

ግድየለህም ኢህአዴግ እመነኝ አብዛኛው የሃገርህ የፌስቡክ ተጠቃሚ ..አብዮተኛ.. የሚባል ከባድ ስም የሚሰጠው አይነት አይደለም፡፡ ዘርፈ ብዙውን የፌስቡክ ቴክኖሎጂ፣ ሁነኛ የመረጃ እና የእውቀት ማእድ የሆነውን ገበታ፣ ኢትዮጵያውያን ደንበኞቹ እንደ ጉድ እያሰቃዩት ነው፡፡ “አቢዩዝ” እያደረጉት ነው፡፡

ግን ልብ በል ኢህአዴግ!

እስከአሁን የሰነዘርኩት ወቀሳ አብዛኞቹን እንጂ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የፌስቡክ ደንበኞች አያጠቃልልም፡፡ በፍፁም! ጥቂቶች አሉ- ፌስቡክ የገባቸው፡፡ ድንቅ የመረጃ ምንጭ የሆናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ፌስቡክ እና ሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾች የእውቀት የመረጃ ገበያ ናቸው፡፡ ይሰጡባቸዋል። ይቀበሉባቸዋል፡፡ ቁምነገረኛ ወዳጅ ያፈሩባቸዋል፡፡ የባህል ማስተዋወቂያ፣ የፍልስፍና መሞገቻ፣ የፖለቲካ መከራከሪያ መድረካቸውም ነው፡፡

እነጊዜሽወርቅ ተሰማ እነማን ናቸው?

ጊዜሽወርቅ ተሰማ ይላል የፌስቡክ አካውንቷ ስም፡፡ ፕሮፋይል ፒክቸሯ ብስል ቀይ፣አፍንጫ ሰልካካ ፣ ደመ ግቡ ሴት መሆኗን ያሳያል፡፡ ሌሎቹ ፎቶዎቿም ተመሳሳይ እውነት አላቸው። “ጊዜ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር” የተሰኘ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሆኗን እና ከ2000 በላይ የፌስቡክ ጓደኞች እንዳሏት ከገጿ ላይ ሰፍሯል፡፡

ከአንድ አመት በፊት ይመስለኛል በሬዲዮ ፋና ቃለመጠይቅ ተደርጐላት ሰምቼ ነው “ፍሬንድ ሪክዌስት” የላኩላት፡፡ ወዲያው ተቀበለችኝ፡፡ ትዝ ይለኛል ሬዲዮ ጣቢያው በስኬታማ  የንግድ ሰውነቷ ነበር እንግዳ ያደረጋት፡፡ ሙዚቃ እየመረጠች ለአድማጮች ተሞክሮዋን አካፈለች፡፡ የምር ሁሉ ነገሯ ቀልብ ይይዝ ነበር፡፡ ጥያቄዎቹን የምትመልስበት መንገድ፣ የምታነሳቸው ሃሳቦች እና ድፍረቷ … የሚማርክ ነበር፡፡ በቃ ምን አለፋችሁ… አሪፍ ሴት ናት። እስከመጨረሻው እየጣፈጠችኝ አዳመጥኳት፡፡  ከሁሉም በላይ ግን ስለማህበራዊ ድረ-ገጾች እና ስለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያላትን አመለካከት የገለጸችበት መንገድ ስለማረከኝ ነበር የጓደኝነት ጥያቄ በፍጥነት የላኩላት፡፡

በቃለመጠይቋ ምን አለች መሰላችሁ? “በእረፍት ጊዜ ብቻ አይደለም፤ እንደስራም የተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾችን በንቃት እጠቀማለሁ፡፡ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ሊንክዲን፣ ፓልቶክ”  ወዘተ ሁሉንም በደንብ እጠቀማለሁ፡፡ የሃገሬን ባህል፣ ታሪክ እና ኪነጥበብ በተቻለኝ መጠን አስተዋውቅበታለሁ፡፡ የንግድ እንቅስቃሴዬን አቀላጥፍበታለሁ፣ ወዳጆች አፈራበታለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን እንቅስቃሴዎች በሙሉ በንቃት እየተከታተልኩ ለአለም አሳውቅበታለሁ፡፡ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ አዳዲስ እና ወቅታዊ መረጃዎችን አቀርብበታለሁ፡፡ በተለይም ንግግሮቻቸውን በትኩስነታቸው ከያለበት እየፈለፈልኩ ለፌስቡክ ጓደኞቼ አካፍላለሁ” (ልብ አድርጉ ሙሉ ቃሏን እንደወረደ አላቀረብኩም) “ለምን እንዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ አተኮርሽ?” ጋዜጠኛው ይጠይቃል፡፡ “በጣም ስለምወዳቸው፣ ስለማከብራቸውና ስለምኮራባቸው፡፡ ንግግራቸው በእውቀት የተሞላ ነው፡፡ በሳል መሪ ናቸው፡፡ ብልህ እና ለአገር አሳቢ ናቸው፡፡ እንደውም ባይገርምህ ከ5ሺህ በላይ ከእሳቸው ንግግሮች የተወሰዱ ማራኪ አገላለጾች አሉኝ፡፡”

ጊዜሽወርቅ ማብራሪያዋ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የማህበራዊ ድረገጾችን ፋይዳ ገና እንዳልተረዱ፣ መንግስትም ድርሻውን እንዳልተወጣ በግልጽ ተናገረች፡፡ በወጉ ከተጠቀምንባቸው እንደ አሪፍ የመረጃ እና የእውቀት ምንጭ ልንገለገልባቸው እንደምንችል በሙዚቃ እያዋዛች ነገረችን፡፡ (ተባረኪ!)

ሴትየዋ እውነቷን ነው!

የፌስቡክ ጓደኛዬ ከሆነች በኋላ ሁሉን ነገር አረጋገጥኩ፡፡ እውነትም ይቺ ሴት በፌስቡክ በገንዘብ የማይለካ ትርፍ እያገኘችም እያስገኘችም ነው፡፡ በገጿ ላይ ..ፖስት.. የምታደርጋቸው ጽሁፎች፣ ኦዲዮ እና ቪዲዮ ክሊፖች፣ ፎቶዎች፣ ስእሎች ወዘተ… ሃገርን የሚያስተዋውቁ ናቸው፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶዎችና ንግግሮች በብዛት ይገኙበታል፡፡ በተረፈ ስለሴቶች፣ ሰለህፃናት፣ ስለትምህርት፣ ስለጤና በጠቅላላው  ስለልማት የሚያትቱ መረጃዎች ከገጿ ላይ ሞልተዋል፡፡ ኪነጥበቡ ፣ ስፖርቱ፣ ፖለቲካው፣ ሚዲያው … ብቻ ኢትዮጵያዊ የሆነ ነገር ሁሉ የሴትየዋ የፌስቡክ ገጽ ላይ ሰፊ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ከእያንዳንዱ ፎቶ እና ቪዲዮ ስር በኢትዮጵያዊ ጨዋ ቃላት የተሞሉ መልእክቶችን ታሰፍራለች፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን እንቅስቃሴዎች ታደንቃለች፣ ትደግፋለች፡፡ የስኮላርሺፕ እድሎችን በብዛት ፖስት ታደርጋለች። ከታላላቅ መጽሃፍ የተወሰዱ እና ለለውጥ የሚያነሳሱ ጥቅሶችን በየሰከንዱ ታስነብበናለች፡፡ ታዲያ ቁጥራቸው እና አይነታቸው ይብዛ እንጂ መልእክቶቹ በሙሉ የሚሰጡት ትርጉም አንድ ነው። “እንዋደድ! በፍቅርና በአንድነት ተጣምረን ሃገራችንን እናሳድግ፤ በእውቀት እንደግፍ! በእውቀት እንቃወም! ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!” (አሜን)

 

እናም ኢህአዴግ ሆይ፤

ከዚች ሴት መማር ያለብህን ትልቅ ጉዳይ አስረግጬ ልንገርህ፡፡ እስቲ… ሴትየዋ ደከመኝ ሰለቸች ሳትል በፌስቡክ የምታስተላልፋቸውን መልእክቶችና አስተያየቶች በጥሞና ለመመልከት ሞክር፡፡ አንዳንድ ዳያስፖራዎች በዘለፋና በጥላቻ ሊያስመርሩህ ይችላሉ፡፡ ቢሆንም ግን ግዴለም አትበሳጭ! ዘለህ “የፌስቡክ አብዮተኞች..” እያልክ ታፔላ አትለጥፍ! እስቲ የሴትየዋን መልሶች የበለጠ ትኩረት ሰጥተህ ተመልከታቸው፡፡ ለማን ምን እንዳለች፣ ለስድቦቹ ምን እንደምትመልስ እየደጋገምክ አንብብ፡፡ ከዚያ  ይገለጥልሃል፡፡ እውቀት እና ቅንነት ምን ያህል  አሸናፊ እንደሆነ ትረዳለህ፡፡ ሴትየዋ እና መሰሎቿ ምን አይነት ትውልድ እየቀረጹ እንደሆኑ ተገንዝበህ ትደነቃለህ፡፡ በአንተ በመንግስት ደረጃ እንኳን ያልተሰራውን ስራ አንዲት ግለሰብ በሃገር ፍቅር ተነሳስታ (ፖለቲከኛ ትሆን እንዴ? ትሁና!) ስትሰራው አይገርምም! አንተ በሩቁ የምትሸሸውን “ዲያስፖራ” እና “የፌስቡክ አማጺ ቡድን” እሷ ፊት ለፊት ስትጋፈጠው ታያታለህ፡፡

እስቲ በሞቴ ስማኝ!

የዚህችን ሴት አይነት ተግባር የሚያከናውኑ 1000 የፌስቡክ ካድሬዎች ብታሰለጥን ምን ሊፈጠር እንደሚችል? (መቼም ከዚህ ሁሉ የልማት ሰራዊት 1000 በእንግሊዘኛ የሚግባባ አይጠፋም አይደል?) በነገርህ ላይ አንድ የምታስቅም የምታናድድም መረጃ ሹክ ልበልህ (ያ ጋዜጠኛ ወዳጄ ነው ያጫወተኝ) ምን መሰለህ… የማታ ተረኛ የሆኑ የኢቴቪ ሰራተኞች እንደቀኑ አይበዙም አይደል! “ግን ምን የሚሆንበት ሁኔታ አለ” መሰለህ? የማታው የሰራተኞች ሰርቪስ ጢም ብሎ ከመሙላቱ የተነሳ ቦታ ሁሉ ይጠፋል አሉ፡፡ ለምን መሰለህ? ያለስራ የሚያመሹ የቀን ሰራተኞች ስላሉ ነው (አሉ ነው) ምን ሲሰሩ በለኛ … ፌስቡክ ላይ ተጐልተው እልሃለኋ! ይሄ “ልማታዊ ጋዜጠኛህ” ሁሉ አንዲት የቢቢሲ ዜና “እንደነገሩ” ተርጉሞልህ፣ በቀጥታ ወደፌስ ቡክ ቺኮቹ ይወረውርልሃል፡፡

ከዚያ እስከ ማታ “ሰርቪስ ሲሄድ ጥሩኝ” እያለ መጀናጀን ነው፡፡ ግራ ከገባቸው ዲያስፖራዎች ጋር አንተኑ ሲያማህ ይውላል፡፡ ለኢሳት መረጃ ልኮ ከኢቴቪ ደሞዝ ይቀበላል፡፡ (መረጃ ነው ስብቀት?)

እሺ ይሁን ልማታዊዎቹን ጋዜጠኞችህን ተዋቸው፡፡ ቆይ ባለስልጣናቱስ ምንድን ነው የሚሰሩት?፡፡

እስቲ በስሙ የፌስቡክ አካውንት ከፍቶ ስለፓርቲው የፖለቲካ አቋም የሚሰብክ፣ የሚሟገት እና ለፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሥራ የሚሰራ ባለስልጣን ካለህ አስተዋውቀኝ፡፡ የለህም፡፡ ወይም አላገጠመኝም። ግን አትድከም አታገኝም፡፡

እነጊዜሽወርቅ ደሞ አሉልህ … በራሳቸው ወጪ ያንተን ስራ የሚሰሩልህ! ስራችን ነው ብለው ስላመኑ ግን ትጋታቸው ለጉድ ነው፡፡ ኧረ ንቃ ኢህአዴግ!

 

እናም ኢህአዴግ ሆይ እባክህን ምክሬን ተቀበለኝ!

ግብሩ ክፉኛ በተመሳቀለው፣ ፋይዳው ሲበዛ በተንሸዋረረው የኢትዮጵያችን የፌስቡክ ሜዳ ላይ ስድቡን፣ ዘለፋውን፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያውን ተቋቁመው ስለዚች ሀገር መልካምነት የሚተጉትን፣ የሚለፉትን እንደ ትምህርት ቤትህ እያቸው፡፡

ተማርባቸው! አይዞህ…ፌስ ቡክ አትፍራ! ድረገፆችን ጃም አታድርግ፡፡ መረጃ ሃይል ነው!!

 

 

Read 7643 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 11:05