Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 September 2012 10:39

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የለውጥ ጎዳና ላይ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ3 ሳምንታት በኋላ ወደ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከሱዳን አቻው ጋር የሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት እንደሳበ ነው፡፡ ሁለቱ ጎረቤታማቾች ከ2 ሳምንት በፊት በኦምዱርማን ተገናኝተው  ሱዳን 5ለ3 ብታሸንፍም ጥቅምት 4 ላይ በሚኖራቸው የመልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ በሜዳዋ ተጠቃሚ ሆና ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ የምታልፍበት ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጥሮላታል፡፡

ቤት ለእንቦሳ

በዓለም እግር ኳስ ሁልጊዜም በደጋፊው፣ እና በሜዳው የሚጫወት ቡድን ሰፊ የማሸነፍ ዕድል ይኖረዋል፡፡ እንደ 12ኛ ተጨዋች የሚቆጠረው ደጋፊ የሚሰጠው ማበረታቻና ማነቃቃት የባለሜዳውን ቡድን ውጤታማነት ይፈጥራል፡ በሜዳው የሚጫወት ቡድን ተጨዋቾች ከፍተኛ የራስ መተማመን ይኖራቸዋል፡፡ ለጨዋታው የሚሰለፉት በቤታቸው አድረው፤ በረጅም ጉዞዎች ሳይጐሳቆሉ እንዲሁም በለመዱት የአየር ንብረት የተሻለ አቋምና ብርታት ይዘው ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል እንግዳው ቡድን ያለሜዳው በመጫወቱ ጫና አለበት፡፡ የባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች ጩኸት፣ የአየር ንብረትን አለመላመድ፣ በጉዞ እና በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠር ድክመት ለእንግዳው ቡድን ለማሸነፍ መቸገር ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ጥቅምት 4 ላይ በደቡብ አፍሪካ ወደሚስተናገደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሱዳንን በመልስ ጨዋታ የምታስተናግደው ኢትዮጵያ ሜዳዋን ተጠቅማ በሁለት ንፁህ ጎሎች በማሸነፍ የማለፍ እድሏ ሰፊ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ሰውነት

የ59 ዓመቱ ሰውነት ቢሻው ወደ አሰልጣኝነት ሙያ የገቡት በቁጭት ነበር፡፡ በተጨዋችነት ዘመናቸው ለጎጃም ምርጥ፤ ለወሎ ምርጥ እና ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቡድኖች ቢጫወቱም እንደፍላጎታቸው ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ አለመቻላቸው ወደ አሰልጣኝነት ሙያው እንዲገቡ አነሳስቷቸዋል፡፡ በጀርመን አገር የእግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ አሰልጣኝነት ትምህርት የወሰዱት አሰልጣኝ ሰውነት በቀለም ትምህርታቸውም የባዮሎጂ መምህር ሆነው በመድሃኒያለም ትምህርት ቤት ሰርተዋል፡፡ በእግር ኳስ አሰልጣኝነት ከ30 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው አቶ ሰውነት ቢሻው በክለብ ደረጃ በአገር ውስጥ የእርሻ ሰብል፤ የመብራት ሃይል፤ የትራንስ፤ የሙገርና የኒያላ ክለቦችን ከማሰልጠናቸውም በላይ ከአገር ውጭ በየመን ክለብ በመስራትም ልምድ አላቸው፡፡ ጠንክሮ የሚሰራ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል በሚለው ምክራቸው የሚታወቁት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በስፖርት ቤተሰቡ‹ሳይንስ› በሚለው ቅፅል ስያሜ ይጠራሉ፡፡ ይህ ስም የተሰጣቸው ለዘመናዊ እግር ኳስ ስፖርት ሳይንሳዊ የስልጠና መንገድ ጉልህ አስተዋፅኦ አለው በሚል በሚከተሉት ጠንካራ እምነታቸው ነው፡፡ በቀልደኝነታቸው፤ በአዝናኝነታቸው እና በስራቸው የሚያሰለጥኗቸው ተጨዋቾች ከእግር ኳስ ውጤታማነታቸው ባሻገር በትምህርት እና በግል ህይወታቸው መሻሻል እንዲኖራቸው በሚሰጡት ምክር እና ድጋፍም ከበሬታ አግኝተዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ ለተጠየቁት ሁሉ በቂ እና አዝናኝ ምላሽ በመስጠትም በሚዲያ ባለሙያዎች የሚደነቁ ሰው ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ባለፈው 1 ዓመት ባስመዘገቡት ውጤት ተሳክቶላቸዋል፡፡ የቤልጄማዊው ቶም ሴንትፌይት ረዳት የነበሩት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ለ2ኛ ጊዜ የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን መስራት ከጀመሩ 1 ዓመት ሊሆናቸው ነው፡፡ አስቀድሞ ከ2004 እሰከ 2006 እኤአ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት መርተው ነበር፡፡

በ2005 እ.ኤ.አ በሩዋንዳ ላይ በዋና ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በ2004 እ.ኤ.አ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በወጣት ብሔራዊ ቡድን ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችን ያሸነፉ ናቸው፡፡ በ2001 እ.ኤ.አ በረዳት አሰልጣኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሴካፋን ዋንጫ ማግኘትም ችለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከ7 ዓመት በፊት በብሔራዊ ቡድኑ ሲሰሩ በ5 ዓመት ውስጥ 3 የሴካፋን ዋንጫ ማግኘታቸው ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በተጨማሪም አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የታዳጊ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በመስራት ቦትስዋና ጋብሮኒ ላይ በተደረገ የአፍሪካ ታዳጊዎች ሻምፒዮና አራተኛ ደረጃ ለማግኘትም በቅተዋል፡፡

በአሁን ጊዜ በ30ሺ በር ወርሃዊ ደሞዛቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውዱ ተከፋይ የሆኑት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ባለፈው 1 ዓመት ብሔራዊ ቡድኑን በኃላፊነት ይዘው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤ የሚሆን ውጤት ለማስመዝገብ ከጫፍ ደርሰዋል፡፡ በትራንስፈርማርኬት ዶትሲኦዶትዩኬ ድረገፅ ላይ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስኬት ላይ በተሰራ አሃዛዊ ስሌት መሰረት የአሰልጣኝነታቸው ስኬትም ድል 33.33 በመቶ፤ አቻ 50 በመቶ እንዲሁም ሽንፈት በ16.67 በመቶ ተተምኗል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑን ይዘው ካደረጓቸው 6 ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከ3 ግጥሚያዎች ሁለቱን በአቻ አንዱን ሽንፈት እንዲሁም በዓለም ዋንጫ የማጣርያ ግጥሚያ 2 ድልና አንድ አቻ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

ቡድናቸው በተቃራኒ ቡድን ላይ 12 አግብቶ 7 ተቆጥሮበታል፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ አንድ ጨዋታ ቀርቶታል፡በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል ለምታስናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣሪያ ደግሞ ምድብ 1ን እየመራ ነው፡፡

ፕሮፌሽናሎች ያስፈልጉናል...?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ዋና ውድድር እና የማጣሪያ ግጥሚያዎች ላይ ለብቁ ፕሮፌሽናል ደረጃ የበቁ ተጨዋቾችን በስብስቡ ባለመያዙ ይለያል፡፡ ከቡድኑ ተጨዋቾች ከኢትዮጵያ ወጣ ብለው በመጫወት ሊጠቀሱ የሚበቁት በግብጽ ክለብ የሚጫወተው ሳላሃዲን ሰይድና ዘንድሮ በቬይትናም ሊግ ለሚወዳደር ክለብ የሚጫወተውና በደቡብ አፍሪካ ክለቦች በመጫወት ልምድ ያለው ፍቅሩ ተፈራ ብቻ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዘንድሮው ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚጫወቱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ለመቀላቀል የሚያደርገውን ጥረት እንደቀጠለ የኮምኒኬሽን ክፍሉ ገልፆልናል፡፡ የኮምኒኬሽን ክፍሉ ሃላፊ አቶ መላኩ ለስፖርት አድማስ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት በውጭ አገር ያሉ ተጨዋቾችን ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ለመቀላቀል በሚደረግ ጥረት የመጀመርያ ስራዎች ከልጆቹ ጋር ግንኙነት መፍጠር፤ ከዚያም ከቤተሰቦቻቸው ጋር መመካከር፤ የሚጫወቱበትን ክለብና የሚኖሩበትን አገር የእግር ኳስ ፌደሬሽን ባሉት ዓለም አቀፍ ደንቦች ዙርያ ማግባባት እና ማስፈቀድ መሰራት ይኖርበታል፡፡

እነዚህ ተግባራት ከተከናወኑ በኋላ ደግሞ ተጨዋቾቹ ወደ አገር ቤት ተመልሰው እንዲመጡ ፌዴሬሽኑ ሙሉ የጉዞ ወጨ ፓስፖርት እና አስፈላጊውን ሰነዶች በፈቃደኝነት ያዘጋጃል፡፡ በዚህ መንገድ ተጨዋቾቹ ወደ አገር ቤት መምጣት ከቻሉ ቀጣዩ ስራ ተጨዋቾቹን ከአሰልጣኙ ጋር በማገናኘት _ብቃታቸውን እንዲያሳዩ ማድረግ፤ ካሉት የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች ጋር እንዴት ሊጣጣሙ እንደሚችሉ ክትትል በማድረግ ይሰራል፡፡ አቶ መላኩ አየለ ለስፖርት አድማስ በሰጠው መረጃ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ሲያደርግ በቆየው ጥረት በተለይ ሁለት ተጨዋቾችን ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ለመቀላቀል ተንቀሳቅሶ ነበር፡፡ አንዱ በኖርዌይ በሚገኝ ክለብ የመጫወት እና ዮሐንስ ማርኪንግ የተባለ ልጅ ነበር፡፡ ይህን ተጨዋች ወደ አገር ቤት ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ብዙም ባይሳካለትም ፌደሬሽኑ በተጨዋቹ ላይ የሚያደርገውን ክትትል እንደቀጠለ መሆኑን አቶ መላኩ ያስረዳል፡፡

በሌላ በኩል ግን በስዊድን በመገኝ አንድ ክለብ የመጫወተውን የአጥቂ መስመር ተሰላፊውን የሱፍ መሃመድ ለማምጣት በተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጭ ነገሮች እየታዩ ናቸው፡፡ የሱፍ መሃመድን ወደ አትዮጵያ ብሄራወ ቡድን ለመቀላቀል አባቱ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን የሚናገረው አቶ መላኩ ፓስፖርቱ መምጣቱንና የቀረው ነገር ከሚጫወትበት ክለብ ጋር መስማማት ብቻ መሆኑን አብራርቷል፡፡

የየሱፍ መሃመድ መምጣት እውን ከሆነ የብሄራዊ ቡድኑ የአጥቂ መስመር እንደሚያጠናክርም ገልጿል፡፡ በእርግጥ ብሔራዊ ቡድኑ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ልምድ ማጣቱ ይጐዳዋል፡፡ አንዳንድ የመረጃ ድረገፆችን በማሰስ ለመረዳት እንደተቻለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች የስዊድኑ የሱፍ እና የኖርዌዩ ዮሃንስ ብቻ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያዊ ደም ያላቸው ተጨዋቾች በተለያዩ የዓለም አገራት ይገኛሉ፡፡

በእንግሊዝ አማኑዌል ፋንታሁንና ፊልሞን አርአያ የሚባሉ ልጆች በቼልሲና በኒውካስትል ክለቦች ይገኛሉ የሚባል መረጃ አለ፡፡ በብራዚሉ ኤፍሲ ኢንድፔንደንቲ ሳሙኤል አለሙ፤ በግብፁ ክለብ ዛማሌክ አቤል አጥላው በዩክሬን ሊግ ትዕግስቱ የሚባሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾች እንዳሉም ይገልፃል፡፡ ፌዴሬሽኑ እነዚህን ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችንም ካሉበት ለማሰባሰብ የሚያደርገውን ጥረት መቀጠል ይኖርበታል፡፡

ማልያዎችና ቅጽል መጠሪያዎች

ባለፉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ኢንተርናሽናል ግጥሚየዎች የሚለብሰው ማልያ አንድ ወጥ መልክና ቀለም አልነበረውም፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑ ከ5 በላይ የተለያዩ ቀለሞችና ገፅታዎች ያሉአቸው ማልያዎችን ሲለብስ ታይቷል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የኮሚኒኬሽን ክፍል ሃላፊ የሆነው አቶ መላኩ አየለ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና መለያ የባንደራውን ቀለማት የያዘው ማልያ ነው፡፡ይህም ከላይ አረንጓዴ ሹራብ ፣ ቁምጣው ቢጫ እንዲሁም ገምባሌው ቀይ የሆነና በሹራቡ ኢትዮጵያ እና ቁጥር የተፃፈበት ነው፡፡ ይሁንና ብሄራዊ ቡድኑ  ተመሳሳይ ማልያ በደረቱ ላይ ምንም ነገር ሳይፃፍበት የታጠቀበት ግጥሚያ አጋጥሟል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ ቢጫ የሆነ እና በሹራቡ ደረት ላይ ኢትዮጵያና ቁጥር የተፃፈበት ትጥቅም ለብሶም ያውቃል፡ ከላይ የተጠቀሱትን ማልያዎች ብሔራዊ ቡድኑ ለ2012 የአፍሪካ ዋንጫ ከናይጄሪያ ጋር በተደረጉ ሁለት የደርሶ መልስ የማጣርያ ጨዋታዎች ለብሷቸው ነበር፡፡

ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ ቀይ ትጥቅ ለብሶ ደቡብ አፍሪካን በሩስተንበርግ ገጥሟል፡ በአንድ ወቅት በሴካፋ ውድድር ላይ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ ከላይ የሚለብሰው  እጀታው አረንጔዴ እንዲሁም በቢጫና አረንጔዴ ሸንተረሮች የተዥጐረጐረ ሹራብ እና ቀይ ቁምጣና ገምባሌ ያለው ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን ብሔራዊ ቡድኑ በአምዱርማን የሱዳን አቻውን ሲገጥም ደግሞ የለበሰው ማልያ ደግሞ ከጐኑ አረንጓዴ ያለው መደቡ ቢጫ ቀለም የሆነ በደረቱ ላይ ኢትዮጵያና ቁጥር የተፃፈበት ሹራብ ከአረንጔዴ ቁምጣና ቢጫ ገምባሌ ጋር ነው፡፡ አንድ ብሔራዊ ቡድን ደረጃውን የጠበቀ የሚሆነው በኢንተርናሽናል ግጥሚያዎች በሜዳውና በሜዳ ውጭ ከሌሎች የሚለይበትን ሁለትና ሦስት ማልያዎች በቋሚነት መጠቀሙ ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የኮሚኒኬሽን ክፍል በጉዳዩ ላይ በሰጠው ማብራርያ የብሄራዊ ቡድኑ ማሊያዎች አንዳንድ ጊዜ ያልተለመደ ቀለም የሚኖራቸው ከሜዳ ውጭ በሚደረጉ ጨዋታዎች ለባለሜዳው ቡድን በሚሰጥ የምርጫ እድል መደበኛውን ማልያ ለመጠቀም ስለሚያስቸግር ነው፡፡

የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለብሄራዊ ቡድን የሚጠቀመውን ማልያ በፈለገው ጊዜ የሚያገኘው ከፌደራል ስፖርት ኮሚሽንና ከኦሎምፒክ ኮሚቴው እንደሆነ የገለፀው አቶ መላኩ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ስፖርት ኦፊሴላዊ ትጥቅ አቅራቢ አዲዳስ በመሆኑ ትጥቆቹ በዚያ መንገድ የሚገኙ ናቸው ብሏል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እጀታው አረንጔዴ ሆኖ እንዲሁም በቢጫና አረንጔዴ ሸንተረሮች የተዥጐረጐረ ሹራብ እና ቀይ ቁምጣና ገምባሌ ያለውን ማልያ እያዘጋጀ መሆኑን የገለፀው የኮምንኬሽን ክፍሉ ይህ ማልያ በደረቱ ላይ ኢትዮጵያን የሚወክል አርማ የሚሰፍርበትና በክንዶቹ ላይ በአንድ ጎን የስፖርታዊ ጨዋነት አርማ በሌላ ጎን ደግሞ የካፍ ወይም የፊፋ አርማ ያረፈበት እንደሚሆን አስረድቷል፡፡

ወደፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለብሄራዊ ቡድን የሚመጥንና በሚፈለግ ዲዛይንና ቀለም የተሰራ ማልያ ራሱን ችሎ ለማቅረብ የነደፈው ፐሮጀክት እንዳለ በመግለፅም አዲዳስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ትጥቅ አቅራቢ ኩባንያዎችን በማወዳደር ለማሰራት ሃሳብ መኖሩንም ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በብሔራዊ ቡድኑ ቅጽል ስያሜም ዙርያ መደናገሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ በተለይ ባለፈው 1 ዓመት ውስጥ የተለያዩ የአፍሪካ መገናኛ ብዙሐናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን “ጥቁር አናብስት” Black lions ብለው እየጠሩት ይገኛል፡፡ በብዛት የሚታወቀው የብሔራዊ ቡድኑ ቅጽል ስም ግን ዋልያዎቹ የሚባለው ነው፡፡የእግር ኳስ ፌደሬሽኑም በኦፈሴላወ ደረጃ ብሄራወ ቡድኑን የሚወክለው ዋልያዎቹ የሚለው ስያሜ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡

አንዳንድ የመረጃ ምንጮች በበኩላቸው ለብሔራዊ ቡድኑ ዋልያዎቹን ሆነ ጥቁር አናብስት የሚሉትን ስያሜዎች ደርበው እየተጠቀሙ ናቸው፡፡ “ብላክ” ላዮንስ” በንጉሱ ዘመን ፋሽስት ጣሊያንን ይዋጉ የነበሩ የኢትዮጵያ ልዩና ዘመናዊ ወታደሮች መጠሪያ የነበረ ነው፡፡ ዋልያ ደግሞ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ብርቅዬ የዱር እንስሳ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ታድያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቱ ቅጽል ስያሜ ይመስለዋል፡፡ ዋልያዎቹ ወይስ ጥቁር አናብስት፤ አሊያስ ሁለቱም?

ለአፍሪካ ዋንጫ ብናልፍም ባናልፍም

ከ31 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ታሪክ ደግሞ ለ10ኛ ጊዜ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ታረጋግጣለች፡፡  ይህ ስኬት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት ጉልህ ተጽእኖ ይፈጥራል፡፡ የመጀመሪያው ለውጥ አገሪቱ በፊፋ አሁን ካለችበት የእግር ኳስ ደረጃ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት መነሳቷ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት በእግር ኳስ ደረጃው ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል፡፡ በ2004 ዓም በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ  24 እርከኖችን በማሻሻል  በዓለም 114ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ በአፍሪካ ደግሞ 32ኛ ደረጃን ይዟል፡፡

ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከበቃ ኢትዮጵያ ምናልባት አሁን ያለችበት 114ኛ ደረጃ ተሻሽሎ በ70ዎቹ እና 80ዎቹ ተርታ ሊገባ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ከፍተኛውን እርከን ያስመዘገበችው ከ10 ዓመታት በፊት 85ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ነበር፡፡ ይህ የደረጃ እድገት ደግሞ ለኢትዮጵያ ተጨዋቾች የፕሮፌሽናልነት ዕድልን የሚፈጥር ይሆናል፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲታለፍ ደግሞ ጎን ለጎን የምድብ ማጣሪያውን እየመራበት በሚገኘው የዓለም ዋንጫ ስኬታማ ሆኖ እንዲፎካከር ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች በአትሌቲክስ ስፖርት ገናና ብትሆንም እግር ኳስን በከፍተኛ ደረጃ የሚወድ ከ85 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያለባት አገር ናት፡፡

ከ56 ዓመታት በፊት የአፍሪካ ዋንጫን ከመሰረቱ አገራት አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ ለአህጉሪቱ ስፖርቱን በፈርቀዳጅነት በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና ነበራት፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ይህንን ትስስሯን ማደስ ነው፡፡ በእግር ኳስ የሚገኝ ስኬት በኢትዮጵያውያን መካከል ፍቅርን ወንድማማችነት እና ብሄራዊ ስሜትን በማዳበር የሚፈጥረው በጎ ተፅእኖ ስለሚኖር ሁላችንንም ያጓጓል፡፡ ስለሆነም አገሪቱ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ብታልፍም ባታልፍም ለስፖርቱ እድገት የሚሆኑ ተግባራት በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍተው መቀጠል አለባቸው፡፡ በየክልሉ ያሉ ስታድዬሞች ግንባታቸው በአፋጣኝ ተጠናቅቆ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 አመታት አፍሪካ ዋንጫን እንድታስተናግድ ዘመቻ መደረግ አለበት፡፡

አገሪቱ በሌሎች የአፍሪካ ዋንጫና እና የዓለም ዋንጫ  ዋና ውድድሮች እና ማጣርያዎች  ተፎካካሪ እንድትሆን የሚያስችሉ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚዎች እንዲስፋፉ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን ግብዓት የሚሆኑ የታዳጊ እና ወጣት ብሄራዊ ቡድኖች መቋቋም አካዳሚዎቹ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ከአፍሪካ ምርጥ ፌደሬሽኖች ተርታ ለመሰለፍ ራዕይ ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን  በሜዳ ላይ በአገር ውስጥ፤ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከመሳተፍና ውጤታማ ከመሆን ባሻገር በስፖርቱ ፕሮፌሽናሊዝም እንዲስፋፋ የገንዘብ ምንጮች እና ገቢዎች እንዲበዙ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

 

 

Read 4103 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 10:54