ስደት
ከጊዜ ተጣልቶ - እድሜውን ያለፈ
አፍላ ቁንጅናውን - በቀን ያረገፈ
ስሙን በመስቀል ላይ - ደስ ብሎት የጻፈ
እኔን መሳይ አለ ....................
ጡት እንዳጣ ህፃን - ራሱን ያኮረፈ !
--
እግር እንዳጣ ሰው - ልቡ እያነከሰ
ለትዳር ሲያስቡት - እየመነኮሰ
እንደ ገብስ ዛላ - ከአንገት አጎንብሶ
እንደ ቁስለኛ ወታደር ...........
እድሉን መሬት ላይ - ያነባል መልሶ!
--
ያልታለበ መቅኔው - ደርቆ ከረጢቱ
ያልተሰማ ድምጹ - ሰልሎ ከአንገቱ
በምልክት ቋንቋ - የሚያወራ በዓይኑ
እኔን መሳይ አለ
ድንገት የሚባርቅ - ሲመጣ ሰይጣኑ!
--
ልቡን የሚሰጠው - ሰሚ ጆሮ ሽቶ
መንገድ የሚያሳየው - ሽማግሌ አጥቶ
በሀሳብ የመነነ - ቀዬ ቤቱን ትቶ
በኔ ትውልድ መሀል - ከጥላው ተጣልቶ
ሌላ ትውልድ አለ
ሀገር የለቀቀ - የሕልም ድልድይ ሰርቶ!
(ነፃነት አምሳሉ)
Published in
የግጥም ጥግ
Latest from Administrator
- የእስራኤል እና የኢራን ፍጥጫ
- Insights on Israel's Response: Interview with Mr. Tomer Bar-Lavi, Chargé d’Affaires at the Embassy of Israel to Ethiopia
- Barr, a vocal Trump critic, says he will ‘support the Republican ticket’ in November
- Iran president warns of ‘massive’ response if Israel launches ‘tiniest invasion’
- "አልሞቷል" ፊልም ዛሬ በዓለም ሲኒማ ይመረቃል