Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 15 September 2012 14:10

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ 1 ጨዋታ ቀራት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥቅምት 4 ላይ በአዲስ አበባ ከሱዳን አቻው ጋር በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሉን ሊወስን ነው፡፡  ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ሰሞን በኦምዱርማን የመጀመርያው ጨዋታቸውን አድርገው  ሱዳን 5ለ3 አሸንፋለች፡፡ በጨዋታው የመጀመርያው ግማሽ  የተጠናቀቀው በሱዳኖች የበላይነት  3ለ1  በሆነ ውጤት ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀዳሚውን ግብ በመጀመርያው ግማሽ ጌታነህ ከበደ ያስቆጠረ ሲሆን በሁለተኛው ግማሽ ደግሞ ሁለተኛዋን ግብ አዳነ ግርማ፣ ሦስተኛዋን ደግሞ ሥዩም ተስፋዬ ከመረብ አዋህደዋል፡፡ የጎረቤታሞቹ ፍጥጫ እስከ 82ኛው ደቂቃ 3ለ3 አቻ ውጤት ይዞ ነበር፡፡

ካሜሩናዊው ዳኛ በሁለት ደቂቃ ልዩነት አከታትለው ሁለት የፍጹም ቅጣት መስጠታቸው ግን ውጤቱን ቀይሮታል፡፡ ሁለቱ ፍጹም ቅጣቶች ተገቢ እንዳልነበሩ የኢትዮጵያ ቡድን ተጨዋቾች የገለፁ ሲሆን አንዳንድ ዘገባዎችም የተፈጠረው ክስተትና ዳኝነቱ  አግባብ እንዳልሆነ አትተዋል፡፡ በሱዳን የሚኖሩ አራት ሺ ኢትዮጵያውያን ጨዋታው በመከታተል ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ በ2013 ደቡብ አፍሪካ ለምታስተናግደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ለመብቃት በ3ኛ ዙር የመጨረሻ ማጣርያ አንድ የመልስ ጨዋታ ብቻ በሜዳዋ ማድረግ ይቀራታል፡፡ በዋልያዎቹ  በመጀመርያው ጨዋታ ከሜዳ ውጭ የተመዘገቡት 3 ጎሎች  የማለፍ እድሉን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያጋድል አድርጓል፡፡

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የመልስ ጨዋታው የሚካሄደበት ጥቅምት 4 ታሪካዊ ቀን ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብና የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በአዲስ አበባ   በዚያ ቀን የሚደረገውን የመልስ ጨዋታን በእልህና በወኔ፣በጠንካራ ዝግጅት ይጠባበቃሉ፡፡

በኦምዱርማን በሁለቱ ቡድኖች ተደርጎ ከነበረው የመጀመርያ ጨዋታ በፊት የሱዳን አሰልጣኝ ማህመድ ማዝዳ አብደላህ ከካፍ ኦንላይን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ኢትዮጵያን ዝቅ አድርገው እንደማይመለከቱ ገልፀው ነበር፡፡ አሰልጣኙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ መሻሻል እንደሚገኝ ሲጠቁሙ ለረጅም ጊዜያት የራቁትን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለመመለስ ካላቸው ጉጉት አንፃር ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ መስክረው ነበር፡፡

በካፍ ኦንላይን ቃለ ምልልሳቸው ወደ የአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ሁለቱ ጎረቤታማቾች እኩል እድል እንዳላቸውም ከጨዋታው በፊት የተናገሩት ዋና አሰልጣኙ  ከጨዋታው በኋላ ግን በአዲስ አበባ የሚኖራቸው የመልስ ጨዋታ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡  በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተከላካይ አማካይ መስመር የሚሰለፈው የመብራት ሃይሉ አስራት መገርሳ  ለካፍ ኦንላይን በሰጠው አስተያየት በመልሱ ጨዋታ በሜዳችን ተፋልመን ለአፍሪካ ዋንጫ የምናልፍበትን እድል ፈጥረናል ሲል ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ካርቱም ላይ ከሱዳን አቻው ጋር ያደረገው ግጥሚያ በታክቲክ የታጠረ ከባድ ጨዋታ እንደነበር የገለፀው አስራት መገርሳ በመጀመርያው ግማሽ ሱዳኖች በጨዋታ ከፍተኛ ብልጫ ቢወስዱም በሁለተኛው ግማሽ ቡድኑ በእረፍት ከአሰልጣኙ ያገኘውን መመርያ ተግባራዊ በማድረግ ውጤቱን ሊያጠጠብ መቻሉን አብራርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው በካርቱም የተመዘገበው ውጤት ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሉን በሜዳችን እንድንወስን አድርጓል ብለው ለካፍ ኦንላይን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ቡድናቸው ወደ ሱዳን የተጓዘው በጥሩ ጨዋታ ውጤታማ ለመሆን አቅዶ እንደነበር ሲገልፁ ተጨዋቾቻቸው ያገቧቸው 3 ጎሎች በምርጥ ጨዋታ የተገኙ ምርጥ ጎሎች መሆናቸውን አድንቀው ለሱዳን ብሄራዊ ቡድን ባለቀ ሰዓት የተሰጡት ሁለት ኢሊጎሬዎች አግባብ አልነበረም ብለዋል፡፡ከ3 ሳምንት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመልስ ጨዋታው ሱዳንን አስተናግዶ ማሸነፍ ከተሳካለት አገራችን በአፍሪካ ዋንጫ ከ31 ዓመታት በኃላ ለመጀመርያ ግዜ እንዲሁም በታሪኳ ለ10ኛ ግዜ መሳተፏን ታረጋግጣለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መግለጫ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድሉን በ2 ቀን በማሸጋሸግ ኦክቶበር 24 ላይ በደርባን ደቡብ አፍሪካ ለማውጣት እንደወሰነ ታወቀ፡፡ ካፍ በ2012 ኢኳቶርያል ጊኒ እና ጋቦን በጣምራ ያዘጋጁት 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በአጠቃላይ 6.6 ቢሊዮን ድምር ተመልካች በቴሌቭዥን ስርጭት በነበረው የ87072 ሰዓታት ሽፋን ማግኘቱንም ሲያመለክት የአፍሪካ ዋንጫ በቀጣይ ደቡብ አፍሪካ ስታስተናግደው የላቀ የቲቪ ስርጭት እንደሚኖረውም ገልጿል፡፡

 

 

Read 3742 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 14:21

Latest from