Saturday, 11 December 2021 13:18

በንፁሃን ላይ የተፈፀሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

     • በጋሸና፣ በኮምቦልቻና በአንፆኪያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር ተገኝቷል
     • ሽብርተኛው ቡድን በሞላሌ ህዝቡን ለስብሰባ በመጥራት ተመሳሳይ የጅምላ ጭፍጨፋ ለማድረግ ቢሞክርም ህዝቡ ወደ ስብሰባው ባለመሄዱ   ሳይሳካለት ቀርቷል
     • በሸዋ ሮቢት በአሸባሪው ቡድን የተደፈሩ አዛውንት እናት ራሳቸውን አጥፍተዋል
             
         ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን በጋሸና፣ በአንፆኪያና በኮምቦልቻ ከተሞች በግፍ የጨፈጨፋቸው ንጹሃን የተቀበሩበት የጅምላ መቃብሮች እየተገኙ ነው። ቡድኑ በፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ ህፃናት፣ አራሶች፣ የአእምሮ ህሙማንና አዛውንቶች መገደላቸውም ታውቋል። በሰሜን ሸዋ ዞን አንጾኪያ ገምዛ ወረዳ አምቦውሃ ቀበሌ ውስጥ የተጨፈጨፉትን ንፁሃን ለመታደግ ያልቻተለው መረጃ ለመስጠት የሚቻልበት ዕድል  በመታጣቱ መሆኑም ተገልጿል።
የሽብር ቡድኑ ወሯቸው በነበሩት በሰሜን ወሎ ጋሸና እና በሰሜን ሸዋ አንጾኪያ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ዞን በሆነችው ኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ በርካታ የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል። ቡድኑ በተለይም ኮምቦልቻ ከተማን ወርሮ በቆየበት 39 ቀናት በርካታ ተቋማትን አውድሟል፣ ዘረፋ ፈጽሟል፤ በርካታ ህፃናትንና  አዛውንት እናቶችን ጭምር አስገድዶ ደፍሯል። ንጹሃንን በጅምላ ጨፍጭፏል። በከተማዋ ከሚገኘው የደረቅ ወደብ ተርሚናል ከ800 በላይ ኮንቴነሮች ሙሉ ዕቃዎችን ጭኖ ወስዷል። ጢጣ በሚባለው ቦታ የሚገኘውን ነዳጅ ማጠራቀሚያ ሙሉ በሙሉ ዘርፏል።
ቡድኑ በኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ በንፁሃን ላይ በፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ የተገደሉ ንጹሃን የተቀበሩባቸው የተለያዩ የጅምላ መቃብሮች እየተገኙ ነው። እስካሁን በኮምቦልቻ ከተማ ብቻ በሶስት ኮሌጆች ማለትም ኮምቦልቻ ቴክኒክ ኮሌጅ፣ ኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅና በቃሉ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ውስጥ የጅምላ መቃብሮች ተገኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በኮሌጆቹ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለጅምላ ቀብር የተዘጋጁ ጉድጓዶችና መቆፈሪያ ስካቫተሮችም ተገኝተዋል። የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አህመድ የሱፍ፤ “በከተማችን የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ንፁሃን ሰዎች በግፍ ተረሽነዋል፤ በርካቶችም ደብዛቸው ጠፍቷል”-ብለዋል።
ሰይድ አያሌው በኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ ነዋሪ ሲሆን ከተማዋ በህውኃት ወራሪ ቡድን ከተያዘችበት ጊዜ ጀምሮ በየዕለቱ የተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች፣ ዘረፋዎችና የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች እጅግ ዘግናኝና ታሪክ ይቅር የማይላቸው ወንጀሎች ናቸው ብሏል።
“ቡድኑ በጅምላ የረሸናቸውን ወጣቶች አስክሬን በሲኖትራክ ወደ ኮምቦልቻ ቴክኒክ ኮሌጅ ይዞ ሲወጣ በአጋጣሚ ከስፍራው ነበርኩ። ዘራፊው ቡድን ከኮሌጁ የሚዘርፋቸውን ዕቃዎች በመኪና ላይ እንድንጭን እያደረግን ስለነበር ከቦታው ነበርኩ። እናም ሲኖትራኩ አስክሬኖቹን ጭኖ መጣና ከተቆፈረው ጉድጓድ ጫፍ ላይ ቆሞ አስክሬኖቹን ወደ ጉድጓድ ውስጥ ገለበጣቸው። ከዛም አፈሩ በስካቪያተር ወደ ጉድጓዱ መለስ መለስ ተደረገና በሩሎ መኪና ተነዳበት። ይህንን ሁሉ ግፍ ቆመን እያየን ለማልቀስና ለመጮህ አይደለም የሃዘን ገፅታ እንዲታይብን አይፈቀድልንም ነበር። ወደ ስራችሁ ግቡ ነበር የተባልነው። መኪናው  አስክሬኖቹን ጭኖ ሲመጣ ደሞ እየተንጠባጠበ ነበር። ሁኔታውን መቋቋም አቅቷቸው ያለቀሱና የጮሁ ልጆችን በጥይት ገድሎ እዛው ጉድጓድ ውስጥ ጨምሯቸዋል። ይህ ሰይጣን እንኳን ሊፈጽመው የማይችል እጅግ አረመኒያዊ የሆነ ዘግናኝ ወንጀል ነው።  ይህን ወንጀል የፈጸሙ አረመኔዎች ተይዘው ለህግ ሲቀርቡ ማየት የኔ ብቻ ሳይሆን የመላው የኮምቦልቻ ህዝብ ፍላጎት ነው። ወንጀሉ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ ለሽብር ቡድኑ እርዳታና ድጋፍ የሚያደርጉ በርካታ የከተማችን ነዋሪዎችም ነበሩ፡፡ እጅግ የሚያሳዝን ወንጀል ነው የተፈጸመው” ይላል የኮምቦልቻ ነዋሪው ሰይድ አያሌው፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን አንጾኪያ ወረዳ አምቡሃ ቀበሌ ውስጥ የተፈፀመውን የጅምላ ጭፍጨፋ አስመልክቶ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪው አቶ ታደሰ ገ/ፃዲቅ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፤ በአካባቢው በአሸባሪው ትህነግ እና በሸኔ ቡድን ጥምር ሃይሎች  ጥቃት መፈጸሙንና በአንጾኪያ ወረዳ አምቦውሃ ቀበሌ ውስጥ ብቻ 67 ንፁሃን በግፍ ተጨፍጭፈው በጅምላ ተቀብረዋል ብለዋል፡፡ በወረዳው የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የተናጠል ግድያ መፈጸሙን የገለፁት የዞኑ አስተዳዳሪ፤ በአንድ ጊዜና በአንድ ቦታ ላይ ግን 67 ሰዎች  በግፍ ተጨፍጭፈው በጅምላ ተቀብረዋል ብለዋል። እነዚህን ንፁሃን ወገኖች ለማትረፍ ያልቻልነው በወቅቱ መረጃ ልናደርስ የምንችልበት ሁኔታ በማጣታችን ነው ያሉት አስተዳዳሪው፤ በመከላከያ ሰራዊታችንና በልዩ ሃይሎቻችን ተመትቶ በሽሽት ላይ ነበረው የአሸባሪው ቡድን በንፁሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ታውቆ መረጃውን ለህዝቡ የምናደርስበት መንገድ አላገኘንም ብለዋል።
“ይኸው ቡድን በሞላሌ ተመሳሳይ የጅምላ ጭፍጨፋ ለማድረግ አቅዶ በሺዎች የሚቆጠሩ ገጀራዎችን ወደ ስፍራው አስገብቶ ህዝቡን በስብሰባ ሰበብ በመጥራት ለመጨፍጨፍ ማቀዱን መረጃውን በማግኘታችን ለህብረተሰቡ አስቀድመን መረጃውን በመስጠት ከአካባቢው እንዲሸሽና እንዲሰወር፣ ወደተጠራበት ስብሰባም እንዳይሄድ በማድረግ የሽብር ቡድኑ ፍላጎት እንዲከሽፍ አድርገናል” ብለዋል አስተዳዳሪው፡፡
የሽብር ቡድኑ አባላት ፊት ለፊት ከመዋጋትና ከጀግናው መከላከያ ሰራዊታችንና ልዩ ሃይሎቻችን ጋር ከመግጠም ይልቅ መንደር ለመንደር እየዞረ ሲዘርፍ፣ ሲደፍርና ንጹሃንን ሲጨፈጭፍ ነበር ያሉት የዞን አስተዳዳሪው፤ ይሄ መንደር ለመንደር  የገባው መንጋ ከጠዋቱ 2 ሰዓት በንፁሃን ወገኖቻችን ላይ የጀመረውን ጭፍጨፋ እስከ ምሽት 3 ሰዓት ድረስ በመቀጠል  በጅምላ ቀብሯል ብለዋል። በሸዋሮቢት ከተማ በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ ንፁሃን በተናጥል ተገድለዋል ያሉት የዞን አስተዳዳሪው፤ በአካባቢያችን የተፈጸመው አረመኔያዊ ተግባር በሰው ልጅ ሊፈጸም የማይችልና እጅግ ዘግናኝ  ነው ብለዋል።
በዞኑ ሸዋሮቢት ከተማ ቀበሌ 02 ውስጥ ነዋሪ የነበሩትና በአሸባሪው ሃይል በቡድን የተደፈሩት አዛውንት እናት ራሳቸውን ማጥፋታቸውን የሸዋሮቢት ከተማ ፖሊስ ገልጿል። የማገዶ እንጨት ለቅሞ በመሸጥና እንጀራ በመጋገር የሚተዳደሩት አዛውንት በልጃቸው ፊት በቡድን ከተደፈሩ በኋላ ሁኔታውን መቋቋም ተስኗቸው፣ ከዚህ  በኋላ የልጄን  ዓይን ማየት አልችልም ብለው ራሳቸውን ማጥፋታቸውም ተነግሯል።
አሸባሪው የሕውሃት ታጣቂ ቡድን በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ እስከአሁን ድረስ ከ3 ሺ በላይ የግልና የመንግስት የጤና ተቋማት መውደማቸውንና ከ3.7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለከፍተኛ የጤና ችግር መጋለጡን ከክልሉ ጤና ቢሮ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

Read 11662 times