Saturday, 11 December 2021 13:15

ብልፅግናን ጨምሮ 51 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ማካሄድ አልቻሉም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  በሃገሪቱ በህጋዊነት ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ሁለቱ ብቻ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረጋቸውን ያመላከተው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ሌሎቹ ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካበቃ በኋላ ባለው 1 ወር ጊዜ ውስጥ  አካሂደው እንዲያሳውቁት አሳስቧል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ እስከ መስከረም  2014 ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አካሂደው እንዲያሳውቁ የጊዜ ገደብ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፣ ከ53 ፓርቲዎች ሁለቱ ብቻ የጊዜ ገደቡን አክብረው ማከናወናቸው ተጠቁሟል።
በጊዜ ገደቡ ጉባኤያቸውን ያካሄዱት ፓርቲዎች  የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ  ፍትህ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 51 ፓርቲዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ  ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ማካሄድ አልቻሉም- ተብሏል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዳያካሂዱ እንቅፋት ሆኖብናል ብለው ከጠቆሟቸው ምክንያቶች መካከል አባሎቻቸው በህልውና ዘመቻው ተሳታፊ የነበሩ መሆናቸው እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስብሰባ ማካሄድ መከልከሉ እንቅፋት ፈጥሮብናል የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ምክንያቶች በሚገባ የመረመረው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ከሰሞኑ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን ብልፅግናን ጨምሮ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ያላከናወኑ ፓርቲዎች በሙሉ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ካነሳ በኋላ ባለው የ1 ወር ጊዜ ውስጥ ጉባኤያቸውን አካሂደው እንዲያሳውቁ አሳስቧል።

Read 11466 times