Saturday, 11 December 2021 13:14

የህወኃት ታጣቂዎች በቆቦ እና ጭና ሠላማዊ ሰዎችን በግፍ ጨፍጭፈዋል - ሂውማን ራይተስ ዎች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በአማራ ክልል በቆቦ እና ጭና ሠላማዊ ዜጎችን በግፍ መጨፍጨፋቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች በምርመራ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዎች ትናንት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ ባለፈው ነሐሴ እና ጳጉሜ 2013 ዓ.ም በ10 ቀናት ውስጥ የህወኃት ሃይሎች በቆቦ እና ጭና በአጠቃላይ 49 ንጹሃንን በግፍ መግደላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ነሐሴ 25 ቀን 2013 በጎንደር በምትገኘው ጭና መንደር ውስጥ በመግባት በመንደሯ በቆዩባቸው ተከታታይ ቀናት ውስጥ በ15 የተለያዩ ቦታዎች 26 ሠላማዊ ሰዎችን በግፍ መግደላቸውን ተቋሙ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በቆቦ ከተማ ደግሞ ጳጉሜ 4 ቀን 2013 ዓ.ም በአራት የተለያዩ ቦታዎች የህወኃት ታጣቂዎች ሠላማዊ ሰዎችንና አርሶ አደሮችን ኢላማ አድርገው በፈፀሟቸው ጥቃቶች 23 ሰዎችን መግደላቸውን በምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል-ተቋሙ፡፡
የህወኃት ታጣቂዎች በዚህ ድርጊታቸው የህግ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ንጹሃንን በግፍ በመግደል በጦርነት ወቅት የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት የመጠበቅ የሞራል ሃላፊነትን በመጣስ ፣ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ንጹሃንን በማጥቃት ግድየለሽነታቸውን ማሳየታቸውን አመልክቷል- ሂውማን ራይትስ ዎች፡፡
ሂውማን ራይትስ ዎች ይህን ምርመራ በሚያከናውንበት ወቅት በጭና እና በቆቦ ነዋሪ የሆኑ 36 የአይን ምስክሮችን ጨምሮ  የሃይማኖት አባቶችንና የጤና ባለሙያዎችን ምስክርነት መቀበሉን ጠቁሟል፡፡
በሪፖርቱ የተካተተው መረጃ እና የተጠቀሰው አሃዛዊ ቁጥር በስም ጭምር በሚገባ የተረጋገጡትን ብቻ መሆኑን፣ ተጨማሪ ጥቆማዎችም እንደደረሱት ያመለከተው የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት፤ በቀጣይ በገለልተኛና ተዓማኒነት ባለው ተቋም የበለጠ ምርመራ ሊካሄድ ይገባል ብሏል፡፡


Read 11437 times