Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 September 2012 14:09

2012-13 እና የአውሮፓ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በ2012-13 የውድድር ዘመን የሚካሄደው የአውሮፓ ሻምፒዮን ሊግ  በምድብ ማጣሪያ ከሳምንት በኋላ ይጀመራል፡፡ በምድብ ድልድሉ ከፍተኛ ፈተና እንደሚገጥመው የሚጠበቀው የአምናው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ማንችስተር ሲቲ ሆኗል፡፡ ከጀርመን፣ ከስፔንና ከሆላንድ የአምና ሻምፒዮኖች ጋር በተፋጠጠበት የሞት ምድብ ይገኛል፡፡ የአምናው የአውሮፓ ሻምፒዮን ቼልሲ በተደለደለበት ምድብ ከጁቬንትስ ጋር ከመገናኘቱ በቀር ብዙም የሚያስፈራ ተጋጣሚ አልደረሰውም፡፡ አርሰናልና ማን.ዩናይትድም በአውሮፓ እግር ኳስ በ2ኛ ደረጃ ከሚታዩ  ክለቦች ጋር ተደልድለዋል፡፡ ዝላታን ኢብራሞቪችን፣ ቲያጐ ሲልቫና ሌላ ተጨዋችን እስከ 138 ሚሊዮን ፓውንድ ወጭ በማድረግ ቡድኑን ያጠናከረውና ከ8 ዓመታት በኋላ በሻምፒዮንስ ሉግ የመወዳደር ዕድል ያገኘው የፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንትዠርመን በውድድር ዘመኑ የሚኖረው ተሳትፎ ትኩረት ስቧል፡፡

ስምንቱ ምድቦች

ምድብ 1 - ፖርቶ፤ ዳይናሞ ኪዩቭ፣ ፓሪስ ሴንትዥርመን፣

ዳይናሞ ዛግሬብ

ምድብ 2 - አርሰናል፣ ሻልካ፣ ኦሎምፒያኮስ ፣ ሞንትፕሊዬር

ምድብ 3- ኤሲሚላን፣ ዜኒት ፒትስበርግ፣ አንደርሌክት፣ ማላጋ

ምድብ 4 - ሪያል ማድሪድ፣ ማንችስተር ሲቲ፣ አያከስ፣ ቦርስያ

ዶርትመንድ

ምድብ 5 - ቼልሲ፣ ቫካተር ዶኔትስክ፣ ጁቬንትስ፣ ኖርጅላንድ

ምድብ 6 - ባየር ሙኒክ፣ ቫሌንሺያ ፣ ሊል፣ ባቴቦሪሶቭ

ምድብ 7- ባርሴሎና፣ ቤነፊካ፣ ስፖርታክ ሞስኮ፣ ሴልቲክ

ምድብ 8 - ማን.ዩናይትድ፣ ብራጋ፣ ጋላተሳራይ፣ ክሉጅ

ቫን ዘማን

ሆላንዳዊው ሮቢን ቫንፕርሲ ከ6 የውድድር ዘመናት በኋላ የሰሜን ለንደኑን ክለብ አርሰናል በመልቀቅ የኦልድትራፎርዱን ማን.ዩናይትድ ተቀላቅሏል፡፡ለዝውውሩ 37 ሚ.ዶላር ወጭ ሆኖበታል፡፡ ቫንፐርሲ በአርሰናል ክለብ ለ6 የውድድር ዘመን በነበረው ቆይታ 194 ጨዋታዎችን በሁሉም ውድድሮች ለክለቡ በማድረግ 132 ጐሎች አስቆጥሯል፡፡ ዘንድሮ  በማን ዩናይትድ ማልያ መሰለፍ ሲጀምርም ግብ አዳኝነቱን አልተወም፡፡ በ3 ጨዋታዎች 4 ጐሎች አግብቷል፡፡ ይሁንና ለሆላንድ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ባለፈው ሰሞን የደረሰበት ጉዳት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን አሳስቧቸዋል፡፡ ቫንፐርሲ በአርሰናል በቆየባቸው 6 የውድድር ዘመናት በተለያዩ ግዜያት ባጋጠሙት ጉዳቶች ቢያንስ 1 የውድድር ዘመንን ያህል ሳይጫወት አሳልፏል፡፡

ኢብራሞቪች

ስዊድናዊው ዝላታን ኢብራሞቪች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለፈረንሳዩ ክለብ ፓሪስ ሴንት ጀርመን መጫወት ጀምራል፡፡  ባለፉት 8 ዓመታት ጣሊያን ውስጥ በጁቬንትስ በኢንተርሚላንና በኤሲሚላን እንዲሁም በስፔኑ ባርሴሎና የተጫወተው ኢብራሞቪች የፈረንሳዩ ክለብ ፓሪስ ሴንትዠርመን 5ኛ  ክለቡ ነው፡፡ለዝውውሩ የወጣው ሂሳብ ደግሞ  ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በአጠቃላይ የ5 ክለቦች ዝውውር 210 ሚ.ዶላር ወጭ ሆኖበትም በኒኮላስ አኔልካ ተይዞ የነበረን ክብረወሰን ተረክቧል፡፡ የ30 ዓመቱ ኢብራሞቪች በፓሪስ ሴንትዠርመን የተጀመረው የእድገት እንቅስቃሴን በተመለከተ ሲናገር ክለቡ በፈረንሳይ ሊግ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ደረጃም ከፍተኛ ስኬት የሚያገኝ  ይሆናል ብሏል፡፡ ማንኛውም ትልቅ ከተማ የሚወክለው ጠንካራ ክለብ ያስፈልገዋል ያለው ኢብራሞቪች በፓሪስ ሴንትዠርመን ለ2 የውድድር ዘመናት በሚኖረው ቆይታ ዋንጫዎችን ለመሰብሰብ ከፍተኛ ትጋት እንደሚያሳይ ገልጿል፡፡

ሮናልዶ

የ27 አመቱ ክርስትያኖ ሮናልዶ ከሳምንት በፊት በሪያል ማድሪድ ባለው ቆይታ ደስተኛ አለመሆኑን ከገለፀ በኋላ በክለቡ ያለው ቆይታ  መነጋገርያ ሆኗል፡፡ በአንድ የውድድር ዘመን 11 ሚሊዮን ዩሮ ደሞዝ በማድሪድ የሚያገኘውን ደሞዝ ከታክስ በፊት ወደ 15 ሚሊዮን ዩሮ ለማሳደግ የተጨዋቹ ፍላጎት መሆኑን አንዳንድ መረጃዎች እየገለፁ ናቸው፡፡

በሪያል ማድሪድ የዘንድሮው የላሊጋ አጀማመር የተበሳጩ የክለብ ደጋፊዎች የሮናልዶ ብቃት መውረድን እንደሰበብ እየጠቀሱ ቢሆንም ተጨዋቹ ክለቡ  ከሲቪያ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ምርጥ ብቃቱ እንዲመለስ በቡድን አጋሮቹ ምክርና ማበረታቻ ተደርጎለታል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ አገሩ ፖርቱጋል ከሉክዘምበርግ እና ከአዘርባጃን ጋር ተጫውታ ሁለቱንም ስታሸንፍ ጉል አስተዋፅኦ ያደረገው ሮናልዶ አሁን ትኩረቱን ወደ ክለቡ ሪያል ማድሪድ ማድረጉን ሰሞኑን የገለፀ ሲሆን በኮንትራቱ ላይ የመደራደር ጉዳይ ሳያስጨንቀው በውድድር ዘመኑ ለቀረቡት ዋንጫዎች አሸናፊነት በታታሪነት ለመስራት ያለውን ፍላጎት ገልጿል፡፡

ሮናልዶ በማድሪድ ህይወቱ ደስተኛ አይደለሁም የሚለው በክለቡ የሚያገኘውን ደሞዝ ለማስጨመር ነው መባሉ ውጥረቱን ቢያባብስም ተጨዋቹ በበርናባኦ እስከ 2015 የሚቆይበት ኮንትራት መያዙ ቆይታውን የሚያስረው ይሆናል፡፡

ቫንደርቫርት

ሆላንዳዊው ራፋኤል ቫንደርቫርት እንደ ሁለተኛ አገሩ ወደየሚመለከታት ጀርመን ገብቷል፡፡ በቦንደስ ሊጋው ለሚወዳደረው ሃምቡርግ ለ2ኛ ግዜ ተመልሶ ለመጫወት የወሰነው የቀድሞ ክለቡን ቶትንሃም ሆትስፐርስ በ13 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ሂሳብ በመልቀቅ ነበር፡፡ ለሃምቡርግ በመሰለፍ የመጀመርያ ጨዋታውንም ነገ ያደርጋል፡፡ ቫንደርቫርት ዘንድሮ ከቦንደስ ሊጋው ላለፉት 50 ዓመታት ወርዶ የማያውቀውን ሃምቡርግ በተሻለ ውጤት ለመታደግ ሃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ቫንደርቫርት ከ2005 እስከ 2008 እኤአ በሃምቡርግ ክለብ ለ3 የውድድር ዘመናት ተጫውቶ ነበር፡፡ ያኔ በመጀመርያ የውድድር ዘመኑ ለክለቡ 29 ጎሎች አግብቶ በ3ኛ ደረጃ እንዲጨርስ ሲያደርግ፤ በሁለተኛው የውድድር ዘመን በ7ኛ ደረጃ እንዲሁም በ3ኛው የውድድር ዘመን በአራተኛ ደረጃ ቦንደስሊጋውን ሲያጠናቅቅ ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ አድርጎ ሃምቡርግን በመልቀቅ ወደ ሪያል ማድሪድ ተዛውሯል፡፡ ሃሙብርግ ቫንደርቫርትን ካጣ በኋላ ባለፉት 4 የውድድር ዘመናት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚታገል ክለብ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ስፖርታዊ ጨዋነት በፋይናንስ

የአውሮፓ እግር ኳስ የሻምፒዮንስ ሊጉን ድልድል ባወጣበት እለት በአህጉሪቱ ያሉ ክለቦች ከ1 የውድድር ዘመን በኋላ ተግባራዊ መሆን በሚጀምረው የፋይናንስ  ስፖርታዊ ጨዋነት ህገ ደንብ ተገዢ እንዲሆኑ ሲያሳስብ ደንቡን በማያከብሩ ክለቦች ላይ ከትልልቅ ውድድሮች ተሳትፎ የማገድ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ አስጠንቅቋል፡፡ ከ2014 ጀምሮ የትኛውም ክለብ ባንድ የውድድር ዘመን የሚኖረው ወጭ ከ45 ሚሊዮን ዩሮ መብለጥ የለበትም፡፡

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በፋይናንስ ስፖርታዊ ጨዋነት ደንብ ላይ የጋራ ስምምነት አድርጎ የተነሳው ከ3 ዓመት በፊት ነበር፡፡ ከ1 የውድድር ዘመን በኋላ ደግሞ ደንቡን በአስገዳጅነት ሊያስፈፅም ወስኗል፡፡ የደንቡ ዋና ዓለማ ክለቦች ከገቢያቸው በላይ ወጪ በማብዛት ህልውናቸውን አደጋ ውስጥ በሚጥል የፋይናንስ እንቅስቃሴ ያለአግባብ እንዳይሰሩና በየውድድሩ ክለቦች ተመጣጣኝ የፋይናንስ አቅም እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው፡፡ ደንቡን በማያከብሩ ክለቦች ላይ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከውድድር የማገድ፤ የገንዘብ ቅጣት የመጣል ፤ የሽልማት ገንዘብ የመከልከልና በዝውውር ገበያው ህጋዊ እንዳይሆኑ በመከልከል እርምጃ ለመውሰድ አቅዷል፡፡

ከአምስቱ የአውሮፓ ታላቅ ሊጎች የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፤ የስፔኑ ላሊጋና የጣሊያኑ ሴሪኤ ክለቦች በእዳ ቀውስ ላለፉት 4 የውድድር ዘመናት መቀጠላቸው ለአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር አሳሳቢ ሆኖበታል፡፡ የእንግሊዝ ፐሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ የሆኑ 20 ክለቦች ያለባቸው እዳ ከ3.6 ቢሊዮን  ዩሮ በላይ ነው፡፡ በጣሊያን ካሉ ክለቦች አንዱ ኢንተርሚላን ባለፉት 16 ዓመታት እስከ 1.3 ቢሊዮን ዩሮ በኪሳራ አጥቷል፡፡ በስፔን ላሊጋ ካሉ ክለቦች በእዳ ከፍተኛውን ድርሻ ሪያል ማድስሪድና ባርሴሎና ቢይዙም የእዳቸው መጠን እስከ 2.5 ቢሊዮን ፓውንድ ነው፡፡

የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ሼክ መንሱር ቢን ዛዬድ በማንችስተር ሲቲ ፤ ራሽያዊው ቢሊየነር ሮማን አብራሞቪች በቼልሲ ኳታራዊው ነጋዴ ናስር አልካሄልፊ በፈረንሳዩ ክለብ ፓሪስ ሴንትዥርመን በየክለቦቹ በቢሊዮን ዶላሮች በሚገመት ኢንቨስትመንት ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት ክለቦቹን በሊጋቸው እና በአውሮፓ ውድድሮች ውጤታማ እንዲሆኑ አስችለዋል፡፡በመካከለኛው ምስራቅ የእግር ኳስ ዋጋ በ2022 ኳታር እስከምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ በ52 በመቶ እድገት በማሳየት 14 ቢሊዮን እንደሚደርስ አንድ ጥናት ሲያመለክት ከ1986 ወዲህ በዚሁ የዓለም ክፍል የዓለም ዋንጫን በቲቪ የሚመነለከቱት ብዛት በ350 ፐርሰንት ማደጉን በመጥቀስ መካከለኛው ምስራቅ ለስፖርቱ አዲስ ምእራፍ እየከፈተ ነው ብሏል፡፡ ትልልቅ የአውሮፓ ክለቦች በመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ አገራት የእግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚዎች፤ ስታድዬሞች እና ማእከሎች በመገንባትም ላይ ናቸው፡፡ ኳታር በ202 እኤአ ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ አጠቃላይ ዝግጅት እስከ 65 ቢሊዮን ዶላር በመመደብ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለ19ኛው ዓለም ዋንጫ ያወጣችው በጀት 11.4  ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ዴሊዮቴ ቢዝነስ ግሩፕ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በ2012 የአውሮፓ 20 ክለቦች ገቢ በ3 በመቶ እድገት በማሳየት ከ6 ቢሊዮን ዶላር ያለፈ ሲሆን  ለዚህም ዋናው ምክንያት ከመካከከለኛው ምስራቅ የወጡ ባለሃብቶች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጿል፡፡ የኳታሪ ፋውንዴሽን ለባርሴሎና ማሊያ ስፖንሰርሺፕ በየዓመቱ 40 ሚሊዮን ዶላር እየከፈለ ነው፡፡ የዱባዩ አየር መንገድ ኢምሬትስ በአውሮፓ በርካታ ትልልቅ ክለቦችን ስፖንሰር በማድረግ ከፍተኛ የስፖንሰርሺፕ አስተዋፅኦ ያደረገ ሲሆን የእንግሊዙን አርሰናል፤ የጣሊያኑን ኤሲሚላን፤ የፈረንሳዩን ፓሪስ ሴንትዥርመን፤ የግሪኩን ኦሎምፒያኮስና የስፔኑን ሪያል ማድሪድ ስፖንሰር በማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

የገቢ ድርሻ

ባለፈው የውድድር ዘመን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ለተሳተፉ 32 ክለቦች የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር 754.1 ሚሊዮን ዩሮ ያከፋፈለ ሲሆን ቼልሲ ዋንጫውን ሲያሸንፍ ያገኘው ገንዘብ እስከ 60 ሚሊዮን ዩሮ ሲጠጋ ሁለተኛ ደረጃ ያጋኘው ባየር ሙኒክ ደግሞ እስከ 41.73 ሚሊዮን ዩሮ ደርሶታል፡፡  የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ሰሞኑን በ14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ማጣርያ እና ዋናው ውድድር ተጨዋቾችን ለየብሄራዊ ቡድኖች በመስጠት አስተዋፅኦ ላደረጉ 575 ክለቦች 100 ሚሊዮን ዩሮ አከፋፍሏል፡፡

ከዚሁ ክፍያ 40 ሚሊዮን ዩሮ የተከፋፈለው በአውሮፓ ዋንጫው ማጣርያ ለየብሄራዊ ቡድኖቻቸው የተሰለፉ ተጨዋቾችን ላበረከቱ ክለቦች ሲሆን ቀሪው 60 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ በ14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በተካፈሉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች ተጨዋቾቻቸውን ላቀረቡ ክለቦች የተሰጠ ነው፡፡ በክፍፍሉ መሰረት ባየር ሙኒክ በ3.06 ሚሊዮን ዩሮ ከፈትኛውን ድርሻ በቀዳሚነት ሲወስድ ሪያል ማድሪድ 2.9 ሚሊዮን ዩሮ፤ ባርሴሎና 2.27 ሚሊዮን ዩሮ፤ ማንችስተር ሲቲ 2.07 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ጁቬንትስ 2.02 ሚሊዮን ዩሮ ማግኘት ችለዋል፡፡የአውሮፓ ክለቦች ደቡብ አፍሪካ አስተናግዳ ከነበረው 19ኛው ዓለም ዋንጫ ለተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖች ባሰለፏቸው ተጨዋቾች ያገኙት 70 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ብራዚል በ2014 እኤአ በምታዘጋጀው 20ኛው የዓለም ዋንጫው ይህ ክፍያቸው እንዲያድግ ፍላጎት አላቸው፡፡

ምንዛሬ

1ዩሮ  23.0618ብር

1 ፓውንድ 28.6494 ብር

1 ዶላር 18.0517 ብር

 

 

Read 6322 times Last modified on Saturday, 15 September 2012 14:22